ሕዝቅኤል 38:1-23

  • ጎግ በእስራኤል ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት (1-16)

  • በጎግ ላይ የሚነደው የይሖዋ ቁጣ (17-23)

    • ‘ብሔራት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ’ (23)

38  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ፊትህን የመሼቅና የቱባል+ ዋና አለቃ* በሆነውና በማጎግ ምድር በሚገኘው በጎግ ላይ አድርገህ+ በእሱ ላይ ትንቢት ተናገር።+  እንዲህ በል፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የመሼቅና የቱባል ዋና አለቃ* የሆንከው ጎግ ሆይ፣ እኔ በአንተ ላይ ተነስቻለሁ።  እመልስሃለሁ፤ በመንጋጋህም መንጠቆ አስገባለሁ፤+ ከመላው ሠራዊትህ ይኸውም ከፈረሶች፣ ያማረ ልብስ ከለበሱ ፈረሰኞች፣ ትልቅ ጋሻና ትንሽ ጋሻ* ከያዘ እንዲሁም ሰይፍ ከሚመዝ ታላቅ ጉባኤ ጋር አወጣሃለሁ፤+  ትንሽ ጋሻ የያዙና የራስ ቁር የደፉ የፋርስ፣ የኢትዮጵያና የፑጥ+ ሰዎች ከእነሱ ጋር አሉ፤  ጎሜርንና ወታደሮቹን ሁሉ፣ ራቅ ባለው የሰሜን ምድር የሚገኙትን የቶጋርማ+ ቤት ሰዎችንና ወታደሮቻቸውን ሁሉ ጨምሮ ብዙ ሕዝቦች ከአንተ ጋር አሉ።+  “‘“አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር የተሰበሰበው ሠራዊትህ ሁሉ ተነሡ፣ ተዘጋጁም፤ አንተም አዛዣቸው* ትሆናለህ።  “‘“ከብዙ ቀናት በኋላ በአንተ ላይ ትኩረት ይደረጋል።* በመጨረሻዎቹ ዓመታት ከሰይፍ ጥቃት የተረፈውንና ከብዙ ሕዝቦች መካከል ተሰብስቦ ለብዙ ጊዜ ባድማ ሆነው ወደቆዩት የእስራኤል ተራሮች የተመለሰውን ሕዝብ ምድር ትወራለህ። የምድሪቱ ነዋሪዎች ከተለያዩ ሕዝቦች መካከል ተመልሰው የመጡ ናቸው፤ ደግሞም ሁሉም ያለስጋት ተቀምጠዋል።+  አንተም በእነሱ ላይ እንደ አውሎ ነፋስ ትመጣለህ፤ አንተና ወታደሮችህ ሁሉ እንዲሁም ከአንተ ጋር ያሉት ብዙ ሕዝቦች ምድሪቱን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ።”’ 10  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያ ቀን ሐሳብ ወደ ልብህ ይገባል፤ ክፉ ዕቅድም ታወጣለህ፤ 11  እንዲህ ትላለህ፦ “ከለላ የሌላቸው ሰፈሮች* የሚገኙበትን ምድር እወራለሁ።+ ያለስጋት ተረጋግተው በሚኖሩት ላይ እመጣለሁ፤ ሁሉም የሚኖሩት ቅጥር፣ መቀርቀሪያና በር በሌላቸው ሰፈሮች ነው።” 12  ዓላማህ ብዙ ሀብት መበዝበዝና መዝረፍ፣ ደግሞም አሁን የሰው መኖሪያ የሆኑትን ባድማ የነበሩ ስፍራዎችና+ ከብሔራት ሁሉ መካከል ዳግመኛ የተሰበሰበውን ሕዝብ+ ማጥቃት ነው፤ ይህ ሕዝብ ሀብትና ንብረት አከማችቷል፤+ በምድርም እምብርት ላይ ይኖራል። 13  “‘ሳባ፣+ ዴዳን፣+ የተርሴስ+ ነጋዴዎችና ተዋጊዎቹ* ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ “ወረራ የምታካሂደው ብዙ ሀብት ለመበዝበዝና ለመዝረፍ ነው? ሠራዊትህን የሰበሰብከው ብርና ወርቅ ለማጋበስ፣ ሀብትና ንብረት ለመውሰድ እንዲሁም ብዙ ምርኮ ለመንጠቅ ነው?”’ 14  “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፣ ትንቢት ተናገር፤ ጎግንም እንዲህ በለው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ እስራኤል ያለስጋት በሚቀመጥበት ጊዜ፣ አንተ በዚያን ቀን ይህን ማወቅህ ይቀራል?+ 15  አንተ ከስፍራህ ይኸውም ርቆ ከሚገኘው የሰሜን ምድር ትመጣለህ፤+ አንተና ከአንተ ጋር ያሉ ብዙ ሕዝቦች ትመጣላችሁ፤ ሁሉም በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፣ ታላቅ ጉባኤና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት ናቸው።+ 16  ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ሆነህ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትመጣለህ። ጎግ ሆይ፣ በዘመኑ መጨረሻ በአንተ አማካኝነት በፊታቸው ራሴን በምቀድስበት ጊዜ ብሔራት ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።”’+ 17  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘አንተን በእነሱ ላይ እንደማመጣ ለብዙ ዓመታት ትንቢት በተናገሩትና አገልጋዮቼ በሆኑት የእስራኤል ነቢያት አማካኝነት በቀድሞ ዘመን የተናገርኩት ስለ አንተው አይደለም?’ 18  “‘በዚያ ቀን፣ ጎግ የእስራኤልን ምድር በሚወርበት ቀን’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘ታላቅ ቁጣዬ ይነድዳል።+ 19  በቅንዓቴና በቁጣዬ እሳት እናገራለሁ፤ ደግሞም በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል። 20  የባሕር ዓሣዎች፣ የሰማይ ወፎች፣ የዱር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ እንስሳት ሁሉና በምድር ላይ ያሉ ሰዎች በሙሉ ከእኔ የተነሳ ይንቀጠቀጣሉ፤ ተራሮችም ይናዳሉ፤+ ገደላማ ቦታዎችም ይደረመሳሉ፤ ቅጥሩም ሁሉ ይፈርሳል።’ 21  “‘በተራሮቼ ሁሉ፣ በጎግ ላይ ሰይፍ እጠራለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በገዛ ወንድሙ ላይ ይሆናል።+ 22  እኔም በቸነፈርና+ በደም መፋሰስ እፈርድበታለሁ፤* በእሱ፣ በወታደሮቹና ከእሱ ጋር ባሉ ብዙ ሕዝቦች ላይ ኃይለኛ ዶፍ፣ በረዶ፣+ እሳትና+ ድኝ+ አዘንባለሁ።+ 23  ደግሞም ራሴን ገናና አደርጋለሁ፤ እንዲሁም ራሴን እቀድሳለሁ፤ በብዙ ብሔራትም ፊት ማንነቴ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ዋነኛ ገዢ።”
ወይም “ዋነኛ ገዢ።”
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
ቃል በቃል “ጠባቂያቸው።”
ወይም “ትጠራለህ።”
ወይም “ቅጥር የሌላቸው ገጠራማ ቦታዎች።”
ወይም “ደቦል አንበሶቹ።”
ወይም “እፋረደዋለሁ።”