ሕዝቅኤል 48:1-35
48 “ከሰሜናዊ ጫፍ አንስቶ የነገዶቹ ስም ይህ ነው፦ የዳን ድርሻ+ የሄትሎንን መንገድ ተከትሎ እስከ ሌቦሃማት*+ እንዲሁም በስተ ሰሜን በደማስቆ ድንበር በኩል፣ ከሃማት+ አጠገብ እስካለው እስከ ሃጻርኤናን ድረስ ይዘልቃል፤ ድርሻውም ከምሥራቁ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
2 የአሴር ድርሻ+ ከዳን ምድር ጋር የሚዋሰን ሲሆን ከምሥራቁ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
3 የንፍታሌም ድርሻ+ ከአሴር ምድር ጋር የሚዋሰን ሲሆን ከምሥራቁ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
4 የምናሴ ድርሻ+ ከንፍታሌም ምድር ጋር የሚዋሰን ሲሆን ከምሥራቁ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
5 የኤፍሬም ድርሻ ከምናሴ ምድር ጋር የሚዋሰን+ ሲሆን ከምሥራቁ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
6 የሮቤል ድርሻ ከኤፍሬም ምድር ጋር የሚዋሰን+ ሲሆን ከምሥራቁ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
7 የይሁዳ ድርሻ ከሮቤል ምድር ጋር የሚዋሰን+ ሲሆን ከምሥራቁ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
8 በይሁዳ ድንበር፣ ከምሥራቁ ወሰን አንስቶ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ መዋጮ አድርጋችሁ ለመስጠት የምትለዩት መሬት ወርዱ 25,000 ክንድ* ይሁን፤+ ደግሞም ይህ መሬት ከምሥራቁ ወሰን አንስቶ እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ርዝመቱ ከሌሎቹ ነገዶች ድርሻ ጋር እኩል ይሁን። መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል።
9 “መዋጮ አድርጋችሁ በመስጠት ለይሖዋ የምትለዩት መሬት ርዝመቱ 25,000 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 10,000 ክንድ ይሆናል።
10 ይህ ለካህናቱ መዋጮ ሆኖ የሚሰጥ ቅዱስ ስፍራ ይሆናል።+ በሰሜን በኩል 25,000 ክንድ፣ በምዕራብ በኩል 10,000፣ በምሥራቅ በኩል 10,000፣ በደቡብ በኩል ደግሞ 25,000 ይሆናል። የይሖዋ መቅደስ በመካከሉ ይሆናል።
11 ይህ የሳዶቅ ልጆች+ ለሆኑት የተቀደሱ ካህናት ይሆናል፤ እነሱ በእኔ ፊት ያለባቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል፤ እንዲሁም እስራኤላውያንና ሌዋውያን በባዘኑ ጊዜ+ ከእነሱ ጋር አልባዘኑም።
12 በሌዋውያን ድንበር በኩል፣ እጅግ ቅዱስ ተደርጎ ከተለየውና መዋጮ ሆኖ ከተሰጠው መሬት ላይ ድርሻ ያገኛሉ።
13 ሌዋውያኑ ከካህናቱ መሬት አጠገብ ርዝመቱ 25,000 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 10,000 ክንድ የሆነ ድርሻ ይኖራቸዋል። (አጠቃላይ ርዝመቱ 25,000፣ ወርዱ ደግሞ 10,000 ይሆናል።)
14 ምርጥ ከሆነው ከዚህ የመሬቱ ድርሻ ላይ የትኛውንም ቦታ መሸጥ፣ መለወጥ ወይም ለሌሎች አሳልፈው መስጠት የለባቸውም፤ ለይሖዋ የተቀደሰ ነውና።
15 “ደግሞም 25,000 ክንድ ከሆነው ወሰን አጠገብ የሚገኘው፣ ወርዱ 5,000 ክንድ የሆነው የቀረው ቦታ ለከተማዋ ቅዱስ ያልሆነ አገልግሎት+ ይኸውም ለመኖሪያ ቤትና ለግጦሽ መሬት ይውላል። ከተማዋ በመካከሉ ትሆናለች።+
16 የከተማዋም መጠን ይህ ነው፦ የሰሜኑ ወሰን 4,500፣ የደቡቡ ወሰን 4,500፣ የምሥራቁ ወሰን 4,500 እንዲሁም የምዕራቡ ወሰን 4,500 ክንድ ነው።
17 የከተማዋ የግጦሽ መሬት በስተ ሰሜን 250፣ በስተ ደቡብ 250፣ በስተ ምሥራቅ 250 እና በስተ ምዕራብ 250 ክንድ ይሆናል።
18 “የቀረው ድርሻ ርዝመቱ፣ መዋጮ ሆኖ ከተሰጠው ቅዱስ ስፍራ+ ጋር እኩል ይሆናል፤ ይኸውም በስተ ምሥራቅ 10,000፣ በስተ ምዕራብም 10,000 ክንድ ይሆናል። ርዝመቱ መዋጮ ሆኖ ከተሰጠው ቅዱስ ስፍራ ጋር እኩል ይሆናል፤ በዚያም የሚመረተው ከተማዋን ለሚያገለግሉ ምግብ ይሆናል።
19 ከተማዋን የሚያገለግሉ ከሁሉም የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ሰዎች መሬቱን ያርሳሉ።+
20 “በመዋጮ የተሰጠው መሬት በአጠቃላይ አራቱም ማዕዘኑ እኩል ሲሆን እያንዳንዱ ማዕዘን 25,000 ክንድ ነው። መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ቅዱስ ስፍራና የከተማዋ ይዞታ አድርጋችሁ ትለዩታላችሁ።
21 “መዋጮ ሆኖ ከተሰጠው ቅዱስ ስፍራና ከከተማዋ ይዞታ ግራና ቀኝ ያለው የቀረው ቦታ የአለቃው ይሆናል።+ ይህ ቦታ በመዋጮ ከተሰጠው መሬት በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ከሚገኙት 25,000 ክንድ ከሆኑት ወሰኖች አጠገብ ይሆናል። በአቅራቢያው ካሉት የነገዶቹ ድርሻዎች ጋር ይዋሰናል፤ ይህም ለአለቃው ይሆናል። መዋጮ ሆኖ የተሰጠው ቅዱስ ስፍራና የቤተ መቅደሱ መቅደስ በመካከሉ ይሆናል።
22 “የሌዋውያኑ ይዞታና የከተማዋ ይዞታ በአለቃው ክልል መካከል ይሆናል። የአለቃው ክልል በይሁዳ ድንበርና+ በቢንያም ድንበር መካከል ይሆናል።
23 “የቀሩትን ነገዶች በተመለከተ፣ የቢንያም ድርሻ ከምሥራቁ ወሰን እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።+
24 የስምዖን ድርሻ ከቢንያም ምድር ጋር የሚዋሰን+ ሲሆን ከምሥራቁ ወሰን እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
25 የይሳኮር ድርሻ+ ከስምዖን ምድር ጋር የሚዋሰን ሲሆን ከምሥራቁ ወሰን እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
26 የዛብሎን ድርሻ ከይሳኮር ምድር ጋር የሚዋሰን+ ሲሆን ከምሥራቁ ወሰን እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።+
27 የጋድ ድርሻ ከዛብሎን ምድር ጋር የሚዋሰን+ ሲሆን ከምሥራቁ ወሰን እስከ ምዕራቡ ወሰን ድረስ ነው።
28 በጋድ ወሰን በኩል ያለው ደቡባዊ ድንበር ከትዕማር+ እስከ የመሪባትቃዴስ ውኃዎች፣+ እስከ ደረቁ ወንዝና*+ እስከ ታላቁ ባሕር* ይዘልቃል።
29 “ለእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታከፋፍሏት ምድር ይህች ናት፤+ ይህም ድርሻቸው ይሆናል”+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።
30 “የከተማዋ መውጫዎች እነዚህ ይሆናሉ፦ በሰሜን በኩል ያለው 4,500 ክንድ ነው።+
31 “የከተማዋ በሮች በእስራኤል ነገዶች ስም ይሰየማሉ። በስተ ሰሜን ሦስት በሮች ያሉ ሲሆን አንዱ በር ለሮቤል፣ አንዱ በር ለይሁዳ፣ አንዱ በር ደግሞ ለሌዊ ይሆናል።
32 “ምሥራቃዊው አቅጣጫ 4,500 ክንድ ርዝመት የሚኖረው ሲሆን ሦስት በሮች ይኖሩታል፦ አንዱ በር ለዮሴፍ፣ አንዱ በር ለቢንያም፣ አንዱ በር ደግሞ ለዳን ይሆናል።
33 “ደቡባዊው አቅጣጫ 4,500 ክንድ ርዝመት የሚኖረው ሲሆን ሦስት በሮች ይኖሩታል፦ አንዱ በር ለስምዖን፣ አንዱ በር ለይሳኮር፣ አንዱ በር ደግሞ ለዛብሎን ይሆናል።
34 “ምዕራባዊው አቅጣጫ 4,500 ክንድ ርዝመት የሚኖረው ሲሆን ሦስት በሮች ይኖሩታል፦ አንዱ በር ለጋድ፣ አንዱ በር ለአሴር፣ አንዱ በር ደግሞ ለንፍታሌም ይሆናል።
35 “ዙሪያውን መጠኑ 18,000 ክንድ ይሆናል። ከዚያን ቀን ጀምሮ ከተማዋ ‘ይሖዋ በዚያ አለ’ ተብላ ትጠራለች።”+