በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለረጅም ጊዜ በብሩክሊን ጎልቶ የታየ ምልክት

ለረጅም ጊዜ በብሩክሊን ጎልቶ የታየ ምልክት

በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ አናት ላይ የተሰቀለው በቀይ ፊደሎች የተጻፈ ምልክት ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት ሲታይ ቆይቷል፤ በርካታ የኒው ዮርክ ሲቲ ነዋሪዎች ሰዓት ወይም የአካባቢውን የሙቀት መጠን ለማወቅ ይህን ምልክት ይመለከታሉ።

በብሩክሊን በሚገኘው የአፓርታማ ቤቷ ላይ ሆና ይህን ምልክት መመልከት የምትችለው ኢቦኒ እንዲህ ብላለች፦ “ሥራ ከመሄዴ በፊት ሰዓቱንና የሙቀቱን መጠን በመስኮቴ ማየት መቻሌ ያስደስተኛል። ሰዓት እንዳይረፍድብኝና ለአየሩ ሁኔታ የሚስማማ አለባበስ እንዲኖረኝ ያስችለኛል።”

ሰዓትና የሙቀት መጠን የሚያሳውቀው ይህ ምልክት በቀጣዮቹ ዓመታትስ መታየቱን ይቀጥል ይሆን? ላይቀጥል ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮችን ዋና መሥሪያ ቤት በኒው ዮርክ ግዛት ሰሜናዊ ክፍል ወደሚገኝ ቦታ ለማዛወር እቅድ የተያዘ ከመሆኑ አንጻር ይህ ጉዳይ የተመካው ወደፊት የሕንፃው ባለቤት በሚሆኑት ሰዎች ላይ ነው።

ከ70 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የሕንፃው የቀድሞ ባለቤት በሕንፃው ላይ ምልክት እንዲሰቀል አድርጎ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በ1969 ሕንፃውን ከገዙ በኋላ ምልክቱ አሁን ያለውን ዓይነት መልክ እንዲኖረው አደረጉ።

ይህ ምልክት የዘወትር ክትትል ይጠይቃል። ባለፉት ዓመታት ሁሉ በዋናው መሥሪያ ቤት ይሠሩ የነበሩ የተለያዩ ወጣቶች በቀንም ሆነ በማታ ከምልክቱ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ የጥገና ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

በምሽት ፈረቃ ይሠራ የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ በማለት ቀደም ሲል የተፈጠረን አንድ ሁኔታ ተርኳል፦ “አንድ ምሽት የቴሌቪዥን ዜና ዳይሬክተር የሆነ አንድ ሰው ስልክ ደወለልን። የደወለው በምልክቱ ላይ ያለው ሰዓት በ15 ሴኮንዶች እንደተሳሳተ ለማሳወቅ ነበር። በዚያ ምሽት በሚቀርብ ፕሮግራም ላይ ሰዓቱ እንዲታይ ስለፈለገ ሰዓቱን እንድናስተካክለው ጠየቀን። ወዲያውኑ አንድ እንቅልፍ የተጫጫነው የጥገና ሠራተኛ ሰዓቱን ማስተካከል ጀመረ።”

ምልክቱ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆንና በትክክል እንዲሠራ ለማድረግ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል። እየተለዋወጡ ከሚበሩት ሰዓቱንና በፋራናይት የተገለጸውን የሙቀት መጠን ከሚያሳዩት ምልክቶች በተጨማሪ ሙቀቱን በሴንቲ ግሬድ የሚያሳይ ሌላ ምልክት በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ተጨምሯል።

በ2009 ደግሞ ምልክቱ እንዲበራ የሚያደርጉት የኒዮን አምፖሎች ይበልጥ ውጤታማ በሆኑ ላይት ኤሚቲንግ ዳዮድ (LED) በተባሉ ቀይ አምፖሎች ተተኩ፤ እነዚህ አምፖሎች ይበልጥ አስተማማኝ ከመሆናቸውም ሌላ ለጥገና በሚወጣው ዓመታዊ ወጪ ረገድ ከ4,000 ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ ይቆጥባሉ። በአሁኑ ጊዜ ያለው ምልክት የሚወስደው የኤሌክትሪክ ኃይል ቀደም ሲል ከነበረው በጣም ያነሰ ነው፤ ይህም ኃይል ቆጣቢ እንዲሆን አድርጎታል።