ምዕራፍ 42

መጽሐፍ ቅዱስ ሳያገቡ ስለመኖርና ስለ ትዳር ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ሳያገቡ ስለመኖርና ስለ ትዳር ምን ይላል?
ጽሑፉን አሳይ ጽሑፉን ደብቅ

በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ሰው ካላገባ ደስተኛ ሊሆን እንደማይችል ይታመናል። ሆኖም ትዳር የመሠረቱ ሰዎች በሙሉ ደስተኞች ናቸው ማለት አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትዳር ባይመሠርቱም ደስተኛ የሆኑ ሰዎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሳያገቡ መኖርም ሆነ ትዳር መመሥረት ስጦታዎች እንደሆኑ ይናገራል።

1. ሳያገቡ መኖር ምን ጥቅሞች አሉት?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሚያገባ ሁሉ መልካም ያደርጋል፤ ሳያገባ የሚኖር ሁሉ ደግሞ የተሻለ ያደርጋል።” (1 ቆሮንቶስ 7:32, 33, 38⁠ን አንብብ።) ያላገቡ ሰዎች ‘የተሻለ ያደርጋሉ’ የተባለው ከምን አንጻር ነው? ያላገቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛን ፍላጎት የማሟላት ጉዳይ አያሳስባቸውም። በመሆኑም በጥቅሉ ሲታይ የበለጠ ነፃነት አላቸው። አንዳንዶች ይሖዋን የበለጠ ለማገልገል ሁኔታቸው ይፈቅድላቸዋል፤ ለምሳሌ ወደ ሌላ አገር ሄደው ምሥራቹን መስበክ ችለዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የሚያስችል ሰፋ ያለ ጊዜ አላቸው።

2. ሕጋዊ ጋብቻ መመሥረት ምን ጥቅሞች አሉት?

ሳያገቡ መኖር የራሱ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ትዳር መመሥረትም የራሱ ጥቅም አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:9) በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በትዳራቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች ይህ ጥቅስ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ማየት ይችላሉ። ሕጋዊ ጋብቻ የሚመሠርቱ ባለትዳሮች እርስ በርስ ለመዋደድ፣ ለመከባበርና አንዳቸው ሌላውን ለመንከባከብ ቃል ይገባሉ። እንዲህ ያለ ቃለ መሐላ የገቡ ባለትዳሮች በአብዛኛው ሳይጋቡ ከሚኖሩ ጥንዶች የበለጠ የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል። በተጨማሪም ሕጋዊ ጋብቻ መመሥረት ልጆች ከስጋት ነፃ ሆነው እንዲያድጉ ያስችላል።

3. ይሖዋ ለትዳር ምን አመለካከት አለው?

ይሖዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋብቻን ዝግጅት ሲያቋቁም እንዲህ ብሏል፦ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል።” (ዘፍጥረት 2:24) ይሖዋ ባልና ሚስት በሕይወት እስካሉ ድረስ እርስ በርስ እንዲዋደዱና ሳይለያዩ አብረው እንዲኖሩ ይፈልጋል። አንድ ባልና ሚስት ፍቺ እንዲፈጽሙ የሚፈቅደው አንደኛው ወገን ካመነዘረ ብቻ ነው። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ይሖዋ የተበደለው ወገን ፍቺ ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም መወሰን እንዲችል መብት ሰጥቶታል። a (ማቴዎስ 19:9) ይሖዋ ክርስቲያኖች ከአንድ በላይ እንዲያገቡ አይፈቅድም።—1 ጢሞቴዎስ 3:2

ጠለቅ ያለ ጥናት

ያላገባህም ሆንክ ትዳር የመሠረትክ ደስተኛ መሆንና ይሖዋን ማስደሰት የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

4. ያላገባህ መሆንህ የሚያስገኝልህን ነፃነት በአግባቡ ተጠቀምበት

ኢየሱስ ሳያገቡ መኖር ስጦታ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:11, 12) ማቴዎስ 4:23ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ኢየሱስ አለማግባቱ ያስገኘለትን ነፃነት አባቱን ለማገልገልና ሌሎችን ለመርዳት የተጠቀመበት እንዴት ነው?

ያላገቡ ክርስቲያኖችም የኢየሱስ ዓይነት ሕይወት በመምራት ደስታ ማግኘት ይችላሉ። ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ያላገቡ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን በየትኞቹ አስደሳች መንገዶች ሊጠቀሙበት ይችላሉ?

ይህን ታውቅ ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ትዳር ሊመሠርት የሚገባው ስንት ዓመት ሲሞላው እንደሆነ አይናገርም። ሆኖም ‘አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ካለፈ’ በኋላ ማግባት የተሻለ እንደሆነ ይመክራል፤ ምክንያቱም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የፆታ ስሜት ስለሚያይል ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 7:36

5. የትዳር ጓደኛህን በጥበብ ምረጥ

በሕይወትህ ውስጥ ከምታደርጋቸው ከባድ ውሳኔዎች መካከል አንዱ የትዳር ጓደኛን መምረጥ ነው። ማቴዎስ 19:4-6, 9ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ክርስቲያኖች በችኮላ ትዳር መመሥረት የሌለባቸው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ የትዳር አጋር የሚሆንህን ሰው ለማወቅ ይረዳሃል። ትዳር መመሥረት የሚፈልጉ ሰዎች ከሁሉ በላይ ሊያሳስባቸው የሚገባው ሊያገቡ ያሰቡት ሰው ይሖዋን የሚወድ መሆኑ ነው። b አንደኛ ቆሮንቶስ 7:39ን እና 2 ቆሮንቶስ 6:14ን አንብቡ። ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ከእኛ ጋር አንድ ዓይነት እምነት ያለውን ሰው ብቻ ማግባት ያለብን ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ እሱን የማይወድ ሰው ብናገባ ምን የሚሰማው ይመስልሃል?

ሁለት የተለያዩ እንስሳት በአንድ ቀንበር ከተጠመዱ ሁለቱም ይሠቃያሉ። ይሖዋን የማያገለግል ሰው የሚያገቡ ክርስቲያኖችም ብዙ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል

6. ለትዳር የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ይኑርህ

በጥንቷ እስራኤል የነበሩ አንዳንድ ወንዶች እንደፈለጉ ለመኖር ሲሉ ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ነበር። ሚልክያስ 2:13, 14, 16ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር በሚጋጭ መንገድ የሚፈጸምን ፍቺ የሚጠላው ለምንድን ነው?

ምንዝርና ፍቺ፣ በደል በተፈጸመበት ወገንና በልጆች ላይ ከባድ ጉዳት ያስከትላሉ

ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋን ከማይወድ ሰው ጋር ትዳር የመሠረቱ ሰዎች ትዳራቸው አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?

7. ይሖዋ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያወጣውን መሥፈርት ተከተል

አንድ ሰው ይሖዋ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያወጣውን መሥፈርት ለመከተል ሲል ብዙ መሥዋዕትነት መክፈል ሊያስፈልገው ይችላል። c ሆኖም ይሖዋ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎችን ይባርካል። ቪዲዮውን ተመልከቱ

ዕብራውያን 13:4ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያወጣው መሥፈርት ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ክርስቲያኖች ጋብቻ ወይም ፍቺ ሲፈጽሙ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲያስመዘግቡ ይጠብቅባቸዋል፤ ምክንያቱም የብዙ አገሮች ሕግ እንዲህ እንዲደረግ ያዛል። ቲቶ 3:1ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ትዳር የመሠረትክ ከሆንክ ጋብቻህን ሕጋዊ አድርገሃል?

አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የግድ መጋባት ያስፈልጋል? እንዲሁ አብሮ መኖር ምን ችግር አለው?”

  • ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ማጠቃለያ

ሳያገቡ መኖርም ሆነ ትዳር የይሖዋ ስጦታዎች ናቸው። ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ሰዎች ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እስከኖሩ ድረስ ደስታና እርካታ ማግኘት ይችላሉ።

ክለሳ

  • ያላገቡ ሰዎች ነፃነታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?

  • መጽሐፍ ቅዱስ የእኛ ዓይነት እምነት ያለውን ሰው ብቻ እንድናገባ የሚያዝዘው ለምንድን ነው?

  • በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ፍቺ መፈጸም የሚቻልበት ብቸኛው ምክንያት ምንድን ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

ከመጠናናት እና ትዳር ከመመሥረት ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱህን ሁለት ቪዲዮዎች ተመልከት።

ለጋብቻ መዘጋጀት (11:57)

አንድ ወንድም ይሖዋ የሰጠው ነገር እሱ መሥዋዕት ካደረገው ከየትኛውም ነገር እንደሚበልጥ የሚሰማው ለምንድን ነው?

እውነትን ትቀበላለች ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር (1:56)

a ባለትዳሮች፣ ምንዝር ባይፈጸምም ለመለያየት ሊወስኑ የሚችሉባቸውን ምክንያቶች ለማየት ተጨማሪ ሐሳብ 4⁠ን ተመልከት።

b በአንዳንድ ባሕሎች ለልጆቻቸው የትዳር አጋር የሚመርጡት ወላጆች ናቸው። እንዲህ ያለ ባሕል ያላቸው አፍቃሪ ወላጆች ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ ሲመርጡ በገንዘብ ወይም በኑሮ ደረጃ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋን የሚወድ ሰው ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።

c በአሁኑ ወቅት ካላገባሃት ሴት ጋር አብረህ እየኖርክ ከሆነ ለመለየት ወይም ለመጋባት የራስህን ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ።