በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የበላይ አካሉ በሩሲያና በዩክሬን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን አበረታታ

የበላይ አካሉ በሩሲያና በዩክሬን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን አበረታታ

“ልገልጸው ከምችለው በላይ ለእኛ ከፍተኛ ፍቅር እንዳላቸው ተሰምቶናል!” ይህን የተናገረችው፣ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት ያነበበውን የሚያበረታታ ደብዳቤ ያዳመጠች በዩክሬን የምትገኝ ሴት ናት። ይህች ሴት፣ ወንድም ሌት ግንቦት 10 እና 11, 2014 ዩክሬንን በጎበኘበት ወቅት የሰጠውን ንግግር ካዳመጡት 165,000 የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዷ ናት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችና ከላይ የተጠቀሰው ደብዳቤ በአምስት ቋንቋዎች ተተርጉመው የነበረ ከመሆኑም ሌላ በመላው ዩክሬን በሚገኙ 1,100 የመንግሥት አዳራሾች ለተሰበሰቡ ሰዎች ተላልፏል።

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰንም በዚሁ ጊዜ በመላው ሩሲያ ለሚገኙ ወንድሞቻችን በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ደብዳቤውን አነበበ። ፕሮግራሙ በ14 ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በቤላሩስና በሩሲያ በሚገኙት ከ2,500 በላይ የሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ ለተሰበሰቡ 180,413 ወንድሞችና እህቶች ተላልፏል።

ከበላይ አካሉ የተላከው ደብዳቤ በሩሲያና በዩክሬን ለሚገኙ ጉባኤዎች በሙሉ የተጻፈ ነበር። ወንድም ሳንደርሰን ደብዳቤውን በሩሲያኛ ያነበበው ሲሆን የሩሲያ ቅርንጫፍ ቢሮም እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “የበላይ አካሉ በዚህ አካባቢ ላለው ሁኔታ ትኩረት በመስጠቱ ወንድሞችና እህቶች ልባቸው በጥልቅ ተነክቷል። ሁላችንም የበላይ አካሉ እቅፍ ያደረገን ያህል ነው የተሰማን።”

ደብዳቤው የተዘጋጀው የፖለቲካ አለመረጋጋት ባለባቸው አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማጽናናትና ለማበረታታት ታስቦ ነው። ወንድሞች ከዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆን ‘የዓለም ክፍል አለመሆናቸውን’ ማሳየታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስቧቸዋል።​—ዮሐንስ 17:16

ወንድሞች በጸሎት፣ በጥናትና በአምላክ ቃል ላይ በማሰላሰል ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ጠብቀው እንዲኖሩ የበላይ አካሉ አበረታቷቸዋል። ተሰብሳቢዎቹ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማቸውም እንኳ አምላክ በኢሳይያስ 54:17 ላይ “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል” በማለት በገባው ቃል መተማመን እንደሚችሉ ተገልጾላቸዋል።

የበላይ አካሉ ደብዳቤውን የደመደመው እንዲህ በማለት ነው፦ “ሁላችሁንም በጣም እንወዳችኋለን። ዘወትር እንደምናስባችሁና ስለ እናንተ ይሖዋን እንደምንማጸን እርግጠኞች ሁኑ።”

በዩክሬን ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ፣ የበላይ አካሉ ያደረገላቸውን ጉብኝት አስመልክቶ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ወንድሞች የበላይ አካሉ ፍቅራዊ አሳቢነት ስላሳያቸውና ትኩረት ስለሰጣቸው ተደስተዋል። ወንድም ሌት እና ወንድም ሳንደርሰን በተመሳሳይ ጊዜ በዩክሬንና በሩሲያ ያደረጉት ጉብኝት የአምላክ ሕዝቦች አንድነት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ ወንድሞች ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ምን ያህል እንደሚያስቡላቸው እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። ሁላችንም ይህ ጉብኝት የተደረገልን በትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ ተሰምቶናል፤ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመንም እንኳ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል አበረታቶናል።”