ምዕራፍ 40
በአምላክ ፊት ንጹሕ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
ትንሹን ልጇን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እያዘጋጀች ያለችን እናት በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። ልጇ በደንብ መተጣጠቡን እንዲሁም ልብሶቹ ንጹሕና ሥርዓታማ መሆናቸውን ታረጋግጣለች። ንጽሕና ለልጇ ጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ልጁ ንጹሕ መሆኑ ወላጆቹ በሚገባ እንደሚንከባከቡት ያሳያል። በተመሳሳይም አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ አካላዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችን የተጠበቀ እንዲሆን ይፈልጋል። ንጹሕ መሆናችን ራሳችንን ይጠቅመናል፤ ለይሖዋም ክብር ያመጣል።
1. አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቅና ንብረቶቻችንን በንጽሕና መያዝ የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ “ቅዱሳን ሁኑ” የሚል ምክር ሰጥቶናል። (1 ጴጥሮስ 1:16) ቅዱስ መሆን አካላዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅን ይጨምራል። አዘውትረን በመታጠብ እንዲሁም ልብሳችን፣ ቤታችንና ተሽከርካሪያችን ንጹሕና ያልተዝረከረከ እንዲሆን በማድረግ ንጽሕናችንን መጠበቅ እንችላለን። በተጨማሪም የስብሰባ አዳራሻችንን በንጽሕና በመያዝ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። በእነዚህ መንገዶች ንጽሕናችንን በመጠበቅ ይሖዋን እናስከብራለን።—2 ቆሮንቶስ 6:3, 4
2. ንጹሕ ለመሆን የትኞቹን ልማዶች ልናስወግድ ይገባል?
መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን [እንድናነጻ]” ያሳስበናል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) በመሆኑም ሰውነታችንንም ሆነ አእምሯችንን ሊጎዳ ከሚችል ከየትኛውም ነገር እንርቃለን። አስተሳሰባችን ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን ስለምንፈልግ ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦችን ወደ አእምሯችን ላለማስገባት እንሞክራለን። (መዝሙር 104:34) በተጨማሪም ንግግራችን ንጹሕ እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን።—ቆላስይስ 3:8ን አንብብ።
አካላዊ ወይም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን የሚያጎድፉብን ሌሎች ነገሮች ምንድን ናቸው? ወደ ሰውነታችን የምናስገባቸው አንዳንድ ነገሮች ሰውነታችንን ሊጎዱ ይችላሉ። በመሆኑም ሲጋራ እንደማጨስ፣ ጫት እንደመቃምና ዕፆችን አላግባብ እንደመጠቀም ያሉ መጥፎ ልማዶችን እናስወግዳለን። ከእነዚህ ልማዶች መራቃችን የተሻለ ጤንነት እንዲኖረን ያደርጋል፤ በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አክብሮት እንዳለንም ያሳያል። በተጨማሪም እንደ ማስተርቤሽን a እንዲሁም የብልግና ምስሎችን እንደመመልከት ካሉ መጥፎ ልማዶች በመራቅ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ጥረት እናደርጋለን። (መዝሙር 119:37፤ ኤፌሶን 5:5) እንዲህ ያሉ ልማዶችን ማሸነፍ ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ይሖዋ ይረዳናል።—ኢሳይያስ 41:13ን አንብብ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቃችን ይሖዋን የሚያስከብረው እንዴት እንደሆነና መጥፎ ልማዶችን ማስወገድ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
3. አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቃችንና ንብረቶቻችንን በንጽሕና መያዛችን ይሖዋን ያስከብራል
ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጣቸው ትእዛዛት እሱ ለንጽሕና ያለውን አመለካከት ለመረዳት ያስችሉናል። ዘፀአት 19:10ን እና 30:17-19ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
-
እነዚህ ጥቅሶች ይሖዋ ለአካላዊ ንጽሕና ስላለው አመለካከት ምን ይጠቁሙናል?
-
ሁሌም አካላዊ ንጽሕናህ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉህ አንዳንድ ጥሩ ልማዶች የትኞቹ ናቸው?
አካላዊ ንጽሕናን መጠበቅና ንብረቶቻችንን በንጽሕና መያዝ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ሆኖም የምንኖረው የትም ይሁን የት ወይም የኑሮ ደረጃችን ምንም ይሁን ምን ንጽሕናችንን መጠበቅ እንችላለን። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
-
ያሉንን ነገሮች በንጽሕናና በሥርዓት መያዛችን የስብከቱ ሥራችንን የሚያስከብረው እንዴት ነው?
4. ሱሶችን አስወግድ
ሲጋራ የምታጨስ ወይም ዕፆችን አላግባብ የምትጠቀም ከሆነ እነዚህን ሱሶች ማሸነፍ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለመረዳት አትቸገርም። ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ሊረዳህ ይችላል? እነዚህ ሱሶች በሕይወትህ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ለማሰብ ሞክር። ማቴዎስ 22:37-39ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
-
አንድ ሰው ሲጋራ ማጨሱ ወይም ዕፆችን አላግባብ መጠቀሙ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና የሚነካበት እንዴት ነው?
-
እንዲህ ማድረጉ በቤተሰቡና በዙሪያው ባሉ ሰዎችስ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
ሱስ ካለብህ፣ ይህን ሱስ ለማስወገድ ዕቅድ አውጣ። b ቪዲዮውን ተመልከቱ።
ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
-
አንድ ሰው የመጸለይ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናትና በስብሰባዎች ላይ የመገኘት ጥሩ ልማድ ማዳበሩ መጥፎ ልማዶችን ለማሸነፍ ኃይል የሚሰጠው እንዴት ነው?
5. ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦችንና ልማዶችን ለማስወገድ ትግል አድርግ
ቆላስይስ 3:5ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
-
የብልግና ምስሎችን መመልከት፣ ሴክስቲንግ c እንዲሁም ማስተርቤሽን በይሖዋ ዓይን ርኩስ እንደሆኑ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
-
ይሖዋ በሥነ ምግባር ንጹሕ እንድንሆን መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
መጥፎ ሐሳቦችን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ።
ኢየሱስ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሯል። ማቴዎስ 5:29, 30ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
-
ኢየሱስ ቃል በቃል በሰውነታችን ላይ ጉዳት ማድረስ እንዳለብን መናገሩ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ማመልከቱ ነበር። አንድ ሰው ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦችን ለማስወገድ ምን ዓይነት ቆራጥ እርምጃ ሊወስድ ይችላል? d
ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦችን ለማስወገድ እየታገልክ ከሆነ ይሖዋ የምታደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። መዝሙር 103:13, 14ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
-
አንድን መጥፎ ልማድ ለማሸነፍ እየታገልክ ከሆነ ይህ ጥቅስ ተስፋ እንዳትቆርጥ የሚረዳህ እንዴት ነው?
ተስፋ አትቁረጥ!
አንድ መጥፎ ልማድ ሲያገረሽብህ ‘ምንም ሊሳካልኝ አልቻለም፤ ታዲያ ምን አታገለኝ?’ ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ሆኖም ይህን ለማሰብ ሞክር፦ አንድ ሯጭ ተደናቅፎ ወደቀ ማለት በውድድሩ ተሸነፈ ማለት አይደለም፤ ደግሞም ሩጫውን ከመነሻው መጀመር አያስፈልገውም። በተመሳሳይም አንድ መጥፎ ልማድ አገረሸብህ ማለት በምታደርገው ትግል ተሸነፍክ ማለት አይደለም፤ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ያደረግከው ጥረትም ከንቱ ይሆናል ማለት አይደለም። አንድን መጥፎ ልማድ ለማሸነፍ በምታደርገው ትግል እንዲህ ያለ ነገር ማጋጠሙ የሚጠበቅ ነው። ስለዚህ ተስፋ አትቁረጥ! በይሖዋ እርዳታ ያለብህን መጥፎ ልማድ ማሸነፍ ትችላለህ።
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ሱስ ሆኖብኛል፤ ፈጽሞ ላቆመው አልችልም።”
-
በይሖዋ እርዳታ መጥፎ ልማዶችን ማሸነፍ እንደሚቻል ለማሳየት የትኛውን ጥቅስ ልትጠቀም ትችላለህ?
ማጠቃለያ
አካላዊ፣ አእምሯዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን መጠበቃችን ይሖዋን ያስደስተዋል።
ክለሳ
-
ንጹሕ መሆናችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
-
አካላዊ ንጽሕናህን መጠበቅና ንብረቶችህን በንጽሕና መያዝ የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
-
አእምሯዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
ምርምር አድርግ
ብዙ ገንዘብ ባይኖርህም እንኳ አካላዊ ንጽሕናህን ለመጠበቅ የትኞቹን ቀላል ነገሮች ልታደርግ ትችላለህ?
የብልግና ምስሎችን መመልከት የሚያስከትለው ጉዳት አለ?
a ማስተርቤሽን የራስን የፆታ ብልት በማሻሸት የፆታ ስሜትን የማርካት ልማድ ነው።
b በዚህ ምዕራፍ ውስጥ “ምርምር አድርግ” በሚለው ክፍል ሥር የሚገኘው “ማጨስ ለማቆም ምን ማድረግ ይቻላል?” የሚለው ርዕስ ሱሶችን ለማሸነፍ ልትወስዳቸው ስለምትችላቸው ጠቃሚ እርምጃዎች ይናገራል።
c ሴክስቲንግ የብልግና ይዘት ያላቸውን መልእክቶች፣ ፎቶዎች ወይም ቪዲዮዎች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ መላላክን ያመለክታል።
d የማስተርቤሽን ልማድን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 25 ላይ የሚገኘውን “የማስተርቤሽን ልማድን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ