የዎርዊክ ፎቶ ጋለሪ 3 (ከጥር እስከ ሚያዝያ 2015)
ይህ የፎቶ ጋለሪ በአዲሱ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚከናወነው ሥራ ከጥር እስከ ሚያዝያ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ ምን ያህል እየገሰገሰ እንደሆነ ያሳያል።
ጥር 2, 2015—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ
የበላይ አካሉ የሕትመት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ሃሮልድ ኮርከርን “አቅማችሁን በሚገባ መጠቀም” የሚል ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግር ሰጠ። በዎርዊክ የሚሠሩትን ወንድሞች ለማበረታታት ጎብኚ ተናጋሪዎች ዘወትር ንግግር ይሰጧቸዋል።
ጥር 14, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ
ይህ ነጭ የፕላስቲክ መሸፈኛ ለሠራተኞቹ ከለላ የሚሆናቸው ከመሆኑም ሌላ በቅዝቃዜው ወቅት ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ ይረዳቸዋል። የመመገቢያ አዳራሹ፣ ክሊኒኩ፣ ኩሽናውና የልብስ እጥበቱ በዚህ ሕንፃ ላይ ይሆናሉ።
ጥር 16, 2015—መኖሪያ ሕንፃ መ
የኤሌክትሪክ ሠራተኞች ሽቦ ለመዘርጋት ሲያዘጋጁ። ከ12,000 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሽቦ በመኖሪያ ሕንፃዎቹ ግድግዳ ውስጥና ወለሉ ሥር ተቀብሯል። በዎርዊክ ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር የተያያዘ ሥራ የተጀመረው ቦታው ከተገዛ ብዙም ሳይቆይ ሲሆን ፕሮጀክቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሥራው ይቀጥላል።
ጥር 16, 2015—መኖሪያ ሕንፃ ሀ
አንድ ሠራተኛ፣ በረንዳው ውኃ እንዳያስገባ ለሚከናወነው ሥራ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ በፕላስተር ሲሸፍን። በላይኛው ፎቅ ላይ የሚገኙ በረንዳዎች ፖሊሜተል ሜታክራይሌት የተባለ ውኃ የማያስገባ ፈሳሽ ነገር ይቀባሉ።
ጥር 23, 2015—መኖሪያ ሕንፃ ሀ
በኤሌክትሪክ ሥራ ላይ የተሰማሩ አንድ አባትና ሴት ልጁ ወደ መኖሪያ ቤቶቹ ኃይል የሚያስተላልፉ መስመሮችን ሲዘረጉ።
የካቲት 6, 2015—የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ
ሠራተኞቹ በዚህ ጊዜያዊ ምግብ ቤት ምሳ ይበላሉ። በዚህ ቦታ በየዕለቱ ከ2,000 ሰው በላይ ይስተናገዳል።
የካቲት 12, 2015—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ
የጥገና ክፍሎቹን ምድር ቤት ወለል ለአርማታ ለማዘጋጀት ፌሮ ሲዘረጋ።
የካቲት 12, 2015—መኖሪያ ሕንፃ ሐ
ልጆች ለግንባታ ሠራተኞቹ አድናቆታቸውን ለመግለጽ የጻፏቸው ደብዳቤዎች። በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በዚህ ቦታ ለአጭር ጊዜ ይሠራሉ። በየሳምንቱ 500 ገደማ አዳዲስ ሠራተኞች ይመጣሉ። በየካቲት ወር በዎርዊክ ፕሮጀክት ላይ በየዕለቱ 2,500 የሚያህሉ ሠራተኞች ተካፍለዋል።
የካቲት 24, 2015—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ
በአሁኑ ወቅት ከፕሮጀክቱ 60 በመቶ የሚያህለው ተጠናቋል። ከጥር እስከ ሚያዝያ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ በመኖሪያ ሕንፃዎቹ ላይ፣ ከመሠረት በላይ ያለው የሕንፃው ክፍል ተጠናቋል፤ በቢሮዎች እና በአገልግሎት መስጫ ሕንፃው ላይ ደግሞ በብረት የተሠራው ቋሚና ማገር ሥራ አልቋል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ ሠራተኞቹ የጥገናውን ሕንፃ የሲሚንቶ ግድግዳ ማቆም፣ የመኖሪያ ሕንፃዎቹን የሚያገናኙ መተላለፊያዎችን መሥራት እንዲሁም በስተርሊንግ ፎረስት ሌክ (ብሉ ሌክ) ላይ የሚገኘውን ግድብ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል።
የካቲት 25, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ
የደረጃዎቹ ቦታ ከታች ወደ ላይ ሲታይ። የዚህን ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ ደረጃዎች ፍሬም የሠሩት ሕንፃ ተቋራጮች ሲሆኑ አርማታውን የሞሉት ደግሞ ፈቃደኛ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።
የካቲት 26, 2015—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ
በአንድ ቀዝቃዛ ቀን ሠራተኞቹ የመጀመሪያውን ፎቅ ለአርማታ ለማዘጋጀት ፌሮ ሲዘረጉ። በዎርዊክ ከጥር እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ውስጥ 127 ሴንቲ ሜትር የሚያህል በረዶ ጥሏል። በረዶውን የሚጠርጉት ቡድኖች ቦታውን ሁልጊዜ ያጸዳሉ፤ ሠራተኞቹ ደግሞ ሰውነታቸውን ለማሞቅ፣ ሙቀት የሚሰጡ ክፍሎች ውስጥ ይገባሉ።
መጋቢት 12, 2015—የጎብኚዎች የመኪና ማቆሚያ
አስቀድሞ የተዘጋጀው የጣሪያው መዋቅር ላይ ቆርቆሮ ሲያለብሱ። እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በአሞራ ክንፍ ቅርጽ የተሠሩት አብዛኞቹ የመኖሪያ ሕንፃዎች ጣሪያዎች ይጠናቀቃሉ። የመጨረሻዎቹ ጣሪያዎች ሥራ የሚከናወነው በመኖሪያ ሕንፃ ለ ላይ ሲሆን ይህም በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ያልቃል።
መጋቢት 18, 2015—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ
መኖሪያ ሕንፃ ለ፣ ከረጅም የከባድ ዕቃ ማንሻ መሣሪያ (ክሬን) ላይ ሲታይ።
መጋቢት 18, 2015—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ
የቧንቧ ሠራተኞች በነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ ጋራዥ ውስጥ ሆነው ፕላኑን ሲመለከቱ። አጠቃላይ ፕሮጀክቱን ለማከናወን ከ3,400 በላይ የጸደቁ የግንባታ ፕላኖች አስፈልገዋል።
መጋቢት 23, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ
ሠራተኞች፣ ማንሻ መሣሪያ ላይ ሆነው ሕንፃውን በፕላስቲክ ሲሸፍኑት። ሠራተኞቹ፣ ማንሻ መሣሪያዎችንና ሌሎች መገልገያዎችን ለአደጋ በማያጋልጥ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ብዙ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። ሥልጠናዎቹ የማንሻ መሣሪያዎች አጠቃቀምን፣ ሠራተኞች እንዳይወድቁ የሚደረግ ጥንቃቄን፣ አጠቃላይ የደህንነት ግንዛቤን፣ የአፍንጫና የአፍ መሸፈኛ አጠቃቀምን እንዲሁም ትላልቅ ነገሮችን ከቦታ ቦታ ከማንቀሳቀስና ክሬኑን ለሚያንቀሳቅሰው ሰው ምልክት ከመስጠት ጋር የተያያዙ ትምህርቶችን ያጠቃልላሉ።
መጋቢት 30, 2015—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ
በስተ ምዕራብ ያሉት የመኖሪያ ሕንፃዎች። ይህ ፎቶግራፍ እንደሚያሳየው እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ከመኖሪያ ሕንፃዎች ሀ፣ ለ እና መ የሜካኒካል እና የኤሌክትሪካል ሥራዎች ጋር በተያያዘ ሰፊ ሥራ ተከናውኗል። በመኖሪያ ሕንፃ ሐ (ፎቶው ላይ አይታይም) ደግሞ የጂፕሰም፣ የወለል ንጣፍና የቀለም ሥራ ተጀምሯል።
ሚያዝያ 15, 2015—መኖሪያ ሕንፃ ለ
ሁለት ሠራተኞች ማንሻ መሣሪያ ላይ ሆነው የውጭው ግድግዳ እርጥበት እንዳያሰርግ መከላከያ ሲቀቡ። በእያንዳንዱ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ይህን መከላከያ ለመቀባት ሁለት ወር ገደማ ይወስዳል።
ሚያዝያ 27, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ
ግንበኞች የድንጋይ ግንብ ሲሠሩ። ዕቃ የሚራገፈው እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ ክፍሎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በዚህ ቦታ ላይ ነው።
ሚያዝያ 30, 2015—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ
ለዚህ ሥራ የተቀጠረ አንድ ዋናተኛ በብሉ ሌክ፣ አሮጌውን ቫልቭ በአዲስ ሲቀይር። ይህ መደረጉ፣ ኃይለኛ ውሽንፍር ቢነሳ የውኃ መጥለቅለቅ እንዳይፈጠር ለመከላከል አንዲት ቁልፍ ብቻ በመጫን የሐይቁን መጠን ለመቀነስ ያስችላል።