ምዕራፍ 59

ስደትን በጽናት መቋቋም ትችላለህ

ስደትን በጽናት መቋቋም ትችላለህ
ጽሑፉን አሳይ ጽሑፉን ደብቅ

የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች ተቃውሞ አልፎ ተርፎም ስደት ያጋጥማቸዋል። ታዲያ ይህ ሊያስደነግጠን ይገባል?

1. ስደት እንደሚደርስብን የምንጠብቀው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ኢየሱስ የሰይጣን ዓለም ክፍል ስላልነበር ስደት ደርሶበታል። እኛም የዓለም ክፍል ስላልሆንን መንግሥታትና የሃይማኖት ድርጅቶች ስደት ቢያደርሱብን አይገርመንም።—ዮሐንስ 15:18, 19

2. ለስደት አስቀድመን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

ከወዲሁ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ያስፈልገናል። በየዕለቱ ወደ ይሖዋ የምትጸልይበትና ቃሉን የምታነብበት ጊዜ መድብ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ተገኝ። እነዚህን ነገሮች ማድረግህ የቤተሰብ ተቃውሞን ጨምሮ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ዓይነት ስደት በድፍረት ለመቋቋም ብርታት ይሰጥሃል። በተደጋጋሚ ስደት የደረሰበት ሐዋርያው ጳውሎስ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 13:6

አዘውትረን መስበካችንም ድፍረት ለማዳበር ይረዳናል። የስብከቱ ሥራ በይሖዋ እንድንታመንና የሰው ፍርሃትን እንድናሸንፍ ያሠለጥነናል። (ምሳሌ 29:25) ለመስበክ የሚያስፈልግህን ድፍረት ከወዲሁ ካዳበርክ መንግሥት በሥራችን ላይ እገዳ በሚጥልበት ጊዜም መስበክህን ለመቀጠል ዝግጁ ትሆናለህ።—1 ተሰሎንቄ 2:2

3. ስደትን በጽናት መቋቋማችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

እርግጥ ነው፣ ስደት በራሱ የሚያስደስት ነገር አይደለም፤ ሆኖም ስደትን በተሳካ ሁኔታ ስንወጣ እምነታችን ይበልጥ ይጠናከራል። ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነ በሚሰማን ጊዜ የይሖዋን እርዳታ ማየት ስለምንችል ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን። (ያዕቆብ 1:2-4⁠ን አንብብ።) ይሖዋ መከራ ሲደርስብን ሲያይ የሚያዝን ቢሆንም በጽናት መወጣታችን ያስደስተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ነገር በማድረጋችሁ መከራ ሲደርስባችሁ ችላችሁ ብታሳልፉ . . . ይህ አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:20) ይሖዋ በታማኝነት የሚጸኑ አገልጋዮቹን በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ በማድረግ ይክሳቸዋል፤ በዚያን ጊዜ እውነተኛውን አምልኮ የሚቃወም ማንም አይኖርም።—ማቴዎስ 24:13

ጠለቅ ያለ ጥናት

ስደት ቢደርስብህም ለይሖዋ ታማኝ መሆን ትችላለህ የምንልበትን ምክንያትና እንዲህ ማድረግህ የሚያስገኝልህን በረከት እንመለከታለን።

4. ከቤተሰብህ የሚደርስብህን ተቃውሞ መቋቋም ትችላለህ

ኢየሱስ በግልጽ እንደተናገረው ቤተሰባችን ይሖዋን ለማገልገል ያደረግነውን ውሳኔ ሊቃወም ይችላል። ማቴዎስ 10:34-36ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • አንድ ሰው ይሖዋን ለማገልገል ሲወስን ከቤተሰቡ ምን ሊያጋጥመው ይችላል?

ምሳሌ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • የቤተሰብህ አባል ወይም ጓደኛህ ይሖዋን ለማገልገል ያደረግከውን ውሳኔ ቢቃወም ምን ታደርጋለህ?

መዝሙር 27:10ን እና ማርቆስ 10:29, 30ን አንብቡ፤ እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ከቤተሰቦችህ ወይም ከጓደኞችህ ተቃውሞ ሲያጋጥምህ የሚረዳህ እንዴት ነው?

5. ስደት ቢኖርም ይሖዋን ማገልገልህን ቀጥል

ተቃውሞ እያለም ይሖዋን ማገልገል ድፍረት ይጠይቃል። ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በዚህ ቪዲዮ ላይ ከተጠቀሱት ወንድሞችና እህቶች ምሳሌ ምን ማበረታቻ አግኝተሃል?

የሐዋርያት ሥራ 5:27-29ን እና ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብቡ። እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በስብከቱ ሥራችን ወይም በስብሰባዎቻችን ላይ እገዳ ቢጣልም እንኳ በእነዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላችንን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

6. ይሖዋ መጽናት እንድትችል ይረዳሃል

በዓለም ዙሪያ ያሉ በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስደት ቢደርስባቸውም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ምን እንደረዳቸው ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በቪዲዮው ላይ የታዩትን ወንድሞችና እህቶች እንዲጸኑ የረዳቸው ምንድን ነው?

ሮም 8:35, 37-39ን እንዲሁም ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብቡ። እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ይህ ጥቅስ ማንኛውንም ፈተና በጽናት መቋቋም እንደምትችል እርግጠኛ እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት ነው?

ማቴዎስ 5:10-12ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ስደት ቢደርስብህም ደስተኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች ተቃውሞን በጽናት ተቋቁመዋል። አንተም መቋቋም ትችላለህ!

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ስደትን መቋቋም ይከብደኛል።”

  • እነዚህ ሰዎች ስደትን በጽናት መቋቋም እንደሚችሉ እርግጠኛ እንዲሆኑ ለመርዳት የትኞቹን ጥቅሶች ልትጠቀም ትችላለህ?

ማጠቃለያ

ይሖዋ ስደትን ተቋቁመን እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። በእሱ እርዳታ ጸንተን መቀጠል እንችላለን!

ክለሳ

  • ክርስቲያኖች ስደት እንደሚደርስባቸው መጠበቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?

  • ከወዲሁ ራስህን ለስደት ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

  • ማንኛውም ፈተና ቢያጋጥምህ ይሖዋን ማገልገልህን መቀጠል እንደምትችል እርግጠኛ እንድትሆን የሚረዳህ ምንድን ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

አንድ ወጣት ወንድም ገለልተኛ በመሆኑ ምክንያት በታሰረበት ወቅት ይሖዋ የረዳው እንዴት ነው?

ስደትን በጽናት መቋቋም (2:34)

አንድ ባልና ሚስት ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት እንዲያገለግሉ የረዳቸው ምንድን ነው?

የተለያዩ ለውጦች ቢያጋጥሙም ይሖዋን ማገልገል (7:15)