ሕዝቅኤል 47:1-23
47 ከዚያም ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ+ መልሶ አመጣኝ፤ በዚያም ከቤተ መቅደሱ ደፍ ሥር ወደ ምሥራቅ የሚፈስ ውኃ ተመለከትኩ፤+ የቤተ መቅደሱ ፊት ከምሥራቅ ትይዩ ነበር። ውኃው ከቤተ መቅደሱ በስተ ቀኝ ከሥር ወጥቶ ከመሠዊያው በስተ ደቡብ ይወርድ ነበር።
2 ከዚያም ወደ ሰሜን በር+ በሚወስደው መንገድ በኩል አምጥቶ ወደ ውጭ ካወጣኝ በኋላ ከምሥራቅ ትይዩ ወዳለው የውጨኛው በር+ አዙሮ አመጣኝ፤ እኔም በስተ ቀኝ በኩል ቀስ እያለ የሚፈስ ውኃ አየሁ።
3 ሰውየው መለኪያ ገመድ በእጁ ይዞ+ ወደ ምሥራቅ በመሄድ 1,000 ክንድ* ለካ፤ ከዚያም በውኃው መካከል እንዳልፍ አደረገኝ፤ ውኃው እስከ ቁርጭምጭሚት ይደርስ ነበር።
4 ከዚያም 1,000 ክንድ ለካ፤ በውኃውም መካከል እንዳልፍ አደረገኝ፤ ውኃውም እስከ ጉልበት ደረሰ።
ደግሞም 1,000 ክንድ ለካ፤ በውኃውም መካከል እንዳልፍ አደረገኝ፤ ውኃውም እስከ ወገብ ደረሰ።
5 እንደገናም 1,000 ክንድ በለካ ጊዜ ውኃው ልሻገረው የማልችል ወንዝ ሆነ፤ እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ በዋና ካልሆነ በስተቀር በእግር ሊሻገሩት የማይቻል ወንዝ ሆኖ ነበር።
6 እሱም “የሰው ልጅ ሆይ፣ ይህን ታያለህ?” ሲል ጠየቀኝ።
ከዚያም መልሶ ወደ ጅረቱ ዳርቻ ወሰደኝ።
7 በተመለስኩ ጊዜ በጅረቱ ዳርቻ፣ በግራና በቀኝ በጣም ብዙ ዛፎች አየሁ።+
8 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ ውኃ በስተ ምሥራቅ ወዳለው ምድር ይፈስሳል፤ አረባን*+ አቋርጦም ይወርዳል፤ ወደ ባሕሩም* ይገባል። ወደ ባሕሩ በሚገባበት ጊዜ+ በዚያ ያለው ውኃ ይፈወሳል።
9 ውኃዎቹ* በሚፈስሱበት ቦታ ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕያዋን ፍጥረታት* በሕይወት መኖር ይችላሉ። ይህ ውኃ ወደዚያ ስለሚፈስ በዚያ እጅግ ብዙ ዓሣዎች ይኖራሉ። የባሕሩ ውኃ ይፈወሳል፤ ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት ይኖራል።
10 “ከኤንገዲ+ እስከ ኤንዔግላይም ድረስ ዓሣ አጥማጆች በዳርቻው ይቆማሉ፤ በዚያም መረባቸውን የሚያሰጡበት ቦታ ይኖራል። በታላቁ ባሕር*+ እንዳሉት ዓሣዎች በዚያም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ብዙ ዓይነት ዓሣዎች ይኖራሉ።
11 “ረግረጋማ የሆኑና ውኃ ያቆሩ ቦታዎች ይኖሩታል፤ እነዚህ ቦታዎች አይፈወሱም። ጨዋማ እንደሆኑ ይቀራሉ።+
12 “በወንዙ ዳርና ዳር ለመብል የሚሆኑ ብዙ ዓይነት ዛፎች ይበቅላሉ። ቅጠላቸው አይጠወልግም፤ ፍሬ ማፍራትም አያቆሙም። ከመቅደሱ የሚወጣውን ውኃ+ ስለሚጠጡ በየወሩ አዲስ ፍሬ ይሰጣሉ። ፍሬያቸው ለመብል፣ ቅጠላቸውም ለመድኃኒት ይሆናል።”+
13 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ለ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታከፋፍሏት ክልል ይህች ናት፤ ዮሴፍ ሁለት ድርሻ ይኖረዋል።+
14 እናንተ ትወርሷታላችሁ፤ እኩል ድርሻም ታገኛላችሁ።* ለአባቶቻችሁ ይህችን ምድር እንደምሰጣቸው ምዬላቸው ነበር፤+ አሁንም ይህች ምድር ርስት ሆና ተሰጥታችኋለች።*
15 “በስተ ሰሜን በኩል የምድሪቱ ወሰን ይህ ነው፦ ከታላቁ ባሕር ተነስቶ ወደ ሄትሎን+ በሚወስደው መንገድ በኩል እስከ ጼዳድ+ ይደርሳል፤
16 ከዚያም እስከ ሃማት፣+ እስከ ቤሮታ+ እንዲሁም በደማስቆ ክልልና በሃማት ክልል መካከል እስካለው እስከ ሲብራይም ብሎም በሃውራን+ ወሰን እስከሚገኘው እስከ ሃጸርሃቲኮን ይዘልቃል።
17 ስለዚህ ወሰኑ ከባሕሩ በመነሳት በስተ ሰሜን በደማስቆ ድንበርና በሃማት+ ድንበር በኩል እስከ ሃጻርኤናን+ ድረስ ይዘልቃል። በሰሜን በኩል ወሰኑ ይህ ነው።
18 “በምሥራቅ በኩል ወሰኑ ከሃውራን እስከ ደማስቆ እንዲሁም በዮርዳኖስ አጠገብ ከጊልያድ+ እስከ እስራኤል ምድር ይዘልቃል። ከወሰኑ አንስቶ እስከ ምሥራቁ ባሕር* ድረስ ትለካላችሁ። በምሥራቅ በኩል ወሰኑ ይህ ነው።
19 “በደቡብ በኩል ያለው ወሰን* ከትዕማር ተነስቶ እስከ መሪባትቃዴስ+ ውኃዎች፣ ከዚያም እስከ ደረቁ ወንዝና* እስከ ታላቁ ባሕር+ ይደርሳል። በደቡብ በኩል ወሰኑ* ይህ ነው።
20 “በምዕራብ በኩል ታላቁ ባሕር የሚገኝ ሲሆን ይህም ከወሰኑ አንስቶ ከሌቦሃማት*+ ትይዩ እስካለው ቦታ ድረስ ይዘልቃል። በምዕራብ በኩል ወሰኑ ይህ ነው።”
21 “ይህችን ምድር ለእናንተ ይኸውም ለ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ታከፋፍላላችሁ።
22 ምድሪቱን ለእናንተ እንዲሁም በመካከላችሁ በመኖር ልጆች ለወለዱት፣ አብረዋችሁ ለሚኖሩት የባዕድ አገር ሰዎች ርስት አድርጋችሁ አከፋፍሉ፤ እነሱም የአገሪቱ ተወላጆች እንደሆኑት እስራኤላውያን ይሆናሉ። እንደ እስራኤል ነገዶች ከእናንተ ጋር ርስት ያገኛሉ።
23 ከባዕድ አገር ለመጣው ሰው በሚኖርበት ነገድ ክልል ውስጥ ርስት ልትሰጡት ይገባል” ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።