የሉቃስ ወንጌል 11:1-54

  • ጸሎትን በተመለከተ የተሰጠ ትምህርት (1-13)

    • የጸሎት ናሙና (2-4)

  • ኢየሱስ በአምላክ ኃይል አጋንንትን አስወጣ (14-23)

  • ሰባት ርኩሳን መናፍስት ይዞ ይመጣል (24-26)

  • እውነተኛ ደስታ (27, 28)

  • የዮናስ ምልክት (29-32)

  • የሰውነት መብራት (33-36)

  • ግብዝ ለሆኑት የሃይማኖት መሪዎች የተነገረ ወዮታ (37-54)

11  አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ እየጸለየ ነበር፤ ጸሎቱንም ሲጨርስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “ጌታ ሆይ፣ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው ሁሉ አንተም እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን” አለው።  በመሆኑም እንዲህ አላቸው፦ “በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ በሉ፦ ‘አባት ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።*+ መንግሥትህ ይምጣ።+  የዕለቱን ምግባችንን* ለዕለቱ የሚያስፈልገንን ያህል ስጠን።+  እኛ የበደሉንን* ሁሉ ይቅር ስለምንል+ ኃጢአታችንን ይቅር በለን፤+ ወደ ፈተናም አታግባን።’”+  ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ መካከል አንዱ፣ አንድ ወዳጅ አለው እንበል፤ በእኩለ ሌሊትም ወደ እሱ ሄዶ እንዲህ አለው፦ ‘ወዳጄ ሆይ፣ እባክህ ሦስት ዳቦ አበድረኝ፤  አንድ ወዳጄ ከመንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ነገር አጣሁ።’  ወዳጁ ግን ከውስጥ ሆኖ ‘ባክህ አታስቸግረኝ። በሩ ተቆልፏል፤ ልጆቼም አብረውኝ ተኝተዋል። አሁን ተነስቼ ምንም ነገር ልሰጥህ አልችልም’ ይለዋል።  እላችኋለሁ፣ ወዳጁ ስለሆነ ተነስቶ ባይሰጠው እንኳ ስለ ውትወታው ሲል+ ተነስቶ የፈለገውን ሁሉ ይሰጠዋል።  ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ደጋግማችሁ ለምኑ፣+ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።+ 10  ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤+ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ የሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል። 11  ደግሞስ ከመካከላችሁ ልጁ ዓሣ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ የሚሰጥ አባት ይኖራል?+ 12  ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋል? 13  ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባትማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!”+ 14  ከጊዜ በኋላ፣ ኢየሱስ ዱዳ የሚያደርግ ጋኔን አስወጣ።+ ጋኔኑ ከወጣ በኋላ ዱዳው ሰው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም ተደነቀ።+ 15  ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹ ግን “አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል* ነው” አሉ።+ 16  ሌሎች ደግሞ ሊፈትኑት ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ይጠይቁት ጀመር።+ 17  ኢየሱስም ሐሳባቸውን አውቆ+ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ እንዲሁም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ቤት ይወድቃል። 18  በተመሳሳይም ሰይጣን እርስ በርሱ ከተከፋፈለ መንግሥቱ እንዴት ይቆማል? እናንተ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል እንደሆነ ትናገራላችሁና። 19  እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ የሚያስወጧቸው ታዲያ በማን ነው? ልጆቻችሁ ፈራጆች የሚሆኑባችሁ ለዚህ ነው። 20  ሆኖም አጋንንትን የማስወጣው በአምላክ ጣት+ ከሆነ የአምላክ መንግሥት ሳታስቡት ደርሶባችኋል ማለት ነው።+ 21  አንድ ብርቱ ሰው በደንብ ታጥቆ ቤቱን ከጠበቀ ንብረቱ ምንም አይነካበትም። 22  ይሁን እንጂ ከእሱ ይበልጥ ብርቱ የሆነ ሰው ካጠቃውና ካሸነፈው ተማምኖበት የነበረውን መሣሪያ ሁሉ ይነጥቀዋል፤ ከእሱ የወሰደውንም ለሌሎች ያካፍላል። 23  ከእኔ ጎን ያልቆመ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ሁሉ ይበትናል።+ 24  “ርኩስ መንፈስ ከሰው ሲወጣ የሚያርፍበት ቦታ ፍለጋ ውኃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ የሚያርፍበት ቦታ ሲያጣ ግን ‘ወደለቀቅኩት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል።+ 25  ሲመለስም ቤቱ ጸድቶና አጊጦ ያገኘዋል። 26  ከዚያም ሄዶ ከእሱ የከፉ ሌሎች ሰባት መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውም ይኖሩበታል። በመሆኑም የዚያ ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከቀድሞው የከፋ ይሆንበታል።” 27  ይህን እየተናገረ ሳለ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “አንተን የተሸከመች ማህፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ደስተኞች ናቸው!” አለችው።+ 28  እሱ ግን “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” አለ።+ 29  ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር፦ “ይህ ትውልድ ክፉ ትውልድ ነው፤ ምልክትም ማየት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከዮናስ ምልክት በስተቀር ምንም ምልክት አይሰጠውም።+ 30  ምክንያቱም ዮናስ+ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደሆነ ሁሉ የሰው ልጅም ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። 31  የደቡብ ንግሥት+ የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ስለመጣች በፍርድ ወቅት ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነስታ ትኮንናቸዋለች። ነገር ግን ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።+ 32  የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሐ ስለገቡ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይኮንኑታል።+ ነገር ግን ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። 33  አንድ ሰው መብራት ካበራ በኋላ በሰዋራ ቦታ አያስቀምጠውም ወይም እንቅብ* አይደፋበትም፤+ ከዚህ ይልቅ ወደ ቤት የሚገቡ ሁሉ ብርሃን እንዲያገኙ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። 34  የሰውነት መብራት ዓይን ነው። ዓይንህ በአንድ ነገር ላይ ሲያተኩር* መላ ሰውነትህም ብሩህ * ይሆናል፤ ዓይንህ ምቀኛ* ሲሆን ግን መላ ሰውነትህም ጨለማ ይሆናል።+ 35  ስለዚህ በውስጥህ ያለው ብርሃን፣ ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ። 36  እንግዲህ መላ ሰውነትህ ምንም ጨለማ ሳይኖርበት ብሩህ ከሆነ፣ ልክ ብርሃን እንደሚፈነጥቅልህ መብራት ሁለንተናህ ብሩህ ይሆናል።” 37  ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ አንድ ፈሪሳዊ አብሮት እንዲበላ ጋበዘው። እሱም ወደ ቤቱ ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። 38  ይሁን እንጂ ፈሪሳዊው ኢየሱስ ከምሳ በፊት እጁን እንዳልታጠበ* ባየ ጊዜ ተገረመ።+ 39  ጌታ ግን እንዲህ አለው፦ “እናንተ ፈሪሳውያን ጽዋውንና ሳህኑን ከውጭ በኩል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በስግብግብነትና በክፋት የተሞላ ነው።+ 40  እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁ! የውስጡንስ የሠራው የውጭውን የሠራው አይደለም? 41  ስለዚህ በልባችሁ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ምጽዋት* አድርጋችሁ ስጡ፤ ያን ጊዜ በሁሉም ነገር ንጹሕ ትሆናላችሁ። 42  እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ከኮሰረት፣ ከጤና አዳምና ከሌሎች አትክልቶች ሁሉ አሥራት ትሰጣላችሁ፤+ ነገር ግን የአምላክን ፍትሕና እሱን መውደድን ችላ ትላላችሁ። እርግጥ አሥራት የመስጠት ግዴታ አለባችሁ፤ ሆኖም ሌሎቹን ነገሮች ችላ ማለት አልነበረባችሁም።+ 43  እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ምክንያቱም በምኩራብ ከፊት መቀመጥ፣* በገበያ ቦታ ደግሞ ሰዎች እጅ እንዲነሷችሁ ትፈልጋላችሁ።+ 44  ሰዎች ሳያውቁ በላዩ ላይ የሚሄዱበትን የተሰወረ* መቃብር ስለምትመስሉ ወዮላችሁ!”+ 45  ከሕጉ አዋቂዎችም አንዱ መልሶ “መምህር፣ እንዲህ ስትል እኮ እኛንም መስደብህ ነው” አለው። 46  በዚህ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “እናንተ የሕጉ አዋቂዎችም ወዮላችሁ! ምክንያቱም ለመሸከም የሚከብድ ሸክም በሰው ላይ ትጭናላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ ግን ሸክሙን በጣታችሁ እንኳ አትነኩትም።+ 47  “አባቶቻችሁ የገደሏቸውን ነቢያት መቃብሮች ስለምትሠሩ ወዮላችሁ!+ 48  እንግዲህ እናንተ ለአባቶቻችሁ ሥራ ምሥክሮች ናችሁ፤ ያም ሆኖ የእነሱን ሥራ ትደግፋላችሁ፤ ምክንያቱም እነሱ ነቢያትን ገደሉ፤+ እናንተ ደግሞ መቃብሮቻቸውን ትሠራላችሁ። 49  ስለዚህ የአምላክ ጥበብ እንዲህ አለች፦ ‘ነቢያትንና ሐዋርያትን ወደ እነሱ እልካለሁ፤ እነሱም አንዳንዶቹን ይገድላሉ በአንዳንዶቹም ላይ ስደት ያደርሳሉ፤ 50  በመሆኑም ይህ ትውልድ ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ ጀምሮ ለፈሰሰው የነቢያት ደም ሁሉ ተጠያቂ ነው፤*+ 51  ከአቤል+ አንስቶ በመሠዊያውና በቤቱ* መካከል እስከተገደለው እስከ ዘካርያስ+ ድረስ ለፈሰሰው ደም ተጠያቂ ነው።’ አዎ፣ እላችኋለሁ፣ ይህ ትውልድ ይጠየቅበታል።* 52  “እናንተ የሕጉ አዋቂዎች ወዮላችሁ! ምክንያቱም የእውቀትን ቁልፍ ነጥቃችሁ ወስዳችኋል። እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁም፤ ለመግባት የሚሞክሩትንም ትከለክላላችሁ።”+ 53   ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሲሄድ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ከበው እያጨናነቁት ስለተለያዩ ነገሮች በመጠየቅ ያዋክቡት ጀመር፤ 54  በሚናገረውም ነገር ሊያጠምዱት ያደቡ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በቅድስና ይያዝ።”
ቃል በቃል “ዳቧችንን።”
ቃል በቃል “ዕዳ ያለባቸውን።”
ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው።
እንደ ስንዴ ያሉ የእህል ዓይነቶችን ለመስፈር የሚያገለግል ዕቃ።
ወይም “አጥርቶ የሚያይ ሲሆን።” ቃል በቃል “ቀላል ሲሆን።”
ወይም “በብርሃን የተሞላ።”
ቃል በቃል “መጥፎ፤ ክፉ።”
ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ አለመንጻቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “የምሕረት ስጦታ።” ወይም “ለድሆች ስጦታ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የተሻለውን መቀመጫ መያዝ።”
ወይም “ምንም ምልክት የሌለው።”
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
ወይም “የፈሰሰው የነቢያት ደም ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል።”
ወይም “በቤተ መቅደሱ።”
ወይም “ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል።”