በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በአማዞን ደን ውስጥ ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገነባ

በአማዞን ደን ውስጥ ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገነባ

በአማዞን ደን መካከል አንድ የሚያምር የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገንብቷል። ማናውስ ከተባለችው የብራዚል ከተማ በስተ ሰሜን የሚገኘው 52 ሄክታር ስፋት ያለው ይህ መሬት በአብዛኛው አገር በቀል በሆኑ ዛፎች የተሸፈነ ነው። በቀለማት ያሸበረቁት ማኮው እና ቱካን የተባሉት ወፎች እንዲሁም ሌሎች የወፍ ዝርያዎች ኩፑዋሱ፣ ብራዚል ነት እና አንዤሊም ፔድራ በተባሉ ዛፎች አናት ላይ ሆነው ይንጫጫሉ። ታዲያ እንዲህ ባለ አካባቢ ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መገንባት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

የአማዞን ወንዝ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ከሚገባበት ቦታ 1,450 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በማናውስ ከተማ ውስጥ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ይኖራል። አዲስ የተገነባው አዳራሽ በማናውስ፣ በዙሪያዋ ባሉ ትናንሽ ከተሞች እንዲሁም በአማዞንና በገባር ወንዞቹ ዳርቻዎች ላይ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ ለሚኖሩ 7,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ አዳራሽ ሆኖ ያገለግላል። በዚህ አዳራሽ ከሚጠቀሙት ተሰብሳቢዎች መካከል በጣም ርቀው የሚገኙት ሳዎ ጋብርዬል ደ ካሽዌራ በተባለችው ከተማ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ ከተማዋ ከማናውስ በስተ ምዕራብ ከ800 ኪሎ ሜትር በሚበልጥ ርቀት ላይ ትገኛለች። አንዳንድ ተሰብሳቢዎች፣ በአዳራሹ ውስጥ በሚካሄድ የወረዳ ወይም የክልል ስብሰባ ላይ ለመገኘት ለሦስት ቀናት በጀልባ ይጓዛሉ!

በአማዞን ደን መካከል ትልቅ መሰብሰቢያ አዳራሽ መገንባት በጣም ከባድ ሥራ ነበር። የግንባታ ቁሳቁሶችን የያዙ 13 ኮንቴይነሮችን በሳኦ ፓውሎ ከሚገኘው የሳንቶስ ወደብ አንስቶ ግንባታው እስከሚካሄድበት ቦታ ድረስ ለማጓጓዝ የብራዚል የባሕር ዳርቻዎችን ማቋረጥና በአማዞን ወንዝ ላይ ሽቅብ መውጣት ይጠይቅ ነበር።

አዲሱ አዳራሽ በብራዚል ከተገነቡት ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾች 27ኛው ሲሆን እሁድ፣ ግንቦት 4, 2014 በተካሄደው የአዳራሹ የውሰና ፕሮግራም ላይ 1,956 ሰዎች ተገኝተዋል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ እንዲህ ባለ ትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሲገኙ የመጀመሪያቸው ስለነበር በጣም ተደስተው ነበር።

ተሰብሳቢዎቹ ተናጋሪውን መስማት ብቻ ሳይሆን ማየትም ችለዋል። ይህም አስደሳች ነገር ነበር፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል ስብሰባዎቹ ይካሄዱ የነበረው በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ሲሆን ብዙዎቹ ተሰብሳቢዎች ተናጋሪውን ይቅርና መድረኩን እንኳ ማየት አይችሉም ነበር። አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል፦ “ለበርካታ ዓመታት በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቻለሁ፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማዎችን መስማት እንጂ ማየት አልችልም ነበር።” አሁን ሁሉም ተሰብሳቢዎች መድረኩን ማየት ይችላሉ።