በስጦታ የቀረቡ 19,000 የበረራ ቲኬቶች
በሐምሌ 2013 ሚስዮናውያንና በሌላ አገር በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ያሉ ክርስቲያኖች ከይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የተላከ አስደሳች ደብዳቤ ደረሳቸው። ይህ ደብዳቤ በውጭ አገር እያገለገሉ ያሉ ክርስቲያኖች በ2014 እንዲሁም በ2015 መጀመሪያ አካባቢ በሚደረጉ የክልልና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲችሉ ዝግጅት መደረጉን የሚገልጽ ነበር።
የዚህ ዝግጅት ዓላማ በውጭ አገር እያገለገሉ ያሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንዲካፈሉ ለመርዳት ብቻ ሳይሆን ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር ጊዜ የሚያሳልፉበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ለማድረግም ነው። ደብዳቤው የደርሶ መልስ ቲኬቱን የሚገዛላቸው ድርጅቱ እንደሆነ ይገልጻል።
ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ዝግጅቶች ተደርገው የነበረ ቢሆንም የዘንድሮው ለየት ያለ ነው። ቲኬቶቹን የሚገዛው በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የትምህርት ኮሚቴ ሥር የተቋቋመው አዲስ ዲፓርትመንት ይኸውም የዋናው መሥሪያ ቤት የጉዞ ክፍል ነው።
ግብዣውን የሚያሳውቀው ደብዳቤ ከተላከ ብዙም ሳይቆይ የበረራ ቲኬቶች እንዲገዙ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ቀስ በቀስ መምጣት ጀመሩ። በጥር 2014 ግን እነዚህ ጥያቄዎች በብዛት ይጎርፉ ጀመር። በመሆኑም ከዚህ ጉዞ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እንዲሠሩ የተመደቡት ወንድሞች የቲኬት ዋጋዎችን በማጥናት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚጠቀሙባቸውን ቲኬቶች ገዙ።
አንዳንዶቹ የጉዞ መስመሮች አስቸጋሪ ነበሩ። በአይስላንድ ከምትገኘው ከሬይሃቪክ የሚነሱ ተጓዦች ቦሊቪያ ወደሚገኘው ኮቻባምባ መሄድ ነበረባቸው። በኒው ካሌዶንያ ከምትገኘው ከኑሜያ የሚነሱ ተጓዦች ወደ አንታናናሪቮ፣ ማዳጋስካር መብረር ነበረባቸው። አንዳንዶች ከፖርት ሞርዝቢ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ተነስተው ወደ ሲያትል፣ ዋሽንግተን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሌሎች ደግሞ ከኦጋዱጉ፣ ቡርኪና ፋሶ ወደ ዊኒፔግ፣ ካናዳ በረዋል።
በዋናው መሥሪያ ቤት የጉዞ ክፍል ውስጥ የሚያገለግሉት አምስት ወንድሞችና እህቶች 19,000 ገደማ የበረራ ቲኬቶችን መግዛት ነበረባቸው። ጉባኤዎች ለዚህ ዓላማ ያዋጡትን ገንዘብ በመጠቀም የገዟቸውን ቲኬቶች በ176 አገሮች ለሚገኙ 4,300 ተጓዦች ልከዋል።
ብዙዎች ለዚህ ዝግጅት ያላቸውን አመስጋኝነት ገልጸዋል። አንድ ሚስዮናዊ ባልና ሚስት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በደቡብ ምሥራቅ እስያ ወደሚገኘው ምድባችን ዛሬ እንመለሳለን። ከአምስት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትውልድ አገራችን ወደ እንግሊዝ ተመልሰን ከቤተሰቦቻችን ጋር እንድንገናኝ ስለረዳችሁን ከልብ እናመሰግናለን። ይህ ዝግጅት ባይኖር ኖሮ በራሳችን ይህን ለማድረግ አቅማችን አይፈቅድም ነበር። ዝግጅቱ የተሳካ እንዲሆን ላደረጋችሁ ሁሉ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ።”
በፓራጓይ እያገለገለ ያለ አንድ ሚስዮናዊ ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እኔና ባለቤቴ በኒው ጀርሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የመካፈል አጋጣሚ በማግኘታችን በጣም አመስጋኞች ነን። በ2011 መጀመሪያ አካባቢ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን ዋና መሥሪያ ቤት ለመጎብኘት ዕቅድ አወጣን። ለዚህ ስንል ደግሞ ገንዘብ አጠራቅመን ነበር። ይሁንና በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ፓራጓይ የሚገኙ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችን እንድንጎበኝ ጥያቄ ቀረበልን። ይህ ደግሞ ብዙ መጓዝ የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም በጉዳዩ ላይ በደንብ ካሰብንበት በኋላ በአዲሱ ምድባችን ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን እንደሚረዳን ስለተሰማን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መሄዳችንን ትተን መኪና ለመግዛት ወሰንን። በኋላ ግን ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ መጋበዛችንን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን። ስለዚህ ሕልማችን እውን ሆነ! ይሖዋ በዚህ መንገድ ጥሩነቱንና ደግነቱን ስላሳየን በጣም አመስጋኞች ነን።”
“ያለንን ልባዊ አመስጋኝነት ለመግለጽ ይህቺን አጭር ደብዳቤ ለመላክ ወሰንን” በማለት በማላዊ የሚያገለግሉ አንድ ባልና ሚስት ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ይህን ሁሉ የበረራ ቲኬት መግዛት ምን ያህል አድካሚ እንደሆነና ብዙ ጊዜና ወጪ እንደሚጠይቅ መገመት አያዳግትም። ልፋታችሁን ከልብ እናደንቃለን፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ወደ ትውልድ አገራችን ሄደን ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ እንዲሁም ከቤተሰባችንና ከወዳጆቻችን ጋር ጊዜ እንድናሳልፍ በማድረግ ላሳየን ደግነት የይሖዋን ድርጅት ማመስገን እንፈልጋለን።”
በዋናው መሥሪያ ቤት የጉዞ ክፍል ውስጥ የሚያገለግሉትም ቢሆኑ ሥራቸውን ወደውታል። ሚላቪ “ሚስዮናውያኑ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ቤተሰባቸውንና ወዳጆቻቸውን እንዲጠይቁ መርዳት አስደሳች ነው” ብላለች። ዶሪስም “ድርጅቱ በውጭ አገር ተመድበው ለሚሠሩ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ያለውን ጥልቅ ፍቅር እንድገነዘብ አስችሎኛል” በማለት አክላ ተናግራለች። የዲፓርትመንቱ የበላይ ተመልካች የሆነው ሮድኒ ደግሞ “በዚህ ሥራ መካፈል በመቻሌ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በትጋት ለሚሠሩትና የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ለሚያደርጉት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ሲባል በተደረገው በዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው።