ሕዝቅኤል 5:1-17
5 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ እንደ ፀጉር አስተካካይ ምላጭ የምትጠቀምበት ስለታም ሰይፍ ውሰድ። የራስህን ፀጉርና ጢምህን ተላጭ፤ ከዚያም ሚዛን ወስደህ ፀጉሩን መዝነውና ከፋፍለው።
2 የከበባው ጊዜ ሲፈጸም+ አንድ ሦስተኛውን በከተማዋ ውስጥ በእሳት ታቃጥለዋለህ። ከዚያም ሌላ አንድ ሦስተኛ ወስደህ በከተማዋ ዙሪያ በሰይፍ ትመታዋለህ፤+ የመጨረሻውንም አንድ ሦስተኛ ለነፋስ ትበትነዋለህ፤ እኔም እነሱን ለማሳደድ ሰይፍ እመዛለሁ።+
3 “ደግሞም ከፀጉሮቹ ላይ ጥቂት ወስደህ በልብስህ እጥፋት* ቋጥራቸው።
4 የተወሰነውን ደግሞ ወስደህ እሳት ውስጥ ጨምረው፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት አቃጥለው። ይህ እሳት ወጥቶ በእስራኤል ቤት ሁሉ ይሰራጫል።+
5 “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህች ኢየሩሳሌም ናት። አገሮችን በዙሪያዋ አድርጌ፣ በብሔራት መካከል አስቀምጫታለሁ።
6 እሷ ግን ከብሔራትና በዙሪያዋ ካሉ አገሮች ሁሉ የባሰ ክፋት በመሥራት በድንጋጌዎቼና ባወጣኋቸው ደንቦች ላይ ዓምፃለች።+ ሕዝቡ ድንጋጌዎቼን ወደ ጎን ገሸሽ አድርጓልና፤ ደንቦቼንም አክብሮ አልተመላለሰም።’
7 “ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዙሪያችሁ ካሉት ብሔራት ይበልጥ አስቸጋሪ በመሆናችሁ፣ ደንቦቼን አክብራችሁ ባለመመላለሳችሁ ወይም ድንጋጌዎቼን ባለመጠበቃችሁ፣ ይልቁንም በዙሪያችሁ ያሉትን ብሔራት ድንጋጌዎች በመከተላችሁ፣+
8 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንቺ ከተማ ሆይ፣ በአንቺ ላይ ተነስቻለሁ፤+ ደግሞም እኔ ራሴ በብሔራት ፊት በመካከልሽ ፍርዴን አስፈጽማለሁ።+
9 በአስጸያፊ ድርጊቶችሽ ሁሉ የተነሳ ከዚህ በፊት ፈጽሞ ያላደረግኩትን፣ ከዚህም በኋላ የማልደግመውን በአንቺ ላይ አደርጋለሁ።+
10 “‘“ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ፤+ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ በመካከልሽ ፍርዴን አስፈጽማለሁ፤ ከአንቺ የቀሩትንም በሙሉ በየአቅጣጫው* እበትናቸዋለሁ።”’+
11 “‘ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ‘በአስጸያፊ ጣዖቶችሽ ሁሉና ጸያፍ በሆኑ ድርጊቶችሽ ሁሉ መቅደሴን ስላረከስሽ፣+ እኔ ራሴ እተውሻለሁ፤* ዓይኔ አያዝንም ደግሞም አልራራም።+
12 ከአንቺም አንድ ሦስተኛው በቸነፈር* ይሞታል ወይም በመካከልሽ በረሃብ ያልቃል። ሌላ አንድ ሦስተኛ ደግሞ በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃል።+ የመጨረሻውን አንድ ሦስተኛ ደግሞ በየአቅጣጫው* እበትነዋለሁ፤ እነሱንም ለማሳደድ ሰይፍ እመዛለሁ።+
13 ከዚያም ቁጣዬ ይፈጸማል፤ በእነሱም ላይ የነደደው ቁጣዬ ይበርዳል፤ እኔም እረካለሁ።+ በእነሱም ላይ ቁጣዬን ፈጽሜ ባወረድኩ ጊዜ፣ እኔ ብቻ መመለክ የምፈልገው፣+ እኔ ይሖዋ ይህን እንደተናገርኩ ያውቃሉ።
14 “‘በዙሪያሽ ባሉ ብሔራት መካከል እንዲሁም በአጠገብሽ በሚያልፉ ሁሉ ፊት ባድማና መሳለቂያ አደርግሻለሁ።+
15 በቁጣ፣ በንዴትና በኃይለኛ ቅጣት የፍርድ እርምጃ ስወስድብሽ በዙሪያሽ ባሉ ብሔራት ዘንድ መሳለቂያና መዘባበቻ+ ደግሞም የማስጠንቀቂያ ምሳሌና ማስፈራሪያ ትሆኛለሽ። እኔ ይሖዋ ይህን ተናግሬአለሁ።
16 “‘እነሱን ለማጥፋት ገዳይ የሆኑ የረሃብ ፍላጻዎችን እሰድባቸዋለሁ። የምሰዳቸው የረሃብ ፍላጻዎች ያጠፏችኋል።+ የምግብ አቅርቦታችሁ እንዲቋረጥ በማድረግ* ረሃቡን አባብሳለሁ።+
17 በእናንተ ላይ ረሃብንና አደገኛ የዱር አራዊትን እሰዳለሁ፤+ እነሱም የወላድ መሃን ያደርጓችኋል። ቸነፈርና ደም መፋሰስ ያጥለቀልቋችኋል፤ ሰይፍም አመጣባችኋለሁ።+ እኔ ይሖዋ ይህን ተናግሬአለሁ።’”