ሕዝቅኤል 31:1-18

  • በግዙፍ አርዘ ሊባኖስ የተመሰለችው ግብፅ ትወድቃለች (1-18)

31  በ11ኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖንና ስፍር ቁጥር ለሌለው ሕዝቡ እንዲህ በል፦+‘በታላቅነትህ ከማን ጋር ትመሳሰላለህ?   አንድ አሦራዊ፣ በሊባኖስ ያደገ አርዘ ሊባኖስ ነበር፤አርዘ ሊባኖሱ ጥላ እንደሚሰጡ ችፍግ ብለው ያደጉ ዛፎች፣ የሚያማምሩ ቅርንጫፎች ያሉት እጅግ ረጅም ዛፍ ሲሆንጫፉም ደመናትን ይነካ ነበር።   ውኃዎቹ ትልቅ ዛፍ እንዲሆን አደረጉት፤ ጥልቅ ከሆኑት ምንጮች የተነሳ ዛፉ በጣም ረጅም ሆነ። በተተከለበት ቦታ ዙሪያ ጅረቶች ነበሩ፤የውኃ መውረጃዎቻቸውም በሜዳ ያሉትን ዛፎች ሁሉ ያጠጡ ነበር።   ከዚህም የተነሳ ቁመቱ በሜዳ ካሉት ከሌሎቹ ዛፎች ሁሉ ረዘመ። ብዙ ቅርንጫፎች አወጣ፤ ጅረቶቹ ብዙ ውኃ ስለነበራቸውቅርንጫፎቹ ረጃጅም ሆኑ።   የሰማይ ወፎች ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ጎጇቸውን ሠሩ፤የዱር እንስሳትም ሁሉ ከቅርንጫፎቹ ሥር ግልገሎቻቸውን ወለዱ፤ከጥላውም ሥር ብዙ ሕዝብ ያላቸው ብሔራት ሁሉ ሰፈሩ።   ከውበቱና ከቅርንጫፎቹ ርዝመት የተነሳ ግርማ ሞገስ ተላበሰ፤ሥሮቹን ብዙ ውኃ ወዳለበት ስፍራ ሰዶ ነበርና።   በአምላክ የአትክልት ስፍራ+ ያሉ ሌሎች አርዘ ሊባኖሶች ሊተካከሉት አልቻሉም። ከጥድ ዛፎች መካከል የእሱ ዓይነት ቅርንጫፎች ያሉት አንድም ዛፍ የለም፤የአርሞን ዛፎችም* ከእሱ ቅርንጫፎች ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም። በአምላክ የአትክልት ስፍራ ያለ የትኛውም ዛፍ በውበቱ አይወዳደረውም።   ብዙ ቅጠሎች ያሉት ውብ ዛፍ አድርጌ ሠራሁት፤በእውነተኛው አምላክ የአትክልት ስፍራ በኤደን ያሉ ሌሎች ዛፎችም ሁሉ ቀኑበት።’ 10  “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ቁመቱ* እጅግ ከመርዘሙ የተነሳ ጫፉን በደመናት መካከል ከፍ ስላደረገና በቁመቱ የተነሳ ልቡ ስለታበየ፣ 11  ኃያል ለሆነ የብሔራት ገዢ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።+ እሱም በእርግጥ ይነሳበታል፤ በክፋቱም የተነሳ እጥለዋለሁ። 12  ከብሔራት መካከል እጅግ ጨካኝ የሆኑት ባዕዳን ቆርጠው ይጥሉታል፤ በተራሮችም ላይ ጥለውት ይሄዳሉ፤ ቅጠሎቹም በየሸለቆው ይረግፋሉ፤ ቅርንጫፎቹም በምድሪቱ ላይ ባሉ ጅረቶች ሁሉ ላይ ተሰባብረው ይወድቃሉ።+ የምድር ሕዝቦች ሁሉ ከጥላው ሥር ወጥተው ትተውት ይሄዳሉ። 13  የሰማይ ወፎች ሁሉ በወደቀው ግንዱ ላይ ይሰፍራሉ፤ የዱር እንስሳትም ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ይኖራሉ።+ 14  ይህም የሚሆነው በውኃዎች አጠገብ ካሉ ዛፎች መካከል አንዳቸውም ቁመታቸው በጣም እንዳይረዝም ወይም ጫፋቸውን በደመናት መካከል ከፍ እንዳያደርጉ እንዲሁም ውኃ የጠገበ አንድም ዛፍ ቁመቱ እነሱ ጋ እንዳይደርስ ነው። ሁሉም ለሞት ይዳረጋሉና፤ ወደ ጉድጓድ* ከሚወርዱት የሰው ልጆች ጋር በአንድነት ከምድር በታች ይወርዳሉ።’ 15  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ መቃብር* በሚወርድበት ቀን ሰዎች እንዲያዝኑ አደርጋለሁ። ስለዚህ ጥልቅ የሆኑትን ውኃዎች እሸፍናለሁ፤ ጅረቶቹንም እገታለሁ፤ ይህም በገፍ የሚፈስሱት ውኃዎች ይቋረጡ ዘንድ ነው። ከእሱ የተነሳ ሊባኖስን አጨልማለሁ፤ በሜዳም ያሉ ዛፎች ሁሉ ይጠወልጋሉ። 16  ወደ ጉድጓድ* ከሚወርዱት ሁሉ ጋር ወደ መቃብር* በማወርደው ጊዜ ሲወድቅ በሚሰማው ድምፅ ብሔራት እንዲናወጡ አደርጋለሁ፤ ከምድርም በታች የኤደን ዛፎች ሁሉ፣+ ምርጥና ግሩም የሆኑት የሊባኖስ ዛፎች ሁሉ እንዲሁም ውኃ የጠገቡት ዛፎች ሁሉ ይጽናናሉ። 17  ከእሱ ጋር እንዲሁም በብሔራት መካከል በጥላው ሥር ይኖሩ ከነበሩት ደጋፊዎቹ* ጋር በሰይፍ የታረዱት ወዳሉበት ወደ መቃብር* ወርደዋል።’+ 18  “‘በኤደን ካሉት ዛፎች መካከል የአንተ ዓይነት ክብርና ታላቅነት ያለው የትኛው ነው?+ ይሁንና ከኤደን ዛፎች ጋር ከምድር በታች ትወርዳለህ። ባልተገረዙት መካከል፣ በሰይፍ ከታረዱት ጋር ትጋደማለህ። ይህ በፈርዖንና ስፍር ቁጥር በሌለው ሕዝቡ ላይ ይፈጸማል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻ

የተንዠረገጉ ቅርንጫፎችና እየተቀረፈ የሚወድቅ ቅርፊት ያለው ዛፍ።
ቃል በቃል “ቁመትህ።”
ወይም “መቃብር።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “መቃብር።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “(በጥላው ሥር ይኖር ከነበረው) ክንዱ።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።