የሉቃስ ወንጌል 18:1-43

  • ዳኛውን የምትነዘንዘው መበለት ምሳሌ (1-8)

  • ፈሪሳዊውና ቀረጥ ሰብሳቢው (9-14)

  • ኢየሱስና ትናንሽ ልጆች (15-17)

  • አንድ ሀብታም አለቃ ያቀረበው ጥያቄ (18-30)

  • ኢየሱስ እንደሚሞት በድጋሚ ተናገረ (31-34)

  • አንድ ዓይነ ስውር ለማኝ ተፈወሰ (35-43)

18  ከዚያም ምንጊዜም ተስፋ ሳይቆርጡ የመጸለይን+ አስፈላጊነት በተመለከተ ለደቀ መዛሙርቱ አንድ ምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤  እንዲህም አላቸው፦ “በአንዲት ከተማ አምላክን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበር።  በዚያች ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፤ በየጊዜው ወደ እሱ እየሄደች ‘ከባላጋራዬ ጋር ለምከራከርበት ጉዳይ ፍረድልኝ’ ትለው ነበር።  ይሁንና ዳኛው ለተወሰነ ጊዜ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፦ ‘ምንም እንኳ አምላክን የማልፈራ፣ ሰውንም የማላከብር ብሆን  ይህች መበለት ሁልጊዜ እየመጣች ስለምታስቸግረኝ ፍትሕ እንድታገኝ አደርጋለሁ፤ አለዚያ በየጊዜው እየመጣች ትነዘንዘኛለች።’”*+  ከዚያም ጌታ እንዲህ አለ፦ “ምንም እንኳ ዳኛው ዓመፀኛ ቢሆንም ምን እንዳለ ልብ በሉ!  ታዲያ አምላክ በትዕግሥት የሚይዛቸውና+ ቀን ከሌት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ+ ፍትሕ እንዲያገኙ አያደርግም?  እላችኋለሁ፣ በቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል። ሆኖም የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ በእርግጥ እምነት* ያገኝ ይሆን?”  በራሳቸው ጽድቅ ለሚታመኑና ሌሎችን በንቀት ዓይን ለሚመለከቱ ደግሞ የሚከተለውን ምሳሌ ተናገረ፦ 10  “ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ አንደኛው ፈሪሳዊ፣ ሌላኛው ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢ ነበር። 11  ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ እንዲህ ሲል ይጸልይ ጀመር፦ ‘አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌላው ሰው ቀማኛ፣ ዓመፀኛ፣ አመንዝራ፣ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ። 12  በሳምንት ሁለቴ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ነገር ሁሉ አሥራት እሰጣለሁ።’+ 13  ቀረጥ ሰብሳቢው ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለማየትም እንኳ አልደፈረም፤ እንዲያውም ‘አምላክ ሆይ፣ ኃጢአተኛ ለሆንኩት ለእኔ ቸርነት አድርግልኝ’* እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።+ 14  እላችኋለሁ፣ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይሄኛው ሰው ይበልጥ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ።+ ምክንያቱም ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ግን ከፍ ይደረጋል።”+ 15  ሰዎችም ኢየሱስ እጁን እንዲጭንባቸው ሕፃናትን ወደ እሱ ያመጡ ጀመር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህን ሲያዩ ገሠጿቸው።+ 16  ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፦ “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነውና።+ 17  እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።”+ 18  ከአይሁዳውያን አለቆችም አንዱ “ጥሩ መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ሲል ጠየቀው።+ 19  ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም።+ 20  ‘አታመንዝር፣+ አትግደል፣+ አትስረቅ፣+ በሐሰት አትመሥክር፣+ አባትህንና እናትህን አክብር’+ የሚሉትን ትእዛዛት ታውቃለህ።” 21  ሰውየውም “እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጠብቅ ኖሬአለሁ” አለ። 22  ኢየሱስ ይህን ከሰማ በኋላ “አሁንም አንድ የሚቀርህ ነገር አለ፤ ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች አከፋፍል፤ በሰማያትም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን” አለው።+ 23  ሰውየው በጣም ሀብታም ስለነበረ ይህን ሲሰማ እጅግ አዘነ።+ 24  ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፦ “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ነው!+ 25  እንዲያውም ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”+ 26  ይህን የሰሙ ሰዎች “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።+ 27  እሱም “በሰዎች ዘንድ የማይቻል፣ በአምላክ ዘንድ ይቻላል” አለ።+ 28  ጴጥሮስ ግን “እነሆ፣ እኛ ያለንን ነገር ትተን ተከትለንሃል” አለ።+ 29  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለአምላክ መንግሥት ሲል ቤትን ወይም ሚስትን ወይም ወንድሞችን ወይም ወላጆችን ወይም ልጆችን የተወ ሁሉ፣+ 30  አሁን በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት* ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።”+ 31  ከዚያም አሥራ ሁለቱን ገለል አድርጎ በመውሰድ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ! ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰውን ልጅ በተመለከተም በነቢያት የተጻፉት ነገሮች ሁሉ ይፈጸማሉ።+ 32  ለምሳሌ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤+ ያፌዙበታል፤+ ያንገላቱታል እንዲሁም ይተፉበታል።+ 33  ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤+ በሦስተኛው ቀን ግን ይነሳል።”+ 34  ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ መካከል አንዱንም አልተረዱም፤ የተናገረው ቃል ተሰውሮባቸው ነበርና፤ የተባለውም ነገር አልገባቸውም። 35  ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ እየተቃረበ ሳለ አንድ ዓይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።+ 36  ዓይነ ስውሩም ብዙ ሕዝብ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ይጠይቅ ጀመር። 37  ሰዎቹም “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው!” ብለው ነገሩት። 38  በዚህ ጊዜ “ኢየሱስ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” ሲል ጮኸ። 39  ከፊት ከፊት የሚሄዱትም ሰዎች ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይበልጥ መጮኹን ቀጠለ። 40  ኢየሱስም ቆመና ሰውየውን ወደ እሱ እንዲያመጡት አዘዘ። ሰውየው ወደ እሱ በቀረበ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ 41  “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” እሱም “ጌታ ሆይ፣ የዓይኔን ብርሃን መልስልኝ” አለው። 42  ስለዚህ ኢየሱስ “የዓይንህ ብርሃን ይመለስልህ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።+ 43  ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤ አምላክን እያመሰገነም ይከተለው ጀመር።+ ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ አምላክን አወደሱ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነዝንዛ ትገድለኛለች።”
ወይም “እንዲህ ያለ እምነት።”
ወይም “ምሕረት አድርግልኝ።”
ወይም “በሚመጣው ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።