በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመካከለኛው አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮን ጎበኙ
በ2015 ወደ 175,000 የሚጠጉ ሰዎች በሜክሲኮ የሚገኘውን የመካከለኛው አሜሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ጎብኝተው ነበር፤ ይህም ማለት በእያንዳንዱ የሥራ ቀን በአማካይ 670 ሰዎች ጎብኝተዋል ማለት ነው! አብዛኞቹ ጎብኚዎች የመጡት፣ በትላልቅ ቡድኖች ሆነው አውቶቡስ በመከራየት ለቀናት ተጉዘው ነው። አንዳንዶቹ ይህን ጉብኝት ለማድረግ እቅድ ያወጡት ከወራት በፊት ነው።
“የቤቴል ጉብኝት ፕሮጀክት”
ቤቴል ተብሎ የሚጠራውን ቅርንጫፍ ቢሮ መጎብኘት ለአንዳንዶች ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ጠይቆባቸዋል። ለምሳሌ፣ ቬራክሩዝ በተባለው የሜክሲኮ ግዛት ውስጥ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች፣ 550 ኪሎ ሜትር የሚፈጀውን የአውቶቡስ ጉዞ ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ አልነበራቸውም። ስለዚህ “የቤቴል ጉብኝት ፕሮጀክት” የተባለ ዝግጅት አደረጉ። በተለያየ ቡድን ተከፋፍለው ምግብ አብስለው መሸጥ ጀመሩ። እንዲሁም የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ሰብስበው ይሸጡ ነበር። ከሦስት ወር በኋላ ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን በቂ ገንዘብ አገኙ።
እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጋቸው የሚያስቆጭ ነው? የማያስቆጭ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሉሲዮ የተባለ አንድ ወጣት የጉባኤው አባል እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ቤቴልን መጎብኘታችን ተጨማሪ መንፈሳዊ ግቦች እንዳወጣ አነሳስቶኛል፤ በመሆኑም አሁን በጉባኤው ውስጥ ከበፊቱ ይበልጥ በሙሉ ኃይሌ እያገለገልኩ ነው።” የ18 ዓመት ወጣት የሆነችው ኤሊሳቤትም እንዲህ ብላለች፦ “ቤቴል ውስጥ የይሖዋ አገልጋዮች መለያ የሆነውን እውነተኛ ፍቅር በተግባር ማየት ችያለሁ። ጉብኝቱ አምላክን ይበልጥ ለማገልገል አነሳስቶኛል፤ በመሆኑም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ።”
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አንድ ላይ መጡ
አንዳንድ ጊዜ፣ በአንድ ቀን በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለጉብኝት ይመጡ ነበር። የጉብኝት ዴስኩ አባላት ሁሉንም ጎብኚዎች በጥሩ መንገድ ለመቀበል ተግተው ሠርተዋል። ሊዚ እንዲህ ብላለች፦ “በርካታ ሰዎች ሲመጡ ማየት በጣም የሚያበረታታ ነው። ጎብኚዎቹ አድናቆታቸውንና ቅርንጫፍ ቢሮውን ለመጎብኘት የከፈሉትን መሥዋዕት ሲገልጹ ስሰማ እምነቴ ይጠናከራል።”
ቤቴልን ለመጎብኘት የመጡትን በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለማስተናገድ፣ ቤቴል ውስጥ በሌላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም ያስጎበኛሉ። ይህ ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅባቸው ቢሆንም እንግዶቹን ማስጎብኘት ያስደስታቸዋል። ሁዋን እንዲህ ብሏል፦ “እንግዶችን ካስጎበኘሁ በኋላ በፊታቸው ላይ የሚነበበውን ደስታ ሳይ ያደረግኩት ጥረት በእርግጥም እንደማያስቆጭ ይሰማኛል።”
“ልጆቹ በጣም ይወዱታል”
ትንንሽ ልጆችም ቤቴልን መጎብኘት ያስደስታቸዋል። በኮምፒውተር ክፍል ውስጥ የምትሠራው ኖሪኮ እንዲህ ብላለች፦ “ለመጎብኘት የሚመጡትን ልጆች ወደፊት ቤቴል ገብተው ማገልገል ይፈልጉ እንደሆነ እጠይቃቸዋለሁ። ሁሉም ‘አዎ!’ ይላሉ።” ልጆቹ በጣም ከሚወዷቸው ቦታዎች አንዱ የካሌብ ምስል ያለበት ቦታ ነው። ልጆቹ እዚያ ሲደርሱ የይሖዋ ወዳጅ ሁን የተባለው ተከታታይ አኒሜሽን ቪዲዮ ገጸ ባሕርያት ከሆኑት ከካሌብና ከሶፊያ ቅርፅ ጋር ፎቶ መነሳት ይችላሉ። ኖሪኮ “ልጆቹ በጣም ይወዱታል” ብላለች።
በርካታ ልጆች በቤቴል ውስጥ ለሚሠራው ሥራ ያላቸውን አድናቆት ይገልጻሉ። ለምሳሌ፣ በሜክሲኮ የሚኖረው ሄንሪ የተባለ ትንሽ ልጅ ቤቴል ሲመጣ መዋጮ ለመስጠት በማሰብ ገንዘብ አጠራቅሞ ነበር። ከገንዘቡ ጋር አብሮ በሰጠው ማስታወሻ ላይ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እባካችሁ ይህን ገንዘብ ተጨማሪ ጽሑፎች ለማዘጋጀት ተጠቀሙበት፤ ይሖዋን ስለምታገለግሉ አመሰግናችኋለሁ።”
አንተም ተጋብዘሃል
የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎቻቸውንና የማተሚያ ቦታዎቻቸውን በነፃ ያስጎበኛሉ። አንተም ከእነዚህ ቢሮዎች አንዱን እንድትጎበኝ እንጋብዝሃለን። በጉብኝቱ እንደምትደሰት እርግጠኞች ነን። ጉብኝቱን አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ስለ እኛ > ቢሮዎች እና ጉብኝት በሚለው ሥር ተመልከት።