የሉቃስ ወንጌል 2:1-52

  • ኢየሱስ ተወለደ (1-7)

  • መላእክት ለእረኞች ተገለጡ (8-20)

  • ግርዘትና የመንጻት ሥርዓት (21-24)

  • ስምዖን ክርስቶስን አየ (25-35)

  • ሐና ስለ ሕፃኑ ተናገረች (36-38)

  • ወደ ናዝሬት ተመለሱ (39, 40)

  • ኢየሱስ በ12 ዓመቱ በቤተ መቅደስ ያከናወነው ነገር (41-52)

2  በዚያ ዘመን፣ አውግስጦስ ቄሳር የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲመዘገብ አዋጅ አወጣ።  (ይህ የመጀመሪያ ምዝገባ የተካሄደው ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዢ በነበረበት ጊዜ ነው።)  ሁሉም ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ።  ዮሴፍም+ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለነበር በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነስቶ በይሁዳ ወዳለች ቤተልሔም+ ተብላ ወደምትጠራ የዳዊት ከተማ ወጣ።  ለመመዝገብ የሄደውም በታጨችለት መሠረት+ ካገባትና የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው+ ከማርያም ጋር ነበር።  በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ።  የበኩር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅም ወለደች፤+ በእንግዶች ማረፊያም፣ ቦታ ስላላገኙ ልጁን በጨርቅ ጠቅልላ በግርግም ውስጥ አስተኛችው።+  በዚያው ክልል፣ ሌሊት* ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ።  በድንገት የይሖዋ* መልአክ መጥቶ በፊታቸው ቆመ፤ የይሖዋም* ክብር በዙሪያቸው አንጸባረቀ፤ እነሱም በታላቅ ፍርሃት ተዋጡ። 10  መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ እነሆ፣ ለሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ ምሥራች እነግራችኋለሁ፤ 11  በዛሬው ዕለት በዳዊት ከተማ+ አዳኝ+ ተወልዶላችኋልና፤ እሱም ጌታ ክርስቶስ ነው።+ 12  ይህም ምልክት ይሁናችሁ፦ አንድ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” 13  በድንገት ብዙ የሰማይ ሠራዊት+ ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ አምላክንም እያመሰገኑ እንዲህ አሉ፦ 14  “በሰማያት ለአምላክ ክብር ይሁን፤ በምድርም አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች ሰላም ይሁን።” 15  መላእክቱም ከእነሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ እረኞቹ እርስ በርሳቸው “አሁኑኑ ወደ ቤተልሔም ሄደን ይሖዋ* በገለጠልን መሠረት በዚያ የተፈጸመውን ነገር ማየት አለብን” ተባባሉ። 16  በፍጥነትም ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኟቸው፤ ሕፃኑም በግርግም ተኝቶ ነበር። 17  ይህን ባዩ ጊዜ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን መልእክት አወሩ። 18  ይህን የሰሙ ሰዎች ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤ 19  ማርያም ግን የሰማቻቸውን ነገሮች በውስጧ ይዛ በልቧ ታሰላስል ነበር።+ 20  እረኞቹም የሰሙትና ያዩት ነገር ሁሉ ልክ እንደተነገራቸው ሆኖ ስላገኙት አምላክን እያከበሩና እያወደሱ ተመለሱ። 21  ከስምንት ቀን በኋላ፣ ሕፃኑ የሚገረዝበት ጊዜ ሲደርስ+ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ።+ 22  በተጨማሪም በሙሴ ሕግ መሠረት+ የሚነጹበት ጊዜ ሲደርስ ሕፃኑን በይሖዋ* ፊት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት መጡ፤ 23  ይህን ያደረጉት “በኩር የሆነ ወንድ ሁሉ* ለይሖዋ* የተቀደሰ መሆን አለበት”+ ተብሎ በይሖዋ* ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት ነው። 24  ደግሞም የይሖዋ* ሕግ በሚያዘው መሠረት “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች”+ መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 25  እነሆም፣ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እሱም አምላክ እስራኤልን የሚያጽናናበትን+ ጊዜ የሚጠባበቅ ጻድቅና ለአምላክ ያደረ ሰው ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም በእሱ ላይ ነበር። 26  በተጨማሪም ይሖዋ* የቀባውን* ሳያይ እንደማይሞት አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። 27  እሱም በዚህ ጊዜ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መጣ፤ ሕጉ ለልጁ* እንዲደረግ በሚያዘው የተለመደ ሥርዓት መሠረት+ ወላጆቹ ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘውት በገቡ ጊዜ 28  ስምዖን ሕፃኑን ተቀብሎ አቀፈውና አምላክን አወደሰ፤ እንዲህም አለ፦ 29  “ሉዓላዊው ጌታ ሆይ፣ በተናገርከው ቃል መሠረት አሁን ባሪያህን በሰላም እንዲያርፍ ታደርገዋለህ፤+ 30  ምክንያቱም ዓይኖቼ ሰዎችን የምታድንበትን መንገድ አይተዋል፤+ 31  ይህም በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤+ 32  ደግሞም ብሔራትን የጋረደውን መሸፈኛ+ የሚገልጥ ብርሃን+ እንዲሁም የሕዝብህ የእስራኤል ክብር ነው።” 33  አባቱና እናቱም ስለ ልጁ በሚነገሩት ነገሮች ይደነቁ ነበር። 34  ስምዖንም እነሱን ከባረካቸው በኋላ እናቱን ማርያምን እንዲህ አላት፦ “እነሆ፣ ይህ ልጅ በእስራኤል ለብዙዎች መውደቅም+ ሆነ መነሳት+ ምክንያት ይሆናል፤ እንዲሁም ብዙዎች የሚቃወሙት ምልክት ይሆናል፤+ 35  ይህም የሚሆነው በብዙዎች ልብ ውስጥ ያለው ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ነው፤ በአንቺም ውስጥ* ትልቅ ሰይፍ ያልፋል።”+ 36  ከአሴር ነገድ፣ የፋኑኤል ልጅ የሆነች ሐና የምትባል ነቢዪት ነበረች። ይህች ሴት በዕድሜ የገፋች ነበረች፤ ካገባች በኋላ* ከባሏ ጋር የኖረችው ለሰባት ዓመት ብቻ ነበር፤ 37  በዚህ ጊዜ 84 ዓመት የሆናት መበለት ነበረች። ሌትና ቀንም በጾምና በምልጃ ቅዱስ አገልግሎት እያቀረበች ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ አትጠፋም ነበር። 38  በዚያን ሰዓትም ቀርባ አምላክን ታመሰግን ጀመር፤ አምላክ ኢየሩሳሌምን ነፃ ያወጣል ብለው ለሚጠባበቁም ሁሉ ስለ ሕፃኑ መናገር ጀመረች።+ 39  የይሖዋ* ሕግ በሚለው መሠረት+ ሁሉንም ነገር ከፈጸሙ በኋላ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ መኖሪያ ከተማቸው ወደ ናዝሬት+ ተመለሱ። 40  ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ እንዲሁም በጥበብ እየተሞላ ሄደ፤ የአምላክም ሞገስ በእሱ ላይ ነበር።+ 41  ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል* ወደ ኢየሩሳሌም የመሄድ ልማድ ነበራቸው።+ 42  ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ እንደተለመደው በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።+ 43  በዓሉ የሚከበርባቸው ቀናት ተጠናቀው መመለስ በጀመሩ ጊዜ ኢየሱስ እዚያው ኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹም ይህን አላስተዋሉም ነበር። 44  አብረዋቸው ከሚጓዙት ሰዎች ጋር ያለ ስለመሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላም ዘመዶቻቸውና የሚያውቋቸው ሰዎች ጋ ይፈልጉት ጀመር። 45  ባጡት ጊዜ ግን ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እሱን ለማግኘትም ብዙ ደከሙ። 46  በመጨረሻም ከሦስት ቀን በኋላ ቤተ መቅደሱ ውስጥ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ሲጠይቃቸው አገኙት። 47  በዚያ የነበሩት ሰዎችም ሁሉ በመረዳት ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው ያዳምጡት ነበር።+ 48  ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም “ልጄ፣ ምነው እንዲህ አደረግከን? እኔና አባትህ እኮ በጣም ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው። 49  እሱ ግን “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” አላቸው።+ 50  እነሱ ግን ምን እያላቸው እንዳለ አልገባቸውም። 51  ከዚያም ኢየሱስ አብሯቸው ወደ ናዝሬት ተመለሰ፤ እንደ ወትሮውም ይገዛላቸው* ነበር።+ እናቱም የተባሉትን ነገሮች ሁሉ በልቧ ትይዝ ነበር።+ 52  ኢየሱስም በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ ሄደ።

የግርጌ ማስታወሻ

ይህ ቃል አራቱን የሌሊት ክፍለ ጊዜያት ያመለክታል። ማር 13:35 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ማህፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ክርስቶስን።”
ይኸውም በኩር ለሆነ ወንድ ልጅ።
ወይም “በነፍስሽም ውስጥ።”
ቃል በቃል “ከድንግልናዋ ጊዜ አንስቶ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ለማለፍ በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ይታዘዛቸው።”