የሉቃስ ወንጌል 8:1-56

  • ኢየሱስን ይከተሉ የነበሩ ሴቶች (1-3)

  • የዘሪው ምሳሌ (4-8)

  • ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመበት ምክንያት (9, 10)

  • የዘሪው ምሳሌ ትርጉም (11-15)

  • መብራት አብርቶ በዕቃ የሚከድን የለም (16-18)

  • የኢየሱስ እናትና ወንድሞች (19-21)

  • ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አሰኘ (22-25)

  • ኢየሱስ አጋንንቱን ወደ አሳማዎች እንዲገቡ ፈቀደላቸው (26-39)

  • የኢያኢሮስ ሴት ልጅ፤ አንዲት ሴት የኢየሱስን ልብስ ነካች (40-56)

8  ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ተጓዘ።+ አሥራ ሁለቱም ከእሱ ጋር ነበሩ፤  በተጨማሪም ከክፉ መናፍስትና ከበሽታ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፦ ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣  የሄሮድስ ቤት አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐና፣+ ሶስና እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሴቶች የነበሩ ሲሆን በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር።+  ኢየሱስም የየከተማው ሕዝብ ተከትሎት በመጣ ጊዜና እጅግ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ወቅት እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ፦+  “አንድ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወድቀው ተረጋገጡ፤ የሰማይ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው።+  አንዳንዶቹ ዓለት ላይ ወደቁ፤ ከበቀሉም በኋላ እርጥበት ስላላገኙ ደረቁ።+  ሌሎቹ ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ አብሯቸው ያደገውም እሾህ አነቃቸው።+  ሌሎቹ ግን ጥሩ አፈር ላይ ወደቁ፤ ከበቀሉም በኋላ 100 እጥፍ አፈሩ።”+ ይህን ከተናገረ በኋላ ድምፁን ከፍ አድርጎ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።+  ደቀ መዛሙርቱ ግን የዚህን ምሳሌ ትርጉም ጠየቁት።+ 10  እሱም እንዲህ አለ፦ “ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥሮች የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤ ለቀሩት ግን በምሳሌ እነግራቸዋለሁ፤+ ይኸውም እያዩ እንዳያስተውሉ እንዲሁም እየሰሙ ትርጉሙን እንዳይረዱ ነው።+ 11  እንግዲህ የምሳሌው ትርጉም ይህ ነው፦ ዘሩ የአምላክ ቃል ነው።+ 12  በመንገድ ዳር የወደቁት ቃሉን የሰሙ ናቸው፤ ከዚያ በኋላ ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።+ 13  በዓለት ላይ የወደቁት ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም። ለጊዜው አምነው ቢቀበሉም በፈተና ወቅት ይወድቃሉ።+ 14  በእሾህ መካከል የወደቁት ቃሉን የሰሙ ናቸው፤ ሆኖም በዚህ ዓለም የኑሮ ጭንቀት፣ ሀብትና+ ሥጋዊ ደስታ+ ትኩረታቸው ተከፋፍሎ ሙሉ በሙሉ ይታነቃሉ፤ ለፍሬም አይበቁም።+ 15  በጥሩ አፈር ላይ የወደቁት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በጥሩ ልብ+ ሰምተው በውስጣቸው በማኖር በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።+ 16  “መብራት አብርቶ ዕቃ የሚከድንበት ወይም አልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ሰው የለም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ቤት የሚገቡ ሁሉ ብርሃን እንዲያገኙ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል።+ 17  በመሆኑም ተሸሽጎ የማይገለጥ፣ በሚገባ ቢሰወርም የማይታወቅና ይፋ የማይወጣ ነገር የለም።+ 18  ስለዚህ እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ፤ ላለው ተጨማሪ ይሰጠዋልና፤+ የሌለው ግን እንዳለው አድርጎ የሚያስበው ነገር እንኳ ይወሰድበታል።”+ 19  ከዚህ በኋላ እናቱና ወንድሞቹ+ እሱ ወዳለበት መጡ፤ ሆኖም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ወደ እሱ ሊቀርቡ አልቻሉም።+ 20  ስለዚህ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያገኙህ ፈልገው ውጭ ቆመዋል” ተብሎ ተነገረው። 21  እሱም መልሶ “እናቴና ወንድሞቼ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው” አላቸው።+ 22  አንድ ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጀልባ ከተሳፈረ በኋላ “ወደ ሐይቁ ማዶ እንሻገር” አላቸው። በመሆኑም ጉዞ ጀመሩ።+ 23  እየተጓዙም ሳሉ ኢየሱስ እንቅልፍ ወሰደው። በዚህ ጊዜ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በሐይቁ ላይ ተነሳ፤ ጀልባቸውም በውኃ መሞላት ስለጀመረች አደጋ ላይ ወደቁ።+ 24  ስለዚህ ሄደው ቀሰቀሱትና “መምህር፣ መምህር ማለቃችን እኮ ነው!” አሉት። እሱም ከእንቅልፉ ነቅቶ ነፋሱንና የሚናወጠውን ውኃ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱ ቆመ፤ ጸጥታም ሰፈነ።+ 25  ከዚያም “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። እነሱ ግን በፍርሃት ተውጠውና በጣም ተደንቀው እርስ በርሳቸው “ለመሆኑ ይህ ማን ነው? ነፋስና ውኃ እንኳ ይታዘዙለታል” ተባባሉ።+ 26  ከዚያም በገሊላ ማዶ ወደሚገኘው ጌርጌሴኖን+ ወደተባለው ክልል የባሕር ዳርቻ ደረሱ። 27  ኢየሱስ ከጀልባዋ ወደ የብስ በወረደ ጊዜ አጋንንት ያደሩበት በአቅራቢያው በሚገኝ ከተማ የሚኖር አንድ ሰው አገኘው። ይህ ሰው ልብስ መልበስ ከተወ ብዙ ጊዜ ሆኖት ነበር፤ የሚኖረውም በቤት ውስጥ ሳይሆን በመቃብር ስፍራ ነበር።+ 28  ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ በፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም “የልዑል አምላክ ልጅ ኢየሱስ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ።+ 29  (ይህን ያለውም ኢየሱስ ርኩሱ መንፈስ ከሰውየው እንዲወጣ እያዘዘው ስለነበረ ነው። ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን ብዙ ጊዜ ይይዘው ነበር፤*+ ሰውየው በተደጋጋሚ በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም የታሰረበትን ሰንሰለት ይበጣጥስ ነበር፤ ጋኔኑም ጭር ወዳሉ ቦታዎች ይነዳው ነበር።) 30  ኢየሱስ “ስምህ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። እሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለነበር “ሌጌዎን” አለው። 31  አጋንንቱም ወደ ጥልቁ እንዲሄዱ እንዳያዛቸው ተማጸኑት።+ 32  በዚያም በተራራው ላይ ብዛት ያለው የአሳማ+ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ ስለዚህ ወደ አሳማዎቹ ይገቡ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ተማጸኑት፤ እሱም ፈቀደላቸው።+ 33  በዚህ ጊዜ አጋንንቱ ከሰውየው ወጥተው አሳማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ የአሳማውም መንጋ ከገደሉ አፋፍ* እየተንደረደረ በመውረድ ሐይቁ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ። 34  እረኞቹ ግን የሆነውን ነገር ሲያዩ ሸሽተው በመሄድ ወሬውን በከተማውና በገጠሩ አዳረሱ። 35  በዚህ ጊዜ ሕዝቡ የሆነውን ነገር ለማየት ወጡ። ወደ ኢየሱስ ሲመጡም አጋንንት የወጡለት ሰው ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት ኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጦ አገኙት፤ በዚህ ጊዜ ፍርሃት አደረባቸው። 36  የተፈጸመውን ነገር ያዩ ሰዎች አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው እንዴት ጤናማ ሊሆን እንደቻለ አወሩላቸው። 37  በዚህ ጊዜ ከጌርጌሴኖን ክልል የመጡት ሰዎች በሙሉ ታላቅ ፍርሃት ስላደረባቸው ኢየሱስን ከዚያ እንዲሄድላቸው ለመኑት። እሱም ከዚያ ለመሄድ ጀልባዋ ላይ ተሳፈረ። 38  አጋንንት የወጡለት ሰው ግን አብሮት ይሆን ዘንድ ደጋግሞ ለመነው፤ ሆኖም ኢየሱስ ሰውየውን እንዲህ ሲል አሰናበተው፦+ 39  “ወደ ቤትህ ተመለስ፤ አምላክ ያደረገልህንም ነገር ተናገር።” ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር በከተማው ሁሉ እያወጀ ሄደ። 40  ሕዝቡ እየጠበቁት ስለነበር ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ ሁሉም በደስታ ተቀበሉት።+ 41  በዚህ ጊዜ ኢያኢሮስ የሚባል አንድ የምኩራብ አለቃ መጣ። ኢየሱስ እግር ላይም ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ይማጸነው ጀመር፤+ 42  ይህን ያደረገው 12 ዓመት ገደማ የሆናት አንዲት ልጁ ልትሞት ተቃርባ ስለነበር ነው። ኢየሱስ እየተጓዘ ሳለ ሕዝቡ እየተጋፋ ያጨናንቀው ነበር። 43  በዚያም፣ ለ12 ዓመት ደም ሲፈስሳት+ የኖረች አንዲት ሴት የነበረች ሲሆን ይህችን ሴት ሊፈውሳት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።+ 44  ከኋላም መጥታ የልብሱን ዘርፍ ነካች፤+ ይፈሳት የነበረውም ደም ወዲያውኑ ቆመ። 45  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “የነካኝ ማን ነው?” አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፣ ጴጥሮስ “መምህር፣ ሕዝቡ ከቦህ እየተጋፋህ ነው የሚሄደው” አለው።+ 46  ኢየሱስ ግን “ኃይል+ ከእኔ እንደወጣ ስለታወቀኝ አንድ ሰው ነክቶኛል” አለ። 47  ሴትየዋም ሳይታወቅባት መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ከዚያም ለምን እንደነካችውና እንዴት ወዲያውኑ እንደተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። 48  እሱ ግን “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ” አላት።+ 49  ገና እየተናገረ ሳለ ከምኩራብ አለቃው ቤት የተላከ አንድ ሰው መጥቶ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታስቸግረው” አለው።+ 50  ኢየሱስ ይህን ሲሰማ “አትፍራ፤ ብቻ እመን፤ ልጅህ ትድናለች” አለው።+ 51  ወደ ኢያኢሮስ ቤት በደረሰ ጊዜ ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቷ አባትና እናት በስተቀር ማንም አብሮት ወደ ውስጥ እንዲገባ አልፈቀደም። 52  በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ ለልጅቷ እያለቀሱና በሐዘን ደረታቸውን እየደቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ “በቃ አታልቅሱ፤+ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም”+ አላቸው። 53   ይህን ሲሰሙ ልጅቷ እንደሞተች ያውቁ ስለነበር በማፌዝ ይስቁበት ጀመር። 54  እሱ ግን እጇን በመያዝ ድምፁን ከፍ አድርጎ “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” አለ።+ 55  የልጅቷም መንፈስ*+ ተመለሰ፤ ወዲያውም ተነሳች፤+ የምትበላውም ነገር እንዲሰጧት አዘዘ። 56  ወላጆቿም የሚሆኑት ጠፋቸው፤ እሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።+

የግርጌ ማስታወሻ

“ለረጅም ጊዜ ይዞት ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ገደላማ ከሆነው የባሕሩ ዳርቻ።”
ወይም “የሕይወት ኃይል።”