ሕዝቅኤል 34:1-31

  • በእስራኤል እረኞች ላይ የተነገረ ትንቢት (1-10)

  • ይሖዋ በጎቹን ይንከባከባል (11-31)

    • ‘አገልጋዬ ዳዊት’ እረኛቸው ይሆናል (23)

    • “የሰላም ቃል ኪዳን” (25)

34  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር። ትንቢት ተናገር፤ እረኞቹንም እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ራሳቸውን ለሚመግቡ የእስራኤል እረኞች ወዮላቸው!+ እረኞቹ ሊመግቡ የሚገባው መንጋውን አይደለም?+  ጮማውን ትበላላችሁ፤ ሱፉን ትለብሳላችሁ፤ የሰባውንም እንስሳ ታርዳላችሁ፤+ መንጋውን ግን አትመግቡም።+  የደከመውን አላበረታችሁም፣ የታመመውን አልፈወሳችሁም፣ የተጎዳውን በጨርቅ አላሰራችሁትም፣ የባዘኑትን መልሳችሁ አላመጣችሁም ወይም የጠፋውን አልፈለጋችሁም፤+ ከዚህ ይልቅ በጭካኔና በግፍ ገዛችኋቸው።+  በጎቹ እረኛ በማጣታቸው ተበታተኑ፤+ ተበታትነው ለዱር አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ።  በጎቼ በየተራራውና ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ባዘኑ፤ በምድር ሁሉ ላይ ተበተኑ፤ የፈለጋቸው ወይም እነሱን ለማግኘት የጣረ አንድም ሰው የለም።  “‘“ስለዚህ እናንተ እረኞች፣ የይሖዋን ቃል ስሙ፦  ‘“በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ “በጎቼ እረኛ ስላጡና እረኞቼ በጎቼን ስላልፈለጉ፣ ይልቁንም እረኞቹ ራሳቸውን ስለመገቡና በጎቼን ስላልመገቡ፣ በጎቼ ለአደን ተዳርገዋል፤ ለዱር አራዊትም ሁሉ መብል ሆነዋል፤”’  ስለዚህ እናንተ እረኞች፣ የይሖዋን ቃል ስሙ። 10  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ በእረኞቹ ላይ ተነስቻለሁ፤ ስለ በጎቼ እጠይቃቸዋለሁ፤* በጎቼን እንዳያሰማሩም* እከለክላቸዋለሁ፤+ እረኞቹም ከእንግዲህ ራሳቸውን አይመግቡም። በጎቼን ከአፋቸው አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህ ለእነሱ መብል አይሆኑም።’” 11  “‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “እነሆኝ፣ እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ ደግሞም እንከባከባቸዋለሁ።+ 12  የተበታተኑትን በጎቹን አግኝቶ እንደሚመግብ እረኛ በጎቼን እንከባከባለሁ።+ በደመናትና በድቅድቅ ጨለማ ቀን ከተበተኑባቸው ቦታዎች ሁሉ እታደጋቸዋለሁ።+ 13  ከሕዝቦች መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሩም እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤል ተራሮች፣ በየጅረቱ ዳርና በምድሪቱ ላይ በሚገኙት መኖሪያ ስፍራዎች ሁሉ አሰማራቸዋለሁ።+ 14  ጥሩ በሆነ መስክ ላይ አሰማራቸዋለሁ፤ ከፍ ያሉት የእስራኤል ተራሮችም የግጦሽ መሬት ይሆኗቸዋል።+ በዚያም ጥሩ በሆነ የግጦሽ መሬት ላይ ያርፋሉ፤+ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ መስክ ይሰማራሉ።” 15  “‘“በጎቼን እኔ ራሴ አሰማራለሁ፤+ እኔ ራሴም አሳርፋቸዋለሁ”+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 16  “የጠፋውን እፈልጋለሁ፤+ የባዘነውን መልሼ አመጣለሁ፤ የተጎዳውን በጨርቅ አስራለሁ፤ የደከመውን አበረታለሁ፤ የወፈረውንና ጠንካራ የሆነውን ግን አጠፋለሁ። እፈርድበታለሁ፤ ተገቢውንም ቅጣት እሰጠዋለሁ።” 17  “‘በጎቼ ስለሆናችሁት ስለ እናንተ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በበግና በበግ መካከል እንዲሁም በአውራ በጎችና በአውራ ፍየሎች መካከል ልፈርድ ነው።+ 18  እናንተ ምርጥ ከሆነው የግጦሽ ስፍራ መመገባችሁ አነሳችሁ? የቀሩትን የግጦሽ ስፍራዎች ደግሞ በእግራችሁ መረጋገጥ ይገባችኋል? እጅግ የጠራውን ውኃ ከጠጣችሁ በኋላስ ውኃውን በእግራችሁ እየመታችሁ ማደፍረሳችሁ ተገቢ ነው? 19  ታዲያ በጎቼ በእግራችሁ በረጋገጣችሁት የግጦሽ መስክ ላይ መሰማራትና በእግራችሁ እየመታችሁ ያደፈረሳችሁትን ውኃ መጠጣት ይኖርባቸዋል?” 20  “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላቸዋል፦ “እነሆኝ፣ እኔ ራሴ በሰባው በግና ከሲታ በሆነው በግ መካከል እፈርዳለሁ፤ 21  እናንተ የታመሙት ሁሉ በየአቅጣጫው እስኪበታተኑ ድረስ በጎናችሁና በትከሻችሁ ገፍታችኋቸዋልና፤ በቀንዳችሁም ገፍትራችኋቸዋል። 22  በጎቼንም አድናለሁ፤ እነሱም ከእንግዲህ ለአደን አይዳረጉም፤+ እኔም በበግና በበግ መካከል እፈርዳለሁ። 23  በእነሱ ላይ አንድ እረኛ ይኸውም አገልጋዬን ዳዊትን* አስነሳለሁ፤+ እሱም ይመግባቸዋል። እሱ ራሱ ያሰማራቸዋል፤ እረኛቸውም ይሆናል።+ 24  ደግሞም እኔ ይሖዋ አምላካቸው እሆናለሁ፤+ አገልጋዬ ዳዊት ደግሞ በመካከላቸው አለቃ ይሆናል።+ እኔ ይሖዋ ራሴ ተናግሬአለሁ። 25  “‘“ከእነሱም ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤+ አደገኛ የሆኑ የዱር አራዊትንም ከምድሪቱ ላይ አጠፋለሁ፤+ በመሆኑም በምድረ በዳ ያለስጋት ይኖራሉ፤ በጫካዎችም ውስጥ ይተኛሉ።+ 26  እነሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያለውን ቦታ በረከት አደርጋቸዋለሁ፤+ ዝናብም በወቅቱ እንዲዘንብ አደርጋለሁ። በረከት እንደ ዝናብ ይወርዳል።+ 27  የሜዳው ዛፎች ፍሬያቸውን ይሰጣሉ፤ መሬቱም ፍሬ ይሰጣል፤+ እነሱም በምድሪቱ ላይ ያለስጋት ይቀመጣሉ። ቀንበራቸውን በምሰብርበትና ባሪያ አድርገው ከሚገዟቸው እጅ በማድናቸው ጊዜ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።+ 28  ከእንግዲህ ወዲህ ብሔራት እነሱን ለማደን አይነሱም፤ የምድር አራዊትም አይበሏቸውም፤ ያለስጋትም ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም።+ 29  “‘“ዝና የሚያስገኝ* የእርሻ ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ በምድሪቱ ላይ በረሃብ አያልቁም፤+ ደግሞም ከእንግዲህ ወዲህ ብሔራት አያዋርዷቸውም።+ 30  ‘በዚህ ጊዜ እኔ አምላካቸው ይሖዋ ከእነሱ ጋር እንደሆንኩና እነሱ ይኸውም የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እንደሆኑ ያውቃሉ’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”’ 31  “‘እናንተ በጎቼ፣+ የምንከባከባችሁ በጎች፣ ከአፈር የተሠራችሁ ሰዎች ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በጎቼን ከእጃቸው እሻለሁ።”
ወይም “እንዳያግዱም።”
የዳዊትን ዘር ያመለክታል።
ቃል በቃል “ለስም የሚሆን።”