ሕዝቅኤል 21:1-32
21 የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦
2 “የሰው ልጅ ሆይ፣ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አዙረህ ቅዱስ በሆኑት ስፍራዎች ላይ አውጅ፤ በእስራኤልም ምድር ላይ ትንቢት ተናገር።
3 ለእስራኤል ምድር እንዲህ በል፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በአንቺ ላይ ተነስቻለሁ፤ ሰይፌንም ከሰገባው መዝዤ+ ጻድቁንም ሆነ ክፉውን ከአንቺ አስወግዳለሁ።
4 ጻድቁንም ሆነ ክፉውን ከአንቺ ስለማስወግድ ሰይፌ ከደቡብ እስከ ሰሜን ድረስ በሥጋ ለባሽ* ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል።
5 ሰዎች ሁሉ ሰይፌን ከሰገባው የመዘዝኩት እኔ ይሖዋ ራሴ እንደሆንኩ ያውቃሉ። ዳግመኛ ወደ ሰገባው አይመለስም።”’+
6 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ እየተንቀጠቀጥክ* አቃስት፤ አዎ፣ በፊታቸው በምሬት አቃስት።+
7 ‘የምታቃስተው ለምንድን ነው?’ ቢሉህ ‘ከሰማሁት ወሬ የተነሳ ነው’ ትላለህ። በእርግጥ ይመጣልና፤ ልብም ሁሉ በፍርሃት ይቀልጣል፤ እጅ ሁሉ ይዝላል፤ መንፈስ ሁሉ ያዝናል፤ ጉልበትም ሁሉ በውኃ ይርሳል።*+ ‘እነሆ፣ በእርግጥ ይመጣል! ደግሞም ይፈጸማል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”
8 የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦
9 “የሰው ልጅ ሆይ፣ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “‘ሰይፍ! ሰይፍ+ ተስሏል፤ ደግሞም ተወልውሏል።
10 የተሳለው ታላቅ እልቂት ለማስከተል ነው፤ የተወለወለውም እንደ መብረቅ እንዲያበራ ነው’ በል።”’”
“ታዲያ ደስ ሊለን አይገባም?”
“‘ማንኛውንም ዛፍ እንደሚንቅ* ሁሉ የገዛ ልጄን በትረ መንግሥት+ ይንቃል?
11 “‘እንዲወለወልና በእጅ እንዲያዝ ተሰጥቷል። ገዳዩ በእጁ እንዲይዘው ይህ ሰይፍ ተስሏል፤ ደግሞም ተወልውሏል።+
12 “‘የሰው ልጅ ሆይ፣ ሰይፍ በሕዝቤ ላይ ስለመጣ ጩኽ፤ ደግሞም ዋይ ዋይ በል፤+ በእስራኤል አለቆች ሁሉ ላይ ተነስቷል።+ እነዚህ ሰዎች ከሕዝቤ ጋር በአንድ ላይ የሰይፍ ሰለባ ይሆናሉ። ስለዚህ ጭንህን በሐዘን ምታ።
13 ሰይፉ ተፈትሿልና፤+ ደግሞስ በትረ መንግሥቱን ከናቀው ምን ይሆናል? ከሕልውና ውጭ ይሆናል’*+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።
14 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ ትንቢት ተናገር፤ በእጅህም አጨብጭብ፤ ደግሞም ‘ሰይፍ!’ የሚለውን ቃል ሦስት ጊዜ ደጋግመህ ተናገር። ሰለባዎቹን የሚገድልና ታላቅ እልቂት የሚያስከትል፣ እነሱን የሚከብ ሰይፍ ነው።+
15 ልባቸው በፍርሃት ይቀልጣል፤+ ብዙዎችም በከተሞቻቸው በር ላይ ይወድቃሉ፤ እኔም በሰይፉ እገድላለሁ። አዎ፣ ሰይፉ እንደ መብረቅ ያበራል፤ ለመግደልም ተወልውሏል!
16 በስተ ቀኝ በኩል በኃይል ቁረጥ! በስተ ግራ በኩል ተንቀሳቀስ! ስለትህ በዞረበት አቅጣጫ ሁሉ ሂድ!
17 እኔም በእጄ አጨበጭባለሁ፤ ቁጣዬንም አበርዳለሁ።+ እኔ ይሖዋ ራሴ ይህን ተናግሬአለሁ።”
18 የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦
19 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የሚመጣባቸውን ሁለት መንገዶች ንድፍ አውጣ። ሁለቱም መንገዶች የሚነሱት ከአንድ ምድር ነው፤ መንገዱ ወደ ሁለቱ ከተሞች የሚገነጠልበት ቦታ ላይ ምልክት አድርግ።
20 ሰይፍ በአሞናውያን ከተማ በራባ+ ላይ ይመጣ ዘንድ አንደኛውን መንገድ አመልክት፤ እንዲሁም በይሁዳ በምትገኘው በተመሸገችው ኢየሩሳሌም+ ላይ ይመጣ ዘንድ ሌላኛውን መንገድ አመልክት።
21 የባቢሎን ንጉሥ ያሟርት ዘንድ በመንታ መንገድ ይኸውም በሁለቱ መንገዶች መገንጠያ ላይ ይቆማልና። ፍላጾችን ይወዘውዛል። ጣዖቶቹን* ያማክራል፤ ጉበት ይመረምራል።
22 በቀኝ እጁ የወጣው ሟርት የመደርመሻ መሣሪያዎችን ለመደገን፣ የግድያ ትእዛዝ ለማስተላለፍ፣ የጦርነት ሁካታ ለማሰማት፣ በበሮቿ ላይ የመደርመሻ መሣሪያዎች ለመደገን፣ በዙሪያዋ የአፈር ቁልል ለመደልደልና ለከበባ የሚያገለግል ግንብ ለመሥራት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ አመለከተው።+
23 ቃለ መሐላዎች የገቡላቸው ሰዎች* ግን ይህ የሐሰት ሟርት ይመስላቸዋል።+ ይሁንና እሱ በደላቸውን በማስታወስ ማርኮ ይወስዳቸዋል።+
24 “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በምትፈጽሙት ድርጊት ሁሉ መተላለፋችሁ እንዲገለጥና ኃጢአታችሁ እንዲታይ በማድረግ በደላችሁ እንዲታሰብ አድርጋችኋል። እናንተም አሁን ስለታሰባችሁ በኃይል* ትወሰዳላችሁ።’
25 “አንተ ክፉኛ የቆሰልከው፣ መጥፎው የእስራኤል አለቃ፣+ ቀንህ ይኸውም የመጨረሻ ቅጣት የምትቀበልበት ጊዜ ደርሷል።
26 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ጥምጥሙን ፍታ፤ አክሊሉንም አንሳ።+ ይህ እንደ በፊቱ አይሆንም።+ ዝቅ ያለውን ከፍ አድርግ፤+ ከፍ ያለውን ደግሞ ዝቅ አድርግ።+
27 ባድማ፣ ባድማ፣ ባድማ አደርጋታለሁ። እሷም ሕጋዊ መብት ያለው እስኪመጣ ድረስ+ ለማንም አትሆንም፤ ለእሱም እሰጣታለሁ።’+
28 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ስለ አሞናውያንና ስለ ስድባቸው እንዲህ ይላል።’ እንዲህ በል፦ ‘ሰይፍ! ሰይፍ ለግድያ ተመዟል፤ እንዲበላና እንደ መብረቅ እንዲያበራ ተወልውሏል።
29 ስለ ራስሽ የሐሰት ራእዮች ያየሽና የውሸት ሟርት ያሟረትሽ ቢሆንም ቀናቸው፣ የመጨረሻ ቅጣት የሚቀበሉበት ጊዜ በደረሰባቸው ክፉዎች ማለትም በሚገደሉት ሰዎች* ላይ ትከመሪያለሽ።
30 ሰይፉ ወደ ሰገባው ይመለስ። በተፈጠርሽበት ስፍራ፣ በተገኘሽበትም ምድር እፈርድብሻለሁ።
31 ቁጣዬን በአንቺ ላይ አወርዳለሁ። የታላቅ ቁጣዬን እሳት በላይሽ ላይ አነዳለሁ፤ በማጥፋትም ለተካኑ ጨካኝ ሰዎች አሳልፌ እሰጥሻለሁ።+
32 ለእሳት ማገዶ ትሆኛለሽ፤+ የገዛ ደምሽ በምድሪቱ ላይ ይፈስሳል፤ ደግሞም ከእንግዲህ ወዲህ አትታወሺም፤ እኔ ይሖዋ ራሴ ይህን ተናግሬአለሁና።’”