ምዕራፍ 29

የሞቱ ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

የሞቱ ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
ጽሑፉን አሳይ ጽሑፉን ደብቅ

የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ታውቃለህ? እንዲህ ያለ ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥምህ የሚከተሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል፦ ‘የሞቱ ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ እናገኛቸው ይሆን?’ መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን የሚያጽናና መልስ በዚህና በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።

1. የሞቱ ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

ኢየሱስ ሞትን ከከባድ እንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። ሞት ከእንቅልፍ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የወሰደው ሰው በዙሪያው የሚከናወነውን ነገር አያውቅም። በተመሳሳይም አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ምንም ሥቃይ አይሰማውም። ለጓደኞቹና ለቤተሰቦቹ ምንም ያህል ፍቅር የነበረው ቢሆን እንኳ ከሞተ በኋላ የብቸኝነት ስሜት ሊሰማው አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” ይላል።—መክብብ 9:5⁠ን አንብብ።

2. ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

ብዙ ሰዎች ሞትን አልፎ ተርፎም የሞቱ ሰዎችን ይፈራሉ! መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት የሚናገረውን ነገር ማወቅ ግን ያጽናናል። ኢየሱስ ‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:32) አንዳንድ ሃይማኖቶች ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል የማትሞት ነፍስ እንዳለች ያስተምራሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ አይልም። ማንም ሰው ከሞተ በኋላ አይሠቃይም። በተጨማሪም ሙታን ምንም ነገር ስለማያውቁ እኛን ሊጎዱን አይችሉም። እንዲሁም ከሞቱ ሰዎች ጋር በተያያዘ ለየት ያለ ሃይማኖታዊ ሥርዓት መፈጸም ወይም ስለ እነሱ መጸለይ አያስፈልገንም።

አንዳንዶች ‘የሞቱ ሰዎችን ማነጋገር እንችላለን’ ይላሉ። ሆኖም ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ‘ሙታን ምንም አያውቁም።’ በሞት የተለዩአቸውን ሰዎች እንደሚያነጋግሩ የሚያስቡ ሰዎች የሚያነጋግሩት የሞቱትን ሰዎች ሳይሆን እነሱን መስለው የሚቀርቡ አጋንንትን ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ሞትን በተመለከተ እውነቱን ማወቃችን ከአጋንንት ይጠብቀናል። ይሖዋ ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመነጋገር መሞከር እንደሌለብን አስጠንቅቆናል፤ ምክንያቱም አጋንንት በዚህ ተጠቅመው ሊጎዱን እንደሚችሉ ያውቃል።—ዘዳግም 18:10-12⁠ን አንብብ።

ጠለቅ ያለ ጥናት

መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተመለከተ ምን እንደሚያስተምር በስፋት እንመለከታለን። በተጨማሪም አፍቃሪ የሆነው አምላክ የሞቱ ሰዎችን እንደማያሠቃይ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምን እንደሆነ እናያለን።

3. የሞቱ ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

የሞቱ ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ በዓለም ዙሪያ የተለያየ አመለካከት አለ። መቼም እነዚህ ሁሉ አመለካከቶች እውነት ሊሆኑ እንደማይችሉ የታወቀ ነው።

  • የሞቱ ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ በአካባቢህ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ለማወቅ ቪዲዮውን ተመልከቱ

መክብብ 3:20ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • በዚህ ጥቅስ መሠረት ሰው ከሞተ በኋላ ምን ይሆናል?

  • ሰው ሲሞት በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ነገር አለች?

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ ስለነበረው ስለ አልዓዛር ሞት ይናገራል። ዮሐንስ 11:11-14ን አንብቡ፤ ጥቅሱ ሲነበብ ኢየሱስ አልዓዛር የሚገኝበትን ሁኔታ የገለጸው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ኢየሱስ ሞትን ከምን ጋር አመሳስሎታል?

  • ይህ ንጽጽር የሞቱ ሰዎች ስለሚገኙበት ሁኔታ ምን ያስተምረናል?

  • መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተመለከተ ስለሚያስተምረው ትምህርት ምን ይሰማሃል?

4. ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ይጠቅመናል

ሞትን በተመለከተ እውነቱን ማወቃችን የሞቱ ሰዎችን እንዳንፈራ ይረዳናል። መክብብ 9:10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • የሞቱ ሰዎች ሊጎዱን ይችላሉ?

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቃችን ‘የሞቱ ሰዎች በሕይወት ያሉትን ሊጎዱ ይችላሉ’ ወይም ‘ሊመለኩ ይገባል’ ከሚለው እምነትም ይጠብቀናል። ኢሳይያስ 8:19ን እና ራእይ 4:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ለሞቱ ሰዎች አምልኮ የሚያቀርብን ወይም የእነሱን እርዳታ ለማግኘት የሚሞክርን ሰው በተመለከተ ይሖዋ ምን የሚሰማው ይመስልሃል?

ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ይሖዋን ከሚያሳዝኑ ልማዶች እንድንርቅ ይረዳናል

5. ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ያጽናናናል

ብዙ ሰዎች ቀደም ሲል ለሠሩት ኃጢአት፣ ከሞቱ በኋላ እንደሚቀጡ ተምረዋል። ሆኖም ማንም ሰው፣ ሌላው ቀርቶ በጣም መጥፎ ነገሮችን ያደረገ ሰው እንኳ ከሞተ በኋላ እንደማይሠቃይ ማወቃችን ያጽናናናል። ሮም 6:7ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ሞት ከኃጢአት ነፃ የሚያወጣ ከሆነ የሞቱ ሰዎች ቀደም ሲል በሠሩት ኃጢአት ምክንያት የሚሠቃዩ ይመስልሃል?

ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ የሞቱ ሰዎችን እንደማያሠቃይ ያለን እምነትም የዚያኑ ያህል ይጠናከራል። ዘዳግም 32:4ን እና 1 ዮሐንስ 4:8ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተገለጹት ባሕርያት ያሉት አምላክ የሞቱ ሰዎች እንዲሠቃዩ የሚያደርግ ይመስልሃል?

  • ስለ ሞት እውነቱን ማወቅህ ያጽናናሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ከሞትኩ በኋላ እሠቃያለሁ ብዬ እፈራለሁ።”

  • እንዲህ የሚሉ ሰዎችን ለማጽናናት የትኞቹን ጥቅሶች ልትጠቀም ትችላለህ?

ማጠቃለያ

አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ምንም አያውቅም። የሞቱ ሰዎች አይሠቃዩም፤ በሕይወት ያሉትንም ሊጎዱ አይችሉም።

ክለሳ

  • የሞቱ ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

  • ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

  • ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን የሚያጽናናን እንዴት ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

“ነፍስ” የሚለው ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ትርጉም አለው?

“ነፍስ ምንድን ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

አምላክ ክፉዎችን በሲኦል ያሠቃያል?

ሲኦል ኃጢአተኞች የሚሠቃዩበት ቦታ ነው? (3:07)