ሕዝቅኤል 30:1-26

  • በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት (1-19)

    • ናቡከደነጾር ጥቃት እንደሚሰነዝር ትንቢት ተነገረ (10)

  • የፈርዖን ክንድ ተሰበረ (20-26)

30  የይሖዋም ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ዋይ ዋይ በሉ፤ ‘ቀኑ ስለቀረበ ወዮ!’   ቀኑ ቀርቧልና፤ አዎ፣ የይሖዋ ቀን ቀርቧል።+ የደመናት ቀን፣+ በብሔራትም ላይ የሚፈረድበት ቀን ይሆናል።+   ሰይፍ በግብፅ ላይ ይመጣል፤ የታረዱት በግብፅ ሲወድቁ፣ሀብቷ ሲወሰድ እንዲሁም መሠረቶቿ ሲፈራርሱ ኢትዮጵያ በሽብር ትዋጣለች።+   ኢትዮጵያ፣+ ፑጥ፣+ ሉድና ድብልቅ ሕዝቦች ሁሉ*እንዲሁም ኩብ፣ ከቃል ኪዳኑ ምድር ልጆች* ጋርሁሉም በሰይፍ ይወድቃሉ።”’   ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለግብፅ ድጋፍ የሚሰጡም ይወድቃሉ፤የምትታበይበት ኃይሏም ይወገዳል።’+ “‘ከሚግዶል+ እስከ ሰዌኔ+ በምድሪቱ ላይ በሰይፍ ይወድቃሉ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።  ‘ከሌሎች አገሮች በከፋ ሁኔታ ባድማ ይሆናሉ፤ ከተሞቿም ከሌሎች ከተሞች በከፋ ሁኔታ ይወድማሉ።+  በግብፅም ላይ እሳት በማነድበትና ተባባሪዎቿ ሁሉ በሚደቁበት ጊዜ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።  በዚያን ቀን በራሷ የምትታመነውን ኢትዮጵያን ለማንቀጥቀጥ መልእክተኞችን በመርከብ እልካለሁ፤ ግብፅ በምትጠፋበት ቀን በሽብር ይዋጣሉ፤ ቀኑ በእርግጥ ይመጣልና።’ 10  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ስፍር ቁጥር የሌለውን የግብፅ ሕዝብ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር* እጅ አጠፋለሁ።+ 11  ከብሔራት መካከል እጅግ ጨካኝ የሆኑት፣ እሱና ሠራዊቱ+ ምድሪቱን ለማውደም ይመጣሉ። እነሱም በግብፅ ላይ ሰይፋቸውን ይመዛሉ፤ ምድሪቱንም ሬሳ በሬሳ ያደርጋሉ።+ 12  የአባይን የመስኖ ቦዮች አደርቃለሁ፤+ ምድሪቱንም ለክፉ ሰዎች እሸጣለሁ። ምድሪቱና በውስጧ ያለው ሁሉ በባዕዳን እጅ እንዲጠፉ አደርጋለሁ።+ እኔ ይሖዋ ራሴ ይህን ተናግሬአለሁ።’ 13  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘አስጸያፊ የሆኑትንም ጣዖቶች* አጠፋለሁ፤ ከንቱ የሆኑትንም የኖፍ*+ አማልክት አስወግዳለሁ። ከእንግዲህ ከግብፅ ምድር የሚወጣ ገዢ* አይኖርም፤ በግብፅም ምድር ፍርሃት እሰዳለሁ።+ 14  ጳትሮስን+ ባድማ አደርጋለሁ፤ በጾዓን እሳት አነዳለሁ፤ ደግሞም በኖእ*+ ላይ የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ። 15  የግብፅ ምሽግ በሆነችው በሲን ላይ ቁጣዬን አፈስሳለሁ፤ የኖእንም ሕዝብ አጠፋለሁ። 16  በግብፅ ላይ እሳት አነዳለሁ፤ ሲን በሽብር ትዋጣለች፤ ኖእ ቅጥሯ ይፈርሳል፤ ኖፍ* ደግሞ በጠራራ ፀሐይ ጥቃት ይሰነዘርባታል! 17  የኦንና* የጲበሰት ወጣቶች በሰይፍ ይወድቃሉ፤ የከተሞቹም ነዋሪዎች በግዞት ይወሰዳሉ። 18  በዚያ የግብፅን ቀንበር በምሰብርበት ጊዜ በጣፍነስ ቀኑ ይጨልማል።+ የምትታበይበት ኃይሏ ይጠፋል፤+ ደመናት ይሸፍኗታል፤ የከተሞቿም ነዋሪዎች በግዞት ይወሰዳሉ።+ 19  በግብፅ ላይ የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ፤ እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’” 20  በ11ኛውም ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በሰባተኛው ቀን፣ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 21  “የሰው ልጅ ሆይ፣ የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፤ እንዲድን አይታሰርም፤ ወይም ጠንክሮ ሰይፍ እንዲይዝ በጨርቅ አይጠቀለልም።” 22  “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ እኔ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ተነስቻለሁ፤+ ብርቱውንና የተሰበረውን፣ ሁለቱንም ክንዶቹን እሰብራለሁ፤+ ሰይፉም ከእጁ ላይ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።+ 23  ከዚያም ግብፃውያንን በብሔራት መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።+ 24  የባቢሎንን ንጉሥ ክንዶች አበረታለሁ፤*+ ሰይፌንም አስጨብጠዋለሁ፤+ የፈርዖንን ክንዶች እሰብራለሁ፤ እሱም ሊሞት እያጣጣረ እንዳለ ሰው በፊቱ* እጅግ ያቃስታል። 25  የባቢሎንን ንጉሥ ክንዶች አበረታለሁ፤ የፈርዖን ክንዶች ግን ይዝላሉ፤ ሰይፌንም ለባቢሎን ንጉሥ ሳስጨብጠውና በግብፅ ምድር ላይ ሲሰነዝረው እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።+ 26  ግብፃውያንንም በብሔራት መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ፤+ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ከሌሎች ብሔራት የተውጣጡ ሁሉ።”
ከግብፅ ጋር የተባበሩትን እስራኤላውያን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “አለቃ።”
ወይም “የሜምፊስ።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ቴብስን ያመለክታል።
ወይም “ሜምፊስ።”
ሂልያፖሊስን ያመለክታል።
ወይም “ለባቢሎን ንጉሥ ኃይል እጨምርለታለሁ።”
በባቢሎን ንጉሥ ፊት ማለት ነው።