ምዕራፍ 30

በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ዳግመኛ በሕይወት ይኖራሉ!

በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ዳግመኛ በሕይወት ይኖራሉ!
ጽሑፉን አሳይ ጽሑፉን ደብቅ

ሞት ከባድ ሐዘን ያስከትላል። መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ጠላት በማለት የሚጠራው ለዚህ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ምዕራፍ 27 ላይ አምላክ ይህን ጠላት ድል እንደሚያደርገው ተምረሃል። ይሁንና እስካሁን ስለሞቱት ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? በዚህ ምዕራፍ ላይ ይሖዋ የሰጠውን ሌላ አስደሳች ተስፋ እንመለከታለን፤ አምላክ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት አስነስቶ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል! በእርግጥ የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ? ከተነሱ በኋላስ የሚኖሩት በሰማይ ነው ወይስ በምድር?

1. ይሖዋ በሞት ለተለዩን ሰዎች ምን ሊያደርግላቸው ይፈልጋል?

ይሖዋ የሞቱ ሰዎች ዳግመኛ በሕይወት እንዲኖሩ የሚያደርግበትን ጊዜ ይናፍቃል። ኢዮብ የተባለ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ፣ ከሞተ በኋላ አምላክ እንደማይረሳው እርግጠኛ ነበር። “አንተ ትጣራለህ፤ እኔም [ከመቃብር] እመልስልሃለሁ” በማለት ለአምላክ ተናግሯል።—ኢዮብ 14:13-15⁠ን አንብብ።

2. የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ በምን እናውቃለን?

ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ አምላክ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል ሰጥቶት ነበር። ኢየሱስ አንዲትን የ12 ዓመት ልጅና የአንዲትን መበለት ልጅ ከሞት አስነስቷል። (ማርቆስ 5:41, 42፤ ሉቃስ 7:12-15) ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ወዳጅ አልዓዛር ሞተ። አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ቢያልፈውም ኢየሱስ ከሞት አስነስቶታል። ኢየሱስ ወደ አምላክ ከጸለየ በኋላ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” አለ። በዚህ ጊዜ “የሞተው ሰው . . . ወጣ።” አልዓዛር ዳግመኛ በሕይወት መኖር ጀመረ! (ዮሐንስ 11:43, 44) የአልዓዛር ቤተሰቦችና ጓደኞች ምን ያህል ተደስተው ይሆን!

3. በሞት ያጣሃቸው ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች “ከሞት እንደሚነሱ” ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች ወደ ሰማይ አልሄዱም። (ዮሐንስ 3:13) እዚሁ ምድር ላይ ዳግመኛ በሕይወት የመኖር አጋጣሚ በማግኘታቸው ተደስተዋል። ወደፊትም ቢሆን ኢየሱስ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ያደርጋል። “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ” ትንሣኤ እንደሚያገኙ ተናግሯል፤ አንዳንዶቹ ከሰዎች አእምሮ የጠፉ ቢሆንም እንኳ አምላክ ያስታውሳቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29

ጠለቅ ያለ ጥናት

ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል እንዳለው ደግሞም እንዲህ እንደሚያደርግ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንመረምራለን። በተጨማሪም የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ ማወቅህ እንድትጽናና እና ተስፋ እንዲኖርህ የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

4. ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን ማስነሳት እንደሚችል አሳይቷል

ኢየሱስ ለወዳጁ ለአልዓዛር ያደረገውን ነገር በስፋት እንመልከት። ዮሐንስ 11:14, 38-44ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • አልዓዛር በእርግጥ ሞቶ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?—ቁጥር 39⁠ን ተመልከት።

  • አልዓዛር ወደ ሰማይ ሄዶ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ መልሶ ወደ ምድር እንዲመጣ የሚያደርገው ይመስልሃል?

ቪዲዮውን ተመልከቱ።

5. ብዙ ሰዎች ከሞት ይነሳሉ!

መዝሙር 37:29ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ከሞት የሚነሱት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚኖሩት የት ነው?

ኢየሱስ ይሖዋን ያመልኩ የነበሩ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ሰዎችንም ከሞት ያስነሳል። የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በትንሣኤ ለማግኘት የምትጓጓው ማንን ነው?

እስቲ አስበው፦ አንድ አባት በቀላሉ ልጁን ከእንቅልፉ መቀስቀስ እንደሚችል ሁሉ ኢየሱስም የሞቱ ሰዎችን በቀላሉ ማስነሳት ይችላል

6. የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ ማወቅህ እንድትጽናና እና ተስፋ እንዲኖርህ ይረዳሃል

ስለ ኢያኢሮስ ሴት ልጅ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሐዘን የደረሰባቸውን ብዙ ሰዎች አጽናንቷል እንዲሁም አበረታቷል። ይህን እውነተኛ ታሪክ ሉቃስ 8:40-42, 49-56 ላይ አንብቡ።

ኢየሱስ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ከማስነሳቱ በፊት ለኢያኢሮስ “አትፍራ፤ ብቻ እመን” ብሎታል። (ቁጥር 50⁠ን ተመልከት።) የትንሣኤ ተስፋ በሚከተሉት ሁኔታዎች ሥር የሚረዳህ እንዴት ነው?

  • የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ

  • ሕይወትህ አደጋ ላይ ሲወድቅ

ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • የትንሣኤ ተስፋ የፌሊሲቲን ወላጆች ያጽናናቸውና ያበረታታቸው እንዴት ነው?

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ሰዎች ከሞት ተነስተው ምድር ላይ ይኖራሉ ብሎ ማመን ይከብደኛል።”

  • አንተ ምን ይመስልሃል?

  • የሞቱ ሰዎች ተነስተው በምድር ላይ እንደሚኖሩ ለማስረዳት የትኛውን ጥቅስ ልትጠቀም ትችላለህ?

ማጠቃለያ

መጽሐፍ ቅዱስ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ ይናገራል። ይሖዋ እነዚህ ሰዎች ዳግመኛ በሕይወት እንዲኖሩ ይፈልጋል፤ ለኢየሱስም የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል ሰጥቶታል።

ክለሳ

  • ይሖዋና ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት እንደሚጓጉ በምን እናውቃለን?

  • በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነስተው የሚኖሩት የት ነው? በሰማይ ወይስ በምድር? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

  • በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ዳግመኛ በሕይወት እንደሚኖሩ እርግጠኛ እንድትሆን የሚያደርግህ ምንድን ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሐዘን የደረሰበትን ሰው ሊረዱ ይችላሉ?

የምትወዱት ሰው ሲሞት (5:06)

ልጆች የቤተሰባቸው አባል ወይም የጓደኛቸው ሞት ያስከተለባቸውን ሐዘን መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?

ቤዛው (2:07)

ከሞቱ በኋላ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች አሉ? ከሞት የማይነሱ ሰዎችስ አሉ?

“ትንሣኤ ምንድን ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)