በታጋሎግ ቋንቋ በሮም የተደረገ የክልል ስብሰባ—“ትልቅ የቤተሰብ ቅልቅል!”
የታጋሎግ ሕዝብ ከሚኖርባት ከፊሊፒንስ 10,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በጣሊያን አገር በሮም ከተማ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የታጋሎግ ቋንቋ ተናጋሪ የይሖዋ ምሥክሮች ከሐምሌ 24-26, 2015 ልዩ የክልል ስብሰባ አድርገው ነበር።
በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ከ850,000 በላይ የፊሊፒንስ ተወላጆች እንደሚኖሩ ይገመታል። በመሆኑም በአውሮፓ በታጋሎግ ቋንቋ የሚካሄዱ 60 ጉባኤዎችና ትናንሽ ቡድኖች አሉ፤ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው ለሚገኙ የፊሊፒንስ ተወላጆች ይሰብካሉ።
ይሁንና እነዚህ ጉባኤዎችና ቡድኖች በሮም በተደረገው በዚህ የክልል ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ መሰብሰብ ችለው ነበር፤ ይህ የሦስት ቀን ስብሰባ የተካሄደው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ነበር። በዚያ የተገኙት 3,239 ተሰብሳቢዎች፣ ቀደም ሲል በፊሊፒንስ ያገለግል የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን የሦስቱንም ቀን የመደምደሚያ ንግግር በመስጠቱ እጅግ ተደስተዋል።
‘ልቤን በጥልቅ ነክቶታል’
አንድ ሰው ስብሰባውን የተካፈለው በአፍ መፍቻ ቋንቋው ይሁን በሁለተኛ ቋንቋው ለውጥ ያመጣል? ኢቫ የተባለች አንዲት ነጠላ እናት “እንግሊዝኛ የምረዳው በጣም ትንሽ ነው፤ ስብሰባው በታጋሎግ ቋንቋ መካሄዱ ግን የቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ልቤ በጥልቅ እንዲነካ አድርጓል” ብላለች። እሷና ሁለት ልጆቿ ከሚኖሩበት ከስፔን ወደ ጣሊያን ለሚያደርጉት ጉዞ የሚሆናቸውን ገንዘብ ለማጠራቀም ሲሉ ቀደም ሲል እንደሚያደርጉት በየሳምንቱ ሬስቶራንት ሄደው ከመመገብ ይልቅ በወር አንዴ ብቻ ይህን ለማድረግ ወሰኑ። ኢቫ እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት በመክፈላችን ተክሰናል፤ ምክንያቱም በዚህ ስብሰባ ላይ የቀረበውን ትምህርት ሙሉ በሙሉ መረዳት ችያለሁ!”
በጀርመን የምትኖረው ያስሚን በዚህ ስብሰባ ላይ ለመካፈል የሥራ ፈቃድ ጠየቀች። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ሆኖም የምሄድበት ጊዜ ሲደርስ፣ መሠራት ያለበት ነገር ስላለ እረፍት መውጣት እንደማልችል ተነገረኝ። ተረጋግቼ ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ አለቃዬን አነጋገርኩት። በስብሰባው ላይ መገኘት እንድችል ሥራውን ማከናወን የሚቻልባቸውን አንዳንድ ዕቅዶች አወጣን! በመላው አውሮፓ ከሚገኙ የፊሊፒንስ ተወላጅ ከሆኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር መገናኘት መቻል በጣም የሚያስደስት ነገር ነው።”
እርግጥ ነው፣ በአውሮፓ የሚኖሩ በርካታ የፊሊፒንስ ተወላጆች አገራቸውን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በስደት የሚኖሩ ጓደኞቻቸውንም ይናፍቃሉ። ይህ ስብሰባ አሁን መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ከሆኑት የቀድሞ ጓደኞቻቸው ጋር እንደ አዲስ ለመተዋወቅ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። (ማቴዎስ 12:48-50) ፋብሪስ “ከዚህ ቀደም የማውቃቸውን ሰዎች ማግኘቴ በጣም አስደስቶኛል!” በማለት ተናግሯል። ስብሰባው ካበቃ በኋላ አንዲት እህት “ይህ ትልቅ የቤተሰብ ቅልቅል ነው!” እያለች ደጋግማ ትናገር ነበር።