ሆሴዕ 13:1-16
13 “ኤፍሬም በተናገረ ጊዜ ሰዎች ተንቀጠቀጡ፤በእስራኤል ነገዶች መካከል ትልቅ ቦታ ነበረው።+
ሆኖም ባአልን በማምለክ በደል በመፈጸሙ+ ሞተ።
2 አሁንም ተጨማሪ ኃጢአት ይሠራሉ፤በብራቸውም ለራሳቸው የብረት ምስሎች* ይሠራሉ፤+በጥበብ ጣዖቶችን ያበጃሉ፤ ሁሉም የእጅ ጥበብ ባለሙያ የሠራቸው ናቸው።
‘መሥዋዕት የሚያቀርቡት ሰዎች ጥጃዎቹን ይሳሙ’+ በማለት ለእነሱ ይናገራሉ።
3 ስለዚህ እንደ ማለዳ ጉም፣ወዲያው እንደሚጠፋም ጤዛ ይሆናሉ፤አውሎ ነፋስ ከአውድማ ላይ ጠራርጎ እንደሚወስደው እብቅ፣በጭስ ማውጫም በኩል እንደሚወጣ ጭስ ይሆናሉ።
4 ይሁንና ከግብፅ ምድር አንስቶ እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ፤+ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም ነበር፤ከእኔም ሌላ አዳኝ የለም።+
5 እኔ በምድረ በዳ፣ ድርቅ ባለበትም ምድር ተንከባከብኩህ።+
6 በግጦሽ መሬታቸው ላይ ከበሉ በኋላ ጠገቡ፤+በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ።
ከዚህም የተነሳ ረሱኝ።+
7 ስለዚህ እንደ አንበሳ፣+በመንገድም ዳር እንደሚያደባ ነብር እሆንባቸዋለሁ።
8 ግልገሎቿን እንደተነጠቀች ድብ ሆኜ እመጣባቸዋለሁ፤ደረታቸውንም እዘነጥላለሁ።
በዚያ እንደ አንበሳ እውጣቸዋለሁ፤የዱር አውሬ ይቦጫጭቃቸዋል።
9 እስራኤል ሆይ፣ በእኔ ላይ ስለተነሳህ፣ረዳትህንም ስለተቃወምክ ያጠፋሃል።
10 ‘ንጉሥና መኳንንት ስጠኝ’ ብለህ ነበር፤ታዲያ በከተሞችህ ሁሉ ያድንህ ዘንድ+ንጉሥህ የት አለ? ገዢዎችህስ* የት አሉ?+
11 እኔም ተቆጥቼ ንጉሥ ሰጠሁህ፤+በታላቅ ቁጣዬም አስወግደዋለሁ።+
12 የኤፍሬም በደል ታሽጎ ተቀምጧል፤*ኃጢአቱም ተከማችቷል።
13 ምጥ እንደያዛት ሴት ይሆናል።
እሱ ግን ጥበበኛ ልጅ አይደለም፤የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ በቦታው ላይ አይገኝም።
14 ከመቃብር* እጅ እዋጃቸዋለሁ፤ከሞትም እታደጋቸዋለሁ።+
ሞት ሆይ፣ መንደፊያህ የት አለ?+
መቃብር ሆይ፣ አጥፊነትህ የት አለ?+
ርኅራኄ ከዓይኔ ፊት ይሰወራል።
15 በቄጠማዎች መካከል ተመችቶት ቢያድግ እንኳየምሥራቅ ነፋስ ይኸውም የይሖዋ ነፋስ ይመጣል፤የውኃ ጉድጓዱ እንዲደርቅ፣ ምንጩም እንዲነጥፍ ለማድረግ ከበረሃ ይመጣል።
ውድ የሆኑ ንብረቶቹ ሁሉ የሚገኙበትን ግምጃ ቤቱን ይበዘብዛል።+
16 ሰማርያ በአምላኳ ላይ ስላመፀች+ ተጠያቂ ትሆናለች።+
በሰይፍ ይወድቃሉ፤+ልጆቻቸው ይፈጠፈጣሉ፤የእርጉዝ ሴቶቻቸውም ሆድ ይቀደዳል።”
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “ቀልጠው የተሠሩ ሐውልቶች።”
^ ቃል በቃል “ፈራጆችህስ።”
^ ወይም “ተጠብቋል።”
^ ወይም “ከሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።