ሕዝቅኤል 25:1-17

  • በአሞን ላይ የተነገረ ትንቢት (1-7)

  • በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት (8-11)

  • በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት (12-14)

  • በፍልስጤም ላይ የተነገረ ትንቢት (15-17)

25  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ፊትህን ወደ አሞናውያን+ አዙረህ በእነሱ ላይ ትንቢት ተናገር።+  አሞናውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የሉዓላዊውን ጌታ የይሖዋን ቃል ስሙ። ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “መቅደሴ በረከሰ ጊዜና የእስራኤል ምድር ባድማ በሆነ ጊዜ እንዲሁም የይሁዳ ቤት ሰዎች በግዞት በተወሰዱ ጊዜ ‘እሰይ!’ ስላላችሁ  ለምሥራቅ ሰዎች ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ። እነሱ በእናንተ ውስጥ ይሰፍራሉ፤* ድንኳኖቻቸውንም በመካከላችሁ ይተክላሉ። ፍሬያችሁን ይበላሉ፤ ወተታችሁንም ይጠጣሉ።  ራባን+ የግመሎች መሰማሪያ፣ የአሞናውያንን ምድርም መንጋ የሚያርፍበት ስፍራ አደርጋለሁ፤ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።”’”  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘በእጅህ ስላጨበጨብክና+ በእግርህ መሬቱን ስለመታህ እንዲሁም በእስራኤል ምድር ላይ የደረሰውን ሁኔታ ስታይ በንቀት ተሞልተህ* ሐሴት ስላደረግክ፣+  ብሔራት እንዲበዘብዙህ ለእነሱ አሳልፌ እሰጥህ ዘንድ እጄን በአንተ ላይ እዘረጋለሁ። ከሕዝቦች መካከል አስወግድሃለሁ፤ ከአገራትም መካከል ለይቼ አጠፋሃለሁ።+ እደመስስሃለሁ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃለህ።’  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሞዓብና+ ሴይር+ “እነሆ፣ የይሁዳ ቤት ልክ እንደ ሌሎቹ ብሔራት ነው” ስላሉ፣  በድንበሩ ላይ የሚገኙትና የምድሪቱ ውበት* የሆኑት ከተሞች ማለትም ከቤትየሺሞትና ከበዓልመዖን አንስቶ እስከ ቂርያታይም+ ድረስ ያለው የሞዓብ ክንፍ* ለጠላት እንዲጋለጥ አደርጋለሁ። 10  ከአሞናውያን ጋር ለምሥራቅ ሰዎች ርስት አድርጌ እሰጠዋለሁ፤+ ይህም አሞናውያን በብሔራት መካከል እንዳይታወሱ ለማድረግ ነው።+ 11  በሞዓብም ላይ የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ፤+ እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’ 12  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ኤዶም በቂም በቀል ተነሳስቶ በይሁዳ ቤት ላይ እርምጃ ወስዷል፤ ደግሞም እነሱን በመበቀል ከፍተኛ በደል ፈጽሟል፤+ 13  ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እጄን በኤዶምም ላይ እዘረጋለሁ፤ ከምድሪቱም ላይ ሰውንም ሆነ ከብትን አጠፋለሁ፤ ባድማም አደርጋታለሁ።+ ከቴማን አንስቶ እስከ ዴዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ።+ 14  ‘በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምን እበቀላለሁ።+ እነሱም፣ ኤዶም የምወስደውን የበቀል እርምጃ ይቀምስ ዘንድ ቁጣዬንና መዓቴን በኤዶም ላይ ያወርዳሉ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”’ 15  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ፍልስጤማውያን በማይበርድ የጠላትነት ስሜት ተነሳስተው በክፋት* የበቀል እርምጃ ለመውሰድና ጥፋት ለማድረስ ጥረት አድርገዋል።+ 16  ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በፍልስጤማውያን ላይ እጄን እዘረጋለሁ፤+ ከሪታውያንንም አጠፋለሁ፤+ በባሕሩ ዳርቻ ላይ የቀሩትንም ነዋሪዎች እደመስሳለሁ።+ 17  ኃይለኛ ቅጣት በመቅጣት ታላቅ የበቀል እርምጃ እወስድባቸዋለሁ፤ በምበቀላቸውም ጊዜ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”’”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በግንብ የታጠሩ ሰፈሮቻቸውን ይመሠርታሉ።”
ወይም “ነፍስህ በንቀት ተሞልታ።”
ወይም “የሞዓብ አቀበት።”
ወይም “ጌጥ።”
ወይም “በነፍሳቸው ንቀት።”