የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ137ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት
መስከረም 13 ቀን 2014 በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትምህርት ማዕከል ውስጥ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ137ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ ነበር። ይህ ትምህርት ቤት ቀደም ሲል ብዙ ተሞክሮ የነበራቸው የይሖዋ ምሥክሮች የተመደቡበትን ጉባኤ ወይም ቅርንጫፍ ቢሮ በማጠናከር ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ሥልጠና ይሰጣል። በፓተርሰን ተገኝተው ፕሮግራሙን የተከታተሉት እና በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በጃማይካ እና በፖርቶ ሪኮ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በቪዲዮ በቀጥታ የተመለከቱት አድማጮች አጠቃላይ ብዛት 12,333 ነበር።
የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው የበላይ አካል አባል የሆነው ሳሙኤል ኸርድ ነው። በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የይሖዋ ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ገለጸ። (ኢሳይያስ 55:8, 9) የጊልያድ ተማሪዎች ለአምስት ወራት ስለ አምላክ አስተሳሰብ ሲማሩ የቆዩ ቢሆንም ስለ አምላክ ያወቁት ነገር “የመንገዱ ዳር ዳር” ብቻ እንደሆነ ተናገረ። (ኢዮብ 26:14) በተጨማሪም የአምላክን አስተሳሰብ ለመማር በተሰበሰብን ቁጥር ጥቅም እንደምናገኝ ሁሉ ይህ የምረቃ ሥነ ሥርዓትም በዚህ ረገድ እንደሚጠቅመን ገለጸ።
‘የመንፈስ ፍሬ ትዕግሥት ነው።’ (ገላትያ 5:22) የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ጆን ላርሰን የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆነውን ትዕግሥትን ማሳየት የምንችልባቸውን ሁለት መንገዶች አጎላ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ በእምነት ጸንተን መቆም እንድንችል ሲያሠለጥነን እንዲሁም ሲረዳን ልንታገሠው ይገባል። (1 ጴጥሮስ 5:10) አብርሃም በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል፤ ይሖዋ ሲያሠለጥነው በመታገሡ በመጨረሻ ይሖዋ የገባለትን ተስፋ ፍጻሜ አግኝቷል።—ዕብራውያን 6:15
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ራሳችንን መታገሥ ይኖርብናል። ተማሪዎቹ በጊልያድ የሚሰጠውን ሥልጠና ካገኙ በኋላ ከራሳቸው ብዙ ሊጠብቁ ይችላሉ። ወደየምድባቸው ከሄዱ በኋላ አንዳንድ ነገሮች ወዲያውኑ እነሱ እንዳሰቡት ሳይሆኑ ቢቀሩ የሆነ ችግር እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይችላል። ወንድም ላርሰን፣ ተማሪዎቹ ራሳቸውን የሚታገሡ እንዲሁም አምላክ ሥልጠና ሲሰጣቸው በትጋት መሥራታቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት እንደሚችሉ የራሱን ተሞክሮ በመጥቀስ አረጋገጠላቸው።—ዕብራውያን 6:11, 12
“ልባችሁ ትሑት ከሆነ ለዘላለም ይኖራል!” የበላይ አካል አባል የሆነው አንቶኒ ሞሪስ በመዝሙር 22:26 ላይ የተመሠረተ ንግግር አቀረበ፤ የጥቅሱ የመጨረሻ ክፍል ቃል በቃል ሲተረጎም “ልባችሁ ለዘላለም ይኑር” ማለት ነው። ይህን በረከት ለማግኘት ትሑት መሆን አለብን። ወንድሞ ሞሪስ፣ ይሖዋ እንዲጠቀምብን ከፈለግን ትሑት መሆን እንዳለብን ጎላ አድርጎ ገለጸ። ማንኛችንም ብንሆን ሌላው ቀርቶ በእውነት ቤት ለረጅም ጊዜ የቆየን ክርስቲያኖችም እንኳ ክርስቶስ ኢየሱስን መምሰል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ልንዘነጋ እንችላለን።—2 ጴጥሮስ 1:9
በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ትሑት ስለነበሩና ትሑት ስላልነበሩ ሰዎች የሚገልጽ ታሪክ እናገኛለን። ሄሮድስ አግሪጳ ሰዎች ለአምላክ ብቻ ሊሰጥ ይገባ የነበረውን ክብር ሲሰጡት በእብሪተኝነት ውዳሴውን በመቀበሉ የይሖዋ መልአክ ቀሰፈው፤ “በትል ተበልቶም ሞተ።” (የሐዋርያት ሥራ 12:21-23) ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ “የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ” እንደማያስብ በመግለጽ ጴጥሮስን በገሠጸው ጊዜ ጴጥሮስ እንዳላኮረፈ ወይም እንዳልተቆጣ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (ማቴዎስ 16:21-23) ተግሣጹን በመቀበል በትሕትና ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል።—1 ጴጥሮስ 5:5
ከተማሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ እንዲያገለግሉ ይመደባሉ፤ በመሆኑም ወንድም ሞሪስ፣ ተማሪዎቹ ትሑቶች ካልሆኑ በዚህ የሥራ ምድብ ደስታቸውን እንደሚያጡ ማሳሰቢያ ሰጠ። ይሁንና አንድ ሰው ትሕትና እንደሚጎድለው ላይገነዘብ ይችላል። ወንድም ሞሪስ ነጥቡን ለማጉላት ከበርካታ ዓመታት በፊት የተፈጠረን ሁኔታ እንደ ምሳሌ አድርጎ ጠቀሰ፤ አንድ ሽማግሌ ትሕትና እንደሚጎድለው ምክር በተሰጠው ጊዜ ለቅርንጫፍ ቢሮው “እስከማውቀው ድረስ እንደ እኔ ያለ ትሑት ሰው የለም” ብሎ ጽፎ ነበር። ወንድም ሞሪስ፣ ተማሪዎቹ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደማይገባ አሳሰበ። ስላላቸው የኃላፊነት ቦታ የተጋነነ አመለካከት እንዳይኖራቸው የሚጠነቀቁ እንዲሁም ዋነኞቹ ባለሥልጣናት ይሖዋ አምላክና ክርስቶስ ኢየሱስ እንደሆኑ የሚገነዘቡ ከሆነ ትሑት ሆነው መቀጠል ይችላሉ።
“አምላክ መንፈሱን ቆጥቦ አይሰጥም።” (ዮሐንስ 3:34) የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ማይክል በርኔት፣ ተማሪዎቹ በአገልግሎት ምድባቸው የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ወይም ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ነገሮች እንዲቋቋሙ መንፈስ ቅዱስ እንደሚረዳቸው ገለጸ። ባስልኤል የማደሪያ ድንኳኑን እንዲሠራ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት የቻለው በአምላክ መንፈስ እርዳታ ነው። (ዘፀአት 35:30-35) መንፈስ ቅዱስ፣ ባስልኤል ያለውን የሥነ ጥበብ ችሎታ ያሳደገለት ከመሆኑም ሌላ ሌሎችን ማሠልጠን እንዲችል ረድቶታል። የጊልያድ ተመራቂዎችም ክፍል ውስጥ የተማሩትን ከቅዱሳን ጽሑፎች የማስተማር ዘዴ ተግባራዊ ሲያደርጉ መንፈስ ቅዱስ በተመሳሳይ መንገድ ይረዳቸዋል።
በባስልኤል ዘመን እስራኤላውያን ሴቶችም የማደሪያ ድንኳኑን በመገንባቱ ሥራ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። (ዘፀአት 35:25, 26) በተመሳሳይም በጊልያድ የተማሩት እህቶች ባሎቻቸውን በመደገፍ “ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሴቶች” መሆናቸውን አሳይተዋል። ወንድም በርኔት ለተማሪዎቹ የሚከተለውን ምክር በመስጠት ንግግሩን ደመደመ፦ “ተሰጥኦዋችሁን የምትጠቀሙበት በትሕትና እና በታዛዥነት መንፈስ ሊሆን ይገባል። እንዲህ ካደረጋችሁ ይሖዋ መንፈሱን በተሟላ ሁኔታ ይሰጣችኋል።”
“ከእኔ ጋር ልትጨፍር ትችላለህ?” የትምህርት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ማርክ ኑሜር ንግግሩን ያቀረበው ንጉሥ ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ሲያመጣ ያደረገውን ነገር እንደ ምሳሌ በመጠቀም ነው። (2 ሳሙኤል 6:12-14) ታቦቱ በመጣበት ወቅት ዳዊት በትሕትና ‘ከአገልጋዮቹ ሴት ባሪያዎች’ ጋር በደስታ ይጨፍር ነበር። (2 ሳሙኤል 6:20-22) እነዚያ ሴት ባሪያዎች ንጉሥ ዳዊት ከእነሱ ጋር የጨፈረበትን ጊዜ ፈጽሞ እንደማይረሱት የታወቀ ነው። ወንድም ኑሜር በመቀጠል ተማሪዎቹ ‘ከሴት ባሪያዎች ጋር እንዲጨፍሩ’ አበረታታ። ለተማሪዎቹ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው፦ “በጉባኤ ውስጥ ምንም ኃላፊነት የሌላቸውን ወንድሞች በመርዳት ትታወቁ ይሆን? . . . ለሌሎች ከፍ ያለ ግምት እንድትሰጡ የሚያነሳሳችሁ ያሏቸው መንፈሳዊ ባሕርያት ናቸው?”
ተመራቂዎቹ በዚህ መንገድ ታማኝ ፍቅር ማሳየታቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ይሖዋን መምሰል ይችላሉ። (መዝሙር 113:6, 7) በአካባቢያቸው ያሉ አንዳንድ ሰዎች ትሕትና ሳያሳዩ ቢቀሩም እንኳ የሌሎች አለፍጽምና ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው ሊፈቅዱ አይገባም። ወንድም ኑሜር “ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ አትመልከቱ” በማለት ተናገረ፤ አክሎም “የይሖዋን በጎች እሱ በሚይዝበት መንገድ ለመያዝ ጥረት አድርጉ” የሚል ምክር ሰጠ።
“በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መመሥከር።” ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን የሚከታተለው ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ዊልያም ሳሙኤልሰን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን ይሰብክ እንደነበር ጠቀሰ። (የሐዋርያት ሥራ 17:17) ከዚያም ተማሪዎቹ በጊልያድ በነበሩበት ወቅት በአገልግሎት ያጋጠሟቸውን አንዳንድ ተሞክሮዎች በሠርቶ ማሳያ ሲያቀርቡ እንዲመለከቱ አድማጮችን ጋበዘ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ባልና ሚስት በገበያ ቦታ ከአንዲት ሻጭ ጋር ተገናኝተው ነበር። ገበያው ጋብ እስከሚልበት ጊዜ ድረስ ከጠበቁ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የሚል ርዕስ ያለውን ቪዲዮ አሳዩአት። በተጨማሪም የትውልድ ቋንቋዋ በሆነው በሌኦሽኛ የተዘጋጁ መረጃዎችን ለማግኘት jw.org የተባለውን ድረ ገጽ እንድትመለከት ጋበዟት። ከዚያ በኋላ ባልና ሚስቱ ለዚህች ሴት ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግና ፍላጎቷን ይበልጥ ማሳደግ ችለዋል።
“ለመንግሥቱ አገልግሎት ራሳችሁን በፈቃደኝነት ማቅረባችሁን ቀጥሉ።” በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ የሚያገለግለው ዊልያም ኖንኪስ ለአራት የጊልያድ ተመራቂዎች ቃለ መጠይቅ አደረገ። እነዚህ ተመራቂዎች መጀመሪያም ቢሆን ኢሳይያስ 6:8 ላይ የተገለጸውን ዓይነት መንፈስ በማንጸባረቅ ራሳቸውን ለመንግሥቱ አገልግሎት በፈቃደኝነት አቅርበዋል፤ ሆኖም ትምህርት ቤቱ ይህን መንፈስ ይበልጥ እንዲያንጸባርቁ ረድቷቸዋል። እህት ስኖልያ ማሴኮ የጊልያድ ሥልጠና ማሻሻያ ልታደርግባቸው የሚገቡ መስኮችን እንደጠቆማት ገልጻለች፤ በተለይ ደግሞ ሙሉ ቀን ስትሠራ ከዋለች በኋላ ጊዜዋን እንዴት በጥበብ መጠቀም እንደምትችል ትምህርት እንዳገኘች ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ሥልጠናው ቀደም ሲል አስብ ከነበረው የበለጠ ማከናወን እንደምችል አስገንዝቦኛል።” ወንድም ዴኒስ ኒልሰን፣ በጊልያድ ያገኘው ሥልጠና በሶፎንያስ 3:17 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በአገልግሎት ተስፋ እንዳይቆርጥ እንዴት ሊረዳው እንደሚችል አስገንዝቦታል። ወንድም ኒልሰን እንዲህ ብሏል፦ “በአገልግሎት አስደሳች ውጤት ባላገኝም . . . ይሖዋ ይደሰታል፤ እኔም እንዲሁ ሊሰማኝ ይገባል።”
“የሰማይ ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ።” (ማቴዎስ 6:26) የበላይ አካል አባል የሆነው ስቲቨን ሌት የፕሮግራሙን ዋነኛ ንግግር አቀረበ። ኢየሱስ የሰማይን ወፎች ‘ልብ ብለን እንድንመለከት’ ወይም እንድናጤን የሰጠንን ማበረታቻ መሠረት በማድረግ ወንድም ሌት ከእነዚህ ወፎች የምንማረው ብዙ ትምህርት እንዳለ ገለጸ።—ኢዮብ 12:7
ለምሳሌ ይሖዋ ወፎችን እንደሚመግባቸው ሁሉ ለእኛም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያሟላልናል። ‘የአምላክ ቤተሰብ’ አባላት እንደመሆናችን መጠን አምላክ ‘የራሱ ለሆኑት ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያቀርብ’ አረጋግጦልናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:15፤ 5:8) እርግጥ ነው፣ እኛም የራሳችንን ድርሻ መወጣት አለብን። ወፎች አምላክ የሚሰጣቸውን ምግብ ፍለጋ መሰማራት እንደሚኖርባቸው ሁሉ እኛም የእሱን በረከት ለማግኘት ‘አስቀድመን መንግሥቱን መፈለጋችንን መቀጠል’ አለብን።—ማቴዎስ 6:33
በተጨማሪም ወንድም ሌት ብዙ ወፎች አደጋ እየመጣባቸው እንደሆነ ሲሰማቸው የማስጠንቀቂያ ድምፅ እንደሚያሰሙ ገለጸ። እኛም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ለምሳሌ፣ አንድ ወንድም “ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል” ማሳሰቢያ ልንሰጠው ይገባል። (ገላትያ 6:1) እንዲሁም በስብከቱ ሥራችን አማካኝነት በፍጥነት እየቀረበ ስላለው “የይሖዋ ቀን” ለሰዎች ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን። (ሶፎንያስ 1:14) ከዚህም ሌላ ወንድም ሌት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚፈልሱ ወፎች ከፍ ባሉ ተራሮች አናት ላይ እንደሚበርሩ ሁሉ እኛም ልንወጣቸው የማንችል የሚመስሉንን እንቅፋቶች በይሖዋ እርዳታ ማሸነፍ እንደምንችል ተናገረ።—ማቴዎስ 17:20
መደምደሚያ። ተማሪዎቹ ዲፕሎማቸውን ከተቀበሉ በኋላ ከተመራቂዎቹ መካከል አንዱ የተማሪዎቹን የምስጋና ደብዳቤ አነበበ። ወንድም ኸርድ በፕሮግራሙ መደምደሚያ በሰጠው ሐሳብ ላይ የይሖዋ አስተሳሰብ በልባችን እንዲሰርጽ የምናደርግበትን ሂደት የባቡር ሃዲዶችን በትልቅ ሚስማር ከማያያዝ ሥራ ጋር አመሳስሎታል። ሚስማሩ በደንብ እንዲተከል ደጋግሞ መምታት ያስፈልጋል። በተመሳሳይም ተመራቂዎቹ በጊልያድ የተማሯቸውን ነገሮች ማሰባቸውን መቀጠል አለባቸው። ወንድም ኸርድ “ጊዜ ወስዳችሁ ትምህርቱ በልባችሁ ውስጥ በደንብ እንዲተከል አድርጉ” በማለት ተናገረ። አክሎም “የአምላክን አስተሳሰብ የምታንጸባርቁ ከሆነ ለሌሎች በረከት ትሆናላችሁ” በማለት ንግግሩን ደመደመ።