የሉቃስ ወንጌል 5:1-39
5 አንድ ቀን ኢየሱስ በጌንሴሬጥ ሐይቅ*+ ዳርቻ ቆሞ የአምላክን ቃል ሲያስተምር ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ያዳምጡት ነበር፤ ከዚያም ሰዎቹ እየተገፋፉ ያጨናንቁት ጀመር።
2 በዚህ ጊዜ ሁለት ጀልባዎች በሐይቁ ዳርቻ ቆመው ተመለከተ፤ ዓሣ አጥማጆቹ ግን ከጀልባዎቹ ላይ ወርደው መረቦቻቸውን እያጠቡ ነበር።+
3 ኢየሱስም አንደኛዋ ጀልባ ላይ ወጣ፤ የጀልባዋ ባለቤት የሆነውን ስምዖንንም ከየብስ ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ጠየቀው። ከዚያም ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ጀመር።
4 ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ስምዖንን “ጥልቅ ወደሆነው አካባቢ ፈቀቅ በልና መረቦቻችሁን ጥላችሁ አጥምዱ” አለው።
5 ሆኖም ስምዖን መልሶ “መምህር፣ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም፤+ አንተ ካልክ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው።
6 እንደተባሉት ባደረጉም ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ። እንዲያውም መረቦቻቸው መበጣጠስ ጀመሩ።+
7 በመሆኑም በሌላኛው ጀልባ ላይ የነበሩትን የሥራ ባልደረቦቻቸውን መጥተው እንዲያግዟቸው በምልክት ጠሯቸው፤ እነሱም መጡ፤ ሁለቱንም ጀልባዎች በዓሣ ሞሏቸው፤ ከዚህም የተነሳ ጀልባዎቹ መስጠም ጀመሩ።
8 ስምዖን ጴጥሮስ ይህን ባየ ጊዜ በኢየሱስ እግር ሥር ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ስለሆንኩ ከእኔ ራቅ” አለው።
9 ይህን ያለው እሱና ከእሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ከያዙት ዓሣ ብዛት የተነሳ በጣም ስለተደነቁ ነው፤
10 የስምዖን የሥራ ባልደረቦች የሆኑት የዘብዴዎስ ልጆች+ ያዕቆብና ዮሐንስም በጣም ተደንቀው ነበር። ኢየሱስ ግን ስምዖንን “አይዞህ አትፍራ፤ ከአሁን ጀምሮ ሰውን* የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው።+
11 ስለዚህ ጀልባዎቹን መልሰው ወደ የብስ ካስጠጉ በኋላ ሁሉን ነገር ትተው ተከተሉት።+
12 በሌላ ጊዜ ደግሞ በአንድ ከተማ ውስጥ በነበረበት ጊዜ መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ የወረሰው ሰው በዚያ ነበር። ሰውየውም ኢየሱስን ባየው ጊዜ በግንባሩ ተደፍቶ “ጌታ ሆይ፣ ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ሲል ለመነው።+
13 ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀው።+
14 ከዚያም ኢየሱስ ሰውየውን ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፤ “ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ባዘዘው መሠረት+ ስለ መንጻትህ መባ አቅርብ፤ ካህናቱም ማስረጃውን ይመለከታሉ” አለው።+
15 ሆኖም ስለ እሱ የሚወራው ወሬ ይበልጥ እየተሰራጨ ሄደ፤ በጣም ብዙ ሰዎችም የሚናገረውን ለመስማትና ከበሽታቸው ለመፈወስ ይሰበሰቡ ነበር።+
16 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ጭር ወዳሉ ስፍራዎች በመሄድ ይጸልይ ነበር።
17 አንድ ቀን ኢየሱስ እያስተማረ ሳለ ከገሊላ፣ ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕጉ መምህራን በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ ሰዎችንም ለመፈወስ የሚያስችለው የይሖዋ* ኃይል ከኢየሱስ ጋር ነበር።+
18 በዚያን ጊዜም አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ የተሸከሙ ሰዎች መጡ፤ ሽባውን ወደ ውስጥ ለማስገባትና ኢየሱስ ፊት ለማስቀመጥ ጥረት አደረጉ።+
19 ከሕዝቡም ብዛት የተነሳ መግቢያ ስላላገኙ ጣራው ላይ ወጥተው ጡቡን ካነሱ በኋላ የተኛበትን ቃሬዛ አሾልከው፣ ሽባውን ኢየሱስ ፊት በነበሩት ሰዎች መካከል አወረዱት።
20 ኢየሱስም እምነታቸውን በማየት “አንተ ሰው፣ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።+
21 በዚህ ጊዜ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን “አምላክን የሚዳፈረው ይሄ ማን ነው? ከአምላክ በቀር ኃጢአትን ማን ይቅር ሊል ይችላል?” ይባባሉ ጀመር።+
22 ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በልባችሁ የምታስቡት ምንድን ነው?
23 ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል’ ከማለትና ‘ተነስተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?
24 ይሁንና የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ . . .” አላቸውና ሽባውን “ተነስ፣ ቃሬዛህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።+
25 በዚህ ጊዜ ሰውየው በፊታቸው ተነስቶ ተኝቶበት የነበረውን ቃሬዛ ተሸከመና አምላክን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ።
26 ይህን ሲያዩ ሁሉም በአድናቆት ተውጠው አምላክን ማመስገን ጀመሩ፤ ታላቅ ፍርሃትም አድሮባቸው “ዛሬ የሚያስደንቅ ነገር አየን!” አሉ።
27 ይህ ከሆነም በኋላ ኢየሱስ ወጥቶ ሲሄድ ሌዊ የሚባል ቀረጥ ሰብሳቢ በቀረጥ መሰብሰቢያው ቦታ ተቀምጦ አየና “ተከታዬ ሁን” አለው።+
28 እሱም ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ በመተው ተነስቶ ይከተለው ጀመር።
29 ከዚያም ሌዊ በቤቱ ለኢየሱስ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ በግብዣውም ላይ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ሰዎች ከእነሱ ጋር ይበሉ ነበር።+
30 ፈሪሳውያንና ከእነሱ ወገን የሆኑ ጸሐፍት ይህን ባዩ ጊዜ “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?” በማለት በደቀ መዛሙርቱ ላይ ማጉረምረም ጀመሩ።+
31 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም።+
32 እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አይደለም።”+
33 እነሱም “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አዘውትረው ይጾማሉ፤ እንዲሁም ምልጃ ያቀርባሉ፤ የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትም እንዲሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ፣ ይጠጣሉ” አሉት።+
34 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሽራው ከእነሱ ጋር እያለ የሙሽራው ጓደኞች እንዲጾሙ ልታደርጓቸው ትችላላችሁ?
35 ሆኖም ሙሽራው+ ከእነሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።”+
36 በተጨማሪም እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “ከአዲስ ልብስ ላይ ቁራጭ ጨርቅ ወስዶ በአሮጌ ልብስ ላይ የሚጥፍ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን አዲሱ ቁራጭ ጨርቅ ተቦጭቆ ይነሳል፤ ከአዲሱ ልብስ የተቆረጠው ጨርቅ ከአሮጌው ልብስ ጋር አይስማማም።+
37 ደግሞም ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጥ ሰው የለም። እንዲህ ቢያደርግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁ ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል።
38 ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ መቀመጥ አለበት።
39 አሮጌ የወይን ጠጅ ከጠጣ በኋላ አዲሱን የሚፈልግ የለም፤ ምክንያቱም ‘አሮጌው ግሩም ነው’ ይላል።”