ምዕራፍ 43 ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? አጫውት ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ይቅርታ፣ ማጫወቻው መሥራት አልቻለም። ይህን ቪዲዮ አውርድ ጽሑፉን አሳይ ጽሑፉን ደብቅ ዲጂታል እትም በወረቀት የሚታተመው በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ለአልኮል መጠጥ የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች አልፎ አልፎ ከጓደኞቻቸው ጋር መጠጣት ደስ ይላቸዋል። ሌሎች ደግሞ የአልኮል መጠጥ ጨርሶ አይጠጡም። እስኪሰክሩ ድረስ የሚጠጡ ሰዎችም አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ ምን ይላል? 1. የአልኮል መጠጦችን መጠጣት ስህተት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን አይከለክልም። እንዲያውም አምላክ ከሰጠን በርካታ ስጦታዎች መካከል “የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ” እንደሚገኝበት ይገልጻል። (መዝሙር 104:14, 15) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች የአልኮል መጠጥ ይጠጡ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 5:23 2. መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ምን ምክር ይሰጣል? ይሖዋ ከልክ በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። (ገላትያ 5:21) ቃሉ “ብዙ የወይን ጠጅ እንደሚጠጡ . . . ሰዎች አትሁን” ይላል። (ምሳሌ 23:20) በመሆኑም ለብቻችን በምንጠጣበት ጊዜም እንኳ አስተሳሰባችን እስኪዛባ፣ ንግግራችንንና ድርጊታችንን መቆጣጠር እስኪያቅተን ወይም ጤናችን እስከሚጎዳ ድረስ መጠጣት አይኖርብንም። የምንጠጣውን መጠን መቆጣጠር የሚከብደን ከሆነ ከናካቴው መጠጥ ለማቆም መወሰን ሊያስፈልገን ይችላል። 3. ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የሌሎችን ምርጫ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? የአልኮል መጠጥ ከመጠጣት ወይም ካለመጠጣት ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ሊያደርግ ይገባል። አንድ ሰው በልክ ለመጠጣት ከወሰነ ልንተቸው አይገባም፤ መጠጣት የማይፈልግንም ሰው እንዲጠጣ መጫን አይኖርብንም። (ሮም 14:10) የእኛ መጠጣት ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ከሆነ አለመጠጣትን እንመርጣለን። (ሮም 14:21ን አንብብ።) ‘የራሳችንን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም እንፈልጋለን።’—1 ቆሮንቶስ 10:23, 24ን አንብብ። ጠለቅ ያለ ጥናት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት እንድትወስን አሊያም በምትጠጣው መጠን ላይ ገደብ እንድታበጅ የሚረዱህ እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ከመጠጥ ጋር የተያያዘ ችግር ካለብህ ምን ማድረግ እንደምትችል እንመረምራለን። 4. የአልኮል መጠጥ መጠጣት ይኖርብህ እንደሆነና እንዳልሆነ ወስን ኢየሱስ የአልኮል መጠጥ ስለመጠጣት ምን አመለካከት ነበረው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ኢየሱስ የፈጸመውን የመጀመሪያ ተአምር እንመልከት። ዮሐንስ 2:1-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦ ይህ ተአምር ኢየሱስ ለአልኮል መጠጥም ሆነ የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ስላለው አመለካከት ምን ይጠቁመናል? ኢየሱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ስላላወገዘ ክርስቲያኖች የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ክርስቲያኖች የአልኮል መጠጥ መጠጣት ቢችሉም እንዲህ ማድረጋቸው ጥሩ የማይሆንበት ጊዜ አለ። ምሳሌ 22:3ን አንብቡ፤ ከዚያም የሚከተሉት ሁኔታዎች ሰዎች ላለመጠጣት እንዲወስኑ ሊያደርጓቸው የሚችሉት ለምን እንደሆነ ተወያዩ፦ የሚያሽከረክሩ ወይም ማሽን ላይ የሚሠሩ ከሆነ ነፍሰ ጡር ከሆኑ ሐኪም የአልኮል መጠጥ እንዳይጠጡ ከነገራቸው የሚጠጡትን መጠን መቆጣጠር የሚከብዳቸው ከሆነ የአገሪቱ ሕግ የአልኮል መጠጥ እንዲጠጡ የማይፈቅድላቸው ከሆነ የሚጠጣውን መጠን መቆጣጠር ስለሚከብደው ጨርሶ ላለመጠጣት ከወሰነ ሰው ጋር አብረው ሲሆኑ በሠርግ ድግስ ላይ ወይም በሌሎች ግብዣዎች ላይ የአልኮል መጠጥ ማቅረብ ይኖርብህ ይሆን? ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦችን ለማግኘት ቪዲዮውን ተመልከቱ። ቪዲዮ፦ የአልኮል መጠጥ ማቅረብ ይኖርብኝ ይሆን? (2:41) ሮም 13:13ን እና 1 ቆሮንቶስ 10:31, 32ን አንብቡ። እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባር ላይ ማዋልህ ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳህ እንዴት ነው? እያንዳንዱ ክርስቲያን የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት የራሱን ውሳኔ ሊያደርግ ይገባል። የአልኮል መጠጥ የሚጠጡ ክርስቲያኖችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ላለመጠጣት ሊወስኑ ይችላሉ 5. ምን ያህል እንደምትጠጣ ወስን የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ከወሰንክ ይህን ማስታወስ ይኖርብሃል፦ ይሖዋ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ባያወግዝም ከልክ በላይ መጠጣትን ያወግዛል። ለምን? ሆሴዕ 4:11, 18ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦ ከልክ በላይ መጠጣት ምን ጉዳት ያስከትላል? ከልክ በላይ እንዳንጠጣ ምን ይረዳናል? ልካችንን ወይም ገደባችንን ማወቅ ይኖርብናል። ምሳሌ 11:2ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦ በምትጠጣው መጠን ላይ ገደብ ማስቀመጥህ ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው? 6. ከልክ በላይ የመጠጣት ልማድን ማሸነፍ ከልክ በላይ ይጠጣ የነበረ አንድ ሰው ይህን ልማድ እንዲያሸንፍ የረዳው ምንድን ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦ ቪዲዮ፦ ‘በሕይወቴ ተመረርኩ’ (6:32) በቪዲዮው ላይ ዲሚትሪ የአልኮል መጠጥ ሲጠጣ ምን ዓይነት ጠባይ ያሳይ ነበር? የመጠጥ ሱሱን ወዲያው ማሸነፍ ችሏል? በመጨረሻም ከአልኮል መጠጥ ሱስ መላቀቅ የቻለው እንዴት ነው? አንደኛ ቆሮንቶስ 6:10, 11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦ ስካር እንደ ቀላል የሚታይ ጉዳይ ነው? ከልክ በላይ የአልኮል መጠጥ ይጠጣ የነበረ ሰው ሊለወጥ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? ማቴዎስ 5:30ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦ ‘እጅን መቁረጥ’ የሚለው አገላለጽ ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ መሥዋዕትነት መክፈልን ያመለክታል። የመጠጥ ሱስን ለማሸነፍ እየታገልክ ከሆነ ምን ማድረግህ ይረዳሃል? a አንደኛ ቆሮንቶስ 15:33ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦ ብዙ ከሚጠጡ ሰዎች ጋር ጓደኛ መሆንህ ምን ጉዳት ይኖረዋል? አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስህተት ነው?” ምን ብለህ ትመልሳለህ? ማጠቃለያ የአልኮል መጠጥ ይሖዋ ደስታ እንድናገኝ ሲል ከሰጠን ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው፤ ሆኖም ይሖዋ ከልክ በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። ክለሳ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ ምን ይላል? ከልክ በላይ መጠጣት ምን ጉዳት ያስከትላል? ሌሎች ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ምርጫ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ምዕራፉ የተጠናቀቀበት ቀን፦ ግብ የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ከወሰንክ፣ ግምት ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸውን ጉዳዮች በጥንቃቄ አመዛዝን፤ እንዲሁም በምትጠጣው መጠን ላይ ገደብ አውጣ። ሌላ፦ ሌላ ግብ ምርምር አድርግ ወጣቶች ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? መጠጣት የሚያስከትለውን መዘዝ አስብ (2:31) a የአልኮል መጠጥ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ከሱሳቸው ለመላቀቅ የባለሙያ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ብዙ ሐኪሞች የመጠጥ ችግር የነበረባቸው ሰዎች ጨርሶ ባይጠጡ የተሻለ እንደሆነ ይመክራሉ። ተመለስ ቀጥል አትም አጋራ አጋራ ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? https://cms-imgp.jw-cdn.org/img/p/1102021243/univ/art/1102021243_univ_sqr_xl.jpg lff ትምህርት 43