ምዕራፍ 05

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው
ጽሑፉን አሳይ ጽሑፉን ደብቅ

ይሖዋ ልዩ ስጦታ ሰጥቶናል፤ ይህ ስጦታ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን በውስጡ 66 ትናንሽ መጻሕፍትን ይዟል። ሆኖም ‘መጽሐፍ ቅዱስ ወደ እኛ የደረሰው እንዴት ነው? የዚህ መጽሐፍ ባለቤት ማን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን።

1. መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች ከሆኑ የአምላክ ቃል ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት 40 የሚሆኑ ሰዎች ናቸው፤ የተጻፈውም ከ1513 ዓ.ዓ. እስከ 98 ዓ.ም. ድረስ ባሉት 1,600 ዓመታት ገደማ ውስጥ ነው። ጸሐፊዎቹ የተለያየ አስተዳደግና የኑሮ ደረጃ ያላቸው ናቸው፤ ለምሳሌ አንዳንዶቹ ገበሬዎች፣ ሌሎቹ ዓሳ አጥማጆች ወይም ነገሥታት ናቸው:: ያም ቢሆን ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እርስ በርስ ይስማማሉ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ስለሆነ ነው። (1 ተሰሎንቄ 2:13⁠ን አንብብ።) ጸሐፊዎቹ የመዘገቡት የራሳቸውን ሐሳብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ከአምላክ የተቀበሉትን በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናግረዋል a (2 ጴጥሮስ 1:21) አምላክ ሰዎች የእሱን ሐሳብ እንዲጽፉ ለመምራት ወይም ለማነሳሳት መንፈስ ቅዱስን ተጠቅሟል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

2. መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ አጋጣሚ ያላቸው እነማን ናቸው?

“በምድር ላይ [የሚኖር] ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች የመስማት አጋጣሚ አለው። (ራእይ 14:6⁠ን አንብብ።) አምላክ መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ ዘመናት ውስጥ ከተዘጋጁት መጻሕፍት ሁሉ ይበልጥ በብዙ ቋንቋዎች እንዲገኝ አድርጓል። ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚችልበት አጋጣሚ አለው። ሰዎች የሚኖሩት የትም ይሁን የት ወይም የሚናገሩት ቋንቋ ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት ይችላሉ።

3. ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እንደ ቆዳና ፓፒረስ ባሉ በጊዜ ሂደት ሊበላሹ የሚችሉ ነገሮች ላይ ነው። ሆኖም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ፍቅር ያላቸው ሰዎች መልእክቱን በእጃቸው በጥንቃቄ ይገለብጡ ነበር። ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም አንዳንዶች ሕይወታቸውን ጭምር አደጋ ላይ በመጣል መጽሐፍ ቅዱስን ታድገዋል። ይሖዋ ምንም ነገር ወይም ማንኛውም አካል ሐሳቡን ለእኛ ከመግለጽ እንዲያግደው አልፈቀደም። መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላካችን ቃል . . . ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላል።—ኢሳይያስ 40:8

ጠለቅ ያለ ጥናት

አምላክ ሰዎች የእሱን ሐሳብ እንዲጽፉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ተጠብቆ እንዲቆይና ወደ ሰዎች እጅ እንዲደርስ ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

4. መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ስለ መጽሐፉ ባለቤት ማወቅ እንችላለን

ቪዲዮውን ተመልከቱ። ከዚያም 2 ጢሞቴዎስ 3:16ን አንብቡና በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች ከሆኑ የአምላክ ቃል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

  • አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለጻፉት ሰዎች ሐሳቡን አስተላልፏል ብሎ ማመን ምክንያታዊ ይመስልሃል?

አንድ ጸሐፊ፣ አለቃው የነገረውን መልእክት ተቀብሎ ደብዳቤ ሊጽፍ ይችላል፤ ሆኖም የመልእክቱ ባለቤት ጸሐፊው ሳይሆን አለቃው ነው። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት፣ ሰዎች ቢሆኑም የመልእክቱ ምንጭ አምላክ ነው

5. መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መሰናክሎችን አልፏል

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ከሆነ አምላክ ተጠብቆ እንዲቆይ እንደሚያደርገው ግልጽ ነው። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። የሃይማኖት መሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሰዎች እጅ እንዳይገባ ለማድረግ ሞክረዋል። ሆኖም በርካታ ሰዎች ተቃውሞና የሞት ዛቻ ቢደርስባቸውም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው መጽሐፍ ቅዱስ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርገዋል። እንዲህ ካደረጉ ሰዎች መካከል ስለ አንዱ ለማወቅ ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ከፍተኛ ተጋድሎ ተደርጓል። ይህን ማወቅህ መጽሐፉን ለማንበብ እንድትነሳሳ ያደርግሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

መዝሙር 119:97ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎምና ለማሰራጨት እንዲነሳሱ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

6. ሁሉም ሰው ሊያገኘው የሚችል መጽሐፍ

በታሪክ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በስፋት የተተረጎመና የተሰራጨ መጽሐፍ የለም። የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • አምላክ ቃሉ ይህን ያህል በስፋት እንዲተረጎምና እንዲሰራጭ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

  • ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ካነሳናቸው ነጥቦች መካከል ትኩረትህን የሳበው የትኛው ነው?

ወደ

100%

የሚጠጋ የዓለማችን ሕዝብ

መጽሐፍ ቅዱስን ሊገባው በሚችለው ቋንቋ ማግኘት ይችላል

ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል

ከ3,000

በሚበልጡ ቋንቋዎች (የምልክት ቋንቋን ጨምሮ)

ይገኛል።

ከ5,000,000,000

በላይ ቅጂዎች እንደታተሙ ይታመናል

በሕትመት ብዛት የትኛውም መጽሐፍ አይወዳደረውም

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከጻፏቸው ሌሎች ጥንታዊ መጻሕፍት የተለየ ነገር የለውም።”

  • አንተ ምን ይመስልሃል?

  • መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

ማጠቃለያ

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው፤ አምላክ ሁሉም ሰዎች ይህን መጽሐፍ ማግኘት እንዲችሉ አድርጓል።

ክለሳ

  • አምላክ፣ ሰዎች በመንፈስ ተመርተው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ አድርጓል ሲባል ምን ማለት ነው?

  • መጽሐፍ ቅዱስ መሰናክሎችን ካለፈበት፣ ከተተረጎመበትና ከተሰራጨበት መንገድ ጋር በተያያዘ አንተን የሚያስገርምህ ምንድን ነው?

  • አምላክ ሐሳቡን ለአንተ ለማስተላለፍ ይህን ሁሉ እንዳደረገ ስታውቅ ምን ይሰማሃል?

ግብ

ምርምር አድርግ

ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ሲሉ ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደከፈሉ ተመልከት።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር (14:26)

መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ሲገለበጥና ሲተረጎም ኖሯል፤ ታዲያ መልእክቱ እንዳልተቀየረ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

“የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተቀይሯል ወይም ተበርዟል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

a በምዕራፍ 07 ላይ እንደሚብራራው መንፈስ ቅዱስ አምላክ የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን የሚጠቀምበት ኃይል ነው።