ምዕራፍ 10

በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘትህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘትህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?
ጽሑፉን አሳይ ጽሑፉን ደብቅ

በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ተጋብዘህ ታውቃለህ? ከዚህ በፊት ተገኝተህ የማታውቅ ከሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባቸው ላይ መገኘት ያስፈራህ ይሆናል። ‘በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ምን ይከናወናል? እነዚህን ስብሰባዎች ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እኔስ መገኘት ያለብኝ ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ፣ ከሌሎች ጋር አብረህ መሰብሰብህ ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችልህና በግል ሕይወትህ የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

1. አብረን የምንሰበሰብበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከሌሎች ጋር መሰብሰብ አስፈላጊ የሆነበትን ዋነኛ ምክንያት ሲገልጽ “በታላቅ ጉባኤ መካከል ይሖዋን አወድሳለሁ” ብሏል። (መዝሙር 26:12) በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች አብረው መሰብሰብ በጣም ያስደስታቸዋል። በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን ለማወደስ፣ ለመዘመርና ለመጸለይ በየሳምንቱ አብረው ይሰበሰባሉ። በተጨማሪም በዓመት ውስጥ ለተወሰኑ ጊዜያት ትላልቅ ስብሰባዎችን በማድረግ አምልኮ ያቀርባሉ።

2. በስብሰባዎቻችን ላይ ምን ትማራለህ?

በስብሰባዎቻችን ላይ የሚሰጠው ትምህርት በሙሉ በአምላክ ቃል ላይ ያተኮረ ነው፤ የአምላክን ቃል ‘በግልጽ የሚያብራራና ትርጉሙ ምን እንደሆነ’ የሚገልጽ ትምህርት ይቀርባል። (ነህምያ 8:8⁠ን አንብብ።) በስብሰባዎቻችን ላይ ስትገኝ ስለ ይሖዋና ድንቅ ስለሆኑት ባሕርያቱ የመማር አጋጣሚ ታገኛለህ። ይሖዋ ለአንተ ስላለው ፍቅር ይበልጥ ባወቅክ መጠን ወደ እሱ እየቀረብክ ትሄዳለህ። በተጨማሪም በስብሰባዎቻችን ላይ፣ አምላክ አስደሳች ሕይወት እንድትመራ የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ትማራለህ።—ኢሳይያስ 48:17, 18

3. በስብሰባዎቻችን ላይ ከሌሎች ጋር መገናኘትህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

ይሖዋ ‘እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድትችሉ አንዳችሁ ለሌላው ትኩረት ስጡ፤ . . . መሰብሰባችሁን ቸል አትበሉ’ የሚል ምክር ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) በስብሰባዎቻችን ላይ እርስ በርስ ከልብ የሚተሳሰቡና ልክ እንደ አንተ ስለ አምላክ ይበልጥ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎችን ታገኛለህ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያገኟቸውን የሚያበረታቱ ሐሳቦች ሲናገሩ ትሰማለህ። (ሮም 1:11, 12⁠ን አንብብ።) በተጨማሪም በሕይወት ውስጥ ያጋጠሟቸውን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ እየተወጡ ካሉ ያላገቡም ሆኑ ትዳር የመሠረቱ ሰዎች ጋር የመጨዋወት አጋጣሚ ታገኛለህ። ይሖዋ አዘውትረን እንድንሰበሰብ ከሚፈልግባቸው ምክንያቶች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው።

ጠለቅ ያለ ጥናት

በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ምን እንደሚከናወንና በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የምታደርገው ጥረት አያስቆጭም የምንለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

4. የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ለይሖዋ አምልኮ ለማቅረብ አዘውትረው ይሰበሰቡ ነበር። (ሮም 16:3-5) ቆላስይስ 3:16ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ለይሖዋ አምልኮ የሚያቀርቡት እንዴት ነበር?

በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች በአምልኮ ቦታዎቻቸው አዘውትረው ይሰበሰባሉ። ስብሰባዎቻቸው ምን እንደሚመስሉ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም ቪዲዮውንና የጉባኤ ስብሰባ ሲደረግ የሚያሳየውን ሥዕል ተጠቅማችሁ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ በቆላስይስ 3:16 ላይ የተጠቀሱት የትኞቹ ነገሮች እንደሚከናወኑ አስተውለሃል?

  • በቪዲዮው ወይም በሥዕሉ ላይ ሌላ ትኩረትህን የሳበው ነገር አለ?

ሁለተኛ ቆሮንቶስ 9:7ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ገንዘብ የማይጠየቀው ለምንድን ነው?

በዚህ ሳምንት ስብሰባ ላይ ምን ትምህርቶች እንደሚቀርቡ ከአስተማሪህ ጋር ተወያዩ።

  • በስብሰባው ላይ ከሚቀርቡት ትምህርቶች መካከል የአንተን ትኩረት የሳበው ወይም ሊጠቅምህ እንደሚችል የተሰማህ የትኛው ነው?

ይህን ታውቅ ነበር?

jw.org ላይ በዓለም ዙሪያ ስብሰባዎቻችን የሚደረጉበትን አድራሻና ሰዓት ማግኘት ትችላለህ።

  1. ሀ. በስብሰባዎቻችን ላይ ንግግሮችና ቪዲዮዎች ይቀርባሉ፤ እንዲሁም ለመስበክና ለማስተማር የሚረዱ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። ስብሰባዎቻችን የሚጀመሩትና የሚደመደሙት በመዝሙርና በጸሎት ነው

  2. ለ. በአንዳንድ የስብሰባው ክፍሎች ላይ አድማጮች ሐሳብ እንዲሰጡ ይጋበዛሉ

  3. ሐ. ቤተሰቦችን፣ ያላገቡ ሰዎችን፣ አረጋውያንንና ልጆችን ጨምሮ ማንም ሰው በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ይችላል

  4. መ. በስብሰባዎቻችን ላይ ገንዘብ አንጠይቅም። የይሖዋ ምሥክሮች የመግቢያ ክፍያ አይጠይቁም ወይም እየዞሩ ከተሰብሳቢዎች ገንዘብ አይቀበሉም

5. በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጥረት ይጠይቃል

የኢየሱስ ቤተሰቦች በዚህ ረገድ የተዉትን ምሳሌ ተመልከት። በየዓመቱ በሚከበር አንድ በዓል ላይ ለመገኘት ከናዝሬት እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ያለውን 100 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ተራራማ መንገድ መጓዝ ነበረባቸው። ሉቃስ 2:39-42ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉት ይህ ጉዞ መሥዋዕትነት መክፈል የሚጠይቅ ይመስልሃል?

  • በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ምን መሥዋዕትነት መክፈል ሊጠይቅብህ ይችላል?

  • በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጥረት በማድረግህ እንደምትጠቀም ይሰማሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘት ያለብን ለምንድን ነው?

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ከሌሎች ጋር መሰብሰብ አያስፈልግህም። በግልህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ በቂ ነው።”

  • ይሖዋ በዚህ ረገድ ያለውን አመለካከት ለማወቅ የሚረዳን የትኛው ጥቅስ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ነው?

ማጠቃለያ

በስብሰባዎች ላይ መገኘትህ ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለማወቅ፣ ከእሱ ጋር ያለህን ወዳጅነት ለማጠናከርና ከሌሎች ጋር አብረህ አምልኮ ለማቅረብ ይረዳሃል።

ክለሳ

  • ይሖዋ ከሌሎች ጋር እንድንሰበሰብ የሚያበረታታን ለምንድን ነው?

  • በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ምን ትማራለህ?

  • በስብሰባዎች ላይ መገኘትህ ሌላስ ምን ጥቅም የሚያስገኝልህ ይመስልሃል?

ግብ

ምርምር አድርግ

በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ቢያስፈራህስ? በአንድ ወቅት እንዲህ ይሰማው የነበረ ሰው በኋላ ላይ ስብሰባዎቻችንን መውደድ የጀመረው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

የተደረገልንን አቀባበል መቼም ቢሆን አንረሳውም (4:16)

አንድ ወጣት በስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚወደው ለምን እንደሆነና በቋሚነት መሰብሰቡን ለመቀጠል ምን እንዳደረገ ተመልከት።

በስብሰባዎች ላይ መገኘት በጣም ያስደስተኝ ነበር! (4:33)

አንዳንድ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ ስለመገኘት የሰጡትን አስተያየት አንብብ።

“በስብሰባ አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያለብኝ ለምንድን ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)