ሕዝቅኤል 28:1-26

  • በጢሮስ ንጉሥ ላይ የተነገረ ትንቢት (1-10)

    • “እኔ አምላክ ነኝ” (2, 9)

  • ስለ ጢሮስ ንጉሥ የተነገረ ሙሾ (11-19)

    • “በኤደን ነበርክ” (13)

    • “የተቀባህ፣ የምትጋርድ ኪሩብ” (14)

    • ‘ዓመፅ ተገኘብህ’ (15)

  • በሲዶና ላይ የተነገረ ትንቢት (20-24)

  • እስራኤል ተመልሳ ትቋቋማለች (25, 26)

28  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ የጢሮስን ገዢ እንዲህ በለው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ልብህ ከመታበዩ የተነሳ+ ‘እኔ አምላክ ነኝ። በባሕሩ መካከል በአምላክ ዙፋን ላይ እቀመጣለሁ’ ትላለህ።+ በልብህ አምላክ እንደሆንክ የምታስብ ቢሆንምአንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም።   እነሆ፣ አንተ ከዳንኤል+ ይበልጥ ጥበበኛ እንደሆንክ ይሰማሃል። ከአንተ የተሰወረ ሚስጥር እንደሌለ አድርገህ ታስባለህ።   በጥበብህና በማስተዋልህ ራስህን አበልጽገሃል፤በግምጃ ቤቶችህም ውስጥ ወርቅና ብር ማከማቸትህን ቀጥለሃል።+   በንግድህ ስኬታማ ከመሆንህ የተነሳ ብዙ ሀብት አፈራህ፤+ካካበትከውም ሀብት የተነሳ ልብህ ታበየ።”’   “‘ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በልብህ አምላክ እንደሆንክ ስለተሰማህ፣   ከብሔራት መካከል እጅግ ጨካኝ የሆኑትን ባዕዳን አመጣብሃለሁ፤+እነሱም በጥበብህ ውበት ላይ ሰይፋቸውን ይመዛሉ፤ታላቅ ግርማህንም ያረክሳሉ።+   ወደ ጉድጓድ* ያወርዱሃል፤በተንጣለለውም ባሕር መካከል አስከፊ ሞት ትሞታለህ።+   ያም ሆኖ በገዳይህ ፊት ‘እኔ አምላክ ነኝ’ ትላለህ? በሚያረክሱህ ሰዎች እጅ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም።”’ 10  ‘በባዕዳን እጅ፣ ያልተገረዙ ሰዎችን አሟሟት ትሞታለህ፤እኔ ራሴ ተናግሬአለሁና’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።” 11  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 12  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ስለ ጢሮስ ንጉሥ ሙሾ አውርድ፤* እንዲህም በለው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተ ጥበብ የተሞላህና+ ፍጹም ውበት የተላበስክ+የፍጽምና ተምሳሌት* ነበርክ። 13  በአምላክ የአትክልት ስፍራ በኤደን ነበርክ። በከበሩ ድንጋዮች ሁሉይኸውም በሩቢ፣ በቶጳዝዮን፣ በኢያስጲድ፣ በክርስቲሎቤ፣ በኦኒክስ፣ በጄድ፣ በሰንፔር፣ በበሉርና+ በመረግድ አጊጠህ ነበር፤እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች የተሰኩባቸው ማቀፊያዎችም ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ። በተፈጠርክበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር። 14  የተቀባህ፣ የምትጋርድ ኪሩብ አድርጌ ሾምኩህ። በአምላክ ቅዱስ ተራራ ላይ ነበርክ፤+ በእሳታማ ድንጋዮችም መካከል ትመላለስ ነበር። 15  ከተፈጠርክበት ቀን አንስቶ ዓመፅ እስከተገኘብህ ጊዜ ድረስበመንገድህ ሁሉ ምንም እንከን አልነበረብህም።+ 16  ከንግድህ ብዛት የተነሳ+ውስጥህ በዓመፅ ተሞላ፤ ኃጢአትም መሥራት ጀመርክ።+ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፣ እንደ ርኩስ ቆጥሬ ከአምላክ ተራራ እጥልሃለሁ፤ከእሳታማዎቹ ድንጋዮች መካከልም አስወግድሃለሁ።+ 17  በውበትህ+ ምክንያት ልብህ ታበየ። ከታላቅ ግርማህ የተነሳ ጥበብህን አበላሸህ።+ ወደ ምድር እጥልሃለሁ።+ በነገሥታት ፊት ትዕይንት አደርግሃለሁ። 18  ታላቅ በደል በመፈጸምና በንግድ ሥራ በማጭበርበር መቅደሶችህን አረከስክ። እኔም ከመካከልህ እሳት እንዲወጣ አደርጋለሁ፤ እሳቱም ይበላሃል።+ በሚያዩህ ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አደርግሃለሁ። 19  ከሕዝቦች መካከል የሚያውቁህ ሁሉ በመገረም አተኩረው ያዩሃል።+ ፍጻሜህ ድንገተኛና አስከፊ ይሆናል፤ደግሞም ለዘላለም ከሕልውና ውጭ ትሆናለህ።”’”+ 20  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 21  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ፊትህን ወደ ሲዶና+ አዙረህ በእሷ ላይ ትንቢት ተናገር። 22  እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሲዶና ሆይ፣ እነሆ እኔ በአንቺ ላይ ተነስቻለሁ፤ በመካከልሽም እከበራለሁ፤ደግሞም በእሷ ላይ የፍርድ እርምጃ በምወስድበትና በእሷ አማካኝነት በምቀደስበት ጊዜ ሰዎች እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ። 23  በእሷ ላይ ቸነፈር እሰዳለሁ፤ በጎዳናዎቿም ላይ ደም ይፈስሳል። ከየአቅጣጫው ሰይፍ በሚመጣባት ጊዜ የታረዱት ሰዎች በመካከሏ ይወድቃሉ፤እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።+ 24  “‘“ከዚያ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ አደገኛ በሆነ አሜኬላና በሚያሠቃይ እሾህ+ ይኸውም በሚንቁት ብሔራት ዳግመኛ አይከበብም፤ ሰዎችም እኔ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”’ 25  “‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤልን ቤት ሰዎች ከተበተኑባቸው ሕዝቦች መካከል ዳግመኛ በምሰበስባቸው ጊዜ+ በብሔራት ፊት በእነሱ መካከል እቀደሳለሁ።+ እነሱም ለአገልጋዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት+ ምድራቸው ላይ ይኖራሉ።+ 26  በላይዋ ላይ ያለስጋት ይቀመጣሉ፤+ ቤቶችንም ይሠራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤+ ደግሞም በዙሪያቸው ባሉት በሚንቋቸው ሁሉ ላይ የፍርድ እርምጃ በምወስድበት ጊዜ ያለስጋት ይኖራሉ፤+ እኔም አምላካቸው ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”’”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ወደ መቃብር።”
ቃል በቃል “በማኅተም የጸደቀ ንድፍ።”
ወይም “የሐዘን እንጉርጉሮ አሰማ።”