የሉቃስ ወንጌል 21:1-38

  • የድሃዋ መበለት ሁለት ሳንቲሞች (1-4)

  • የወደፊቱ ጊዜ ምልክት (5-36)

    • ጦርነት፣ ታላላቅ የምድር ነውጦች፣ ቸነፈር፣ የምግብ እጥረት (10, 11)

    • ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ትከበባለች (20)

    • “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” (24)

    • የሰው ልጅ መምጣት (27)

    • የበለስ ዛፏ ምሳሌ (29-33)

    • “ነቅታችሁ ጠብቁ” (34-36)

  • ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አስተማረ (37, 38)

21  ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች በመዋጮ ሣጥኖቹ* ውስጥ መባቸውን ሲከቱ አየ።+  ከዚያም አንዲት ድሃ መበለት በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች* ስትከት+ አይቶ  እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።+  ሁሉም መባ የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን መተዳደሪያ ሁሉ ሰጥታለች።”+  በኋላም አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ ውብ በሆኑ ድንጋዮችና ለአምላክ በተሰጡ ስጦታዎች እንዴት እንዳጌጠ+ በተናገሩ ጊዜ  “ይህ የምታዩት ነገር ሁሉ የሚፈርስበት ጊዜ ይመጣል፤ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ አይኖርም” አለ።+  እነሱም “መምህር፣ እነዚህ ነገሮች በእርግጥ የሚፈጸሙት መቼ ነው? እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ የሚጠቁመው ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+  እሱም እንዲህ አለ፦ “እንዳያሳስቷችሁ ተጠንቀቁ፤+ ብዙዎች ‘እኔ እሱ ነኝ’ እንዲሁም ‘ጊዜው ቀርቧል’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና። እነሱን አትከተሉ።+  በተጨማሪም ስለ ጦርነትና ብጥብጥ* ስትሰሙ አትሸበሩ። በመጀመሪያ እነዚህ ነገሮች መፈጸም አለባቸውና፤ ፍጻሜው ግን ወዲያው አይመጣም።”+ 10  ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣+ መንግሥትም በመንግሥት ላይ+ ይነሳል። 11  ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም የምግብ እጥረትና ቸነፈር ይሆናል፤+ ደግሞም የሚያስፈሩ ነገሮች እንዲሁም ከሰማይ ታላላቅ ምልክቶች ይታያሉ። 12  “እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከመፈጸማቸው በፊት ግን ሰዎች ይይዟችኋል፤ ስደት ያደርሱባችኋል+ እንዲሁም ለምኩራብና ለወህኒ ቤት አሳልፈው ይሰጧችኋል። በስሜም ምክንያት በነገሥታትና በገዢዎች ፊት ያቀርቧችኋል።+ 13  ይህም ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትላችኋል። 14  የምትሰጡትን መልስ አስቀድማችሁ መዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ፤+ 15  ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።+ 16  ከዚህም በተጨማሪ ወላጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁ፣ ዘመዶቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንኳ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤* አንዳንዶቻችሁንም ይገድላሉ፤+ 17  በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል።+ 18  ይሁን እንጂ ከራሳችሁ ፀጉር አንዷ እንኳ አትጠፋም።+ 19  ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ።*+ 20  “ይሁንና ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ+ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ።+ 21  በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤+ በከተማዋ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉም ወደ እሷ አይግቡ፤ 22  ምክንያቱም የተጻፈው ነገር ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይህ የፍትሕ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ* ነው። 23  በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!+ ምክንያቱም በምድሪቱ ላይ ታላቅ መከራ፣ በዚህ ሕዝብም ላይ ቁጣ ይመጣል። 24  በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ተማርከውም ወደየአገሩ ይወሰዳሉ፤+ የተወሰኑት የአሕዛብ* ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስም ኢየሩሳሌም በአሕዛብ* ትረገጣለች።+ 25  “እንዲሁም በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክቶች ይታያሉ፤+ በምድርም ላይ ሕዝቦች ከባሕሩ ድምፅና ነውጥ የተነሳ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ። 26  የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ። 27  ከዚያም የሰው ልጅ+ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 28  ሆኖም እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።” 29  ከዚያም እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “የበለስ ዛፍንና ሌሎች ዛፎችን ሁሉ ተመልከቱ።+ 30  ዛፎቹ ሲያቆጠቁጡ ራሳችሁ አይታችሁ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ። 31  በተመሳሳይ እናንተም እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እርግጠኞች ሁኑ። 32  እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።+ 33  ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+ 34  “ይሁንና ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት+ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ+ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት 35  እንደ ወጥመድ+ ይመጣባችኋል። ይህ በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይደርስባቸዋልና። 36  እንግዲያው መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ+ ሁልጊዜ ምልጃ እያቀረባችሁ+ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”+ 37  ኢየሱስ ቀን ቀን በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሲመሽ ግን ወጥቶ ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ያድር ነበር። 38  ሕዝቡም ሁሉ በቤተ መቅደስ እሱን ለመስማት በማለዳ ወደ እሱ ይመጡ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ዕቃዎቹ።”
ቃል በቃል “ሁለት ሌፕተን።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ረብሻ፤ ዓመፅ።”
ወይም “ይከዷችኋል።”
ወይም “ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።”
ወይም “የበቀል ቀን።”
ወይም “የብሔራት።”
ወይም “በብሔራት።”
በጳለስጢና ምድር ዕፀዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።