ሕዝቅኤል 9:1-11
9 ከዚያም በጆሮዬ እየሰማሁ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከተማዋን የሚቀጡት፣ እያንዳንዳቸው አጥፊ መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው እንዲመጡ ጥሯቸው!” አለ።
2 እኔም እያንዳንዳቸው በእጃቸው የማጥፊያ መሣሪያ የያዙ ስድስት ሰዎች በሰሜን ትይዩ ባለው በላይኛው በር+ በኩል ሲመጡ አየሁ፤ ከእነሱም ጋር በፍታ የለበሰ፣ በወገቡ ላይም የጸሐፊ የቀለም ቀንድ* የያዘ አንድ ሰው ነበር፤ እነሱም መጥተው ከመዳብ በተሠራው መሠዊያ+ አጠገብ ቆሙ።
3 ከዚያም የእስራኤል አምላክ ክብር፣+ አርፎበት ከነበረው ከኪሩቦቹ በላይ ተነስቶ ወደ ቤተ መቅደሱ በር ደጃፍ ሄደ፤+ አምላክም በፍታ የለበሰውንና በወገቡ ላይ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘውን ሰው ጠራው።
4 ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “በከተማዋ መካከል ይኸውም በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፤ በከተማዋ ውስጥ እየተፈጸሙ ባሉት አስጸያፊ ነገሮች+ ሁሉ እያዘኑና እየቃተቱ ባሉት ሰዎች+ ግንባር ላይም ምልክት አድርግ።”
5 ሌሎቹን ደግሞ እኔ እየሰማሁ እንዲህ አላቸው፦ “እሱን ተከትላችሁ በከተማዋ መካከል እለፉ፤ ሰዉንም ግደሉ። ዓይናችሁ አይዘን፤ ደግሞም አትራሩ።+
6 ሽማግሌውን፣ ወጣቱን፣ ድንግሊቱን፣ ሕፃኑንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ።+ ምልክቱ ወዳለበት ወደ ማንኛውም ሰው ግን አትቅረቡ።+ ከመቅደሴም ጀምሩ።”+ ስለዚህ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት በነበሩት ሽማግሌዎች ጀመሩ።+
7 ከዚያም “ቤተ መቅደሱን አርክሱ፤ ግቢዎቹንም ሬሳ በሬሳ አድርጓቸው።+ ሂዱ!” አላቸው። ስለዚህ ሄደው የከተማዋን ሕዝብ ገደሉ።
8 እነሱ ሰዉን እየገደሉ ሳሉ ብቻዬን ቀረሁ፤ በግንባሬም ተደፍቼ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ወዮ! በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣህን በማፍሰስ የእስራኤልን ቀሪዎች ሁሉ ልታጠፋ ነው?” በማለት ጮኽኩ።+
9 እሱም እንዲህ አለኝ፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ቤት በደል እጅግ በጣም ታላቅ ነው።+ ምድሪቱ በደም ተጥለቅልቃለች፤+ ከተማዋም በክፋት ተሞልታለች።+ ‘ይሖዋ ምድሪቱን ትቷታል፤ ይሖዋም አያይም’ ይላሉና።+
10 እኔ ግን ዓይኔ አያዝንም፤ ደግሞም አልራራም።+ የተከተሉት መንገድ የሚያስከትለውን መዘዝ በራሳቸው ላይ አመጣባቸዋለሁ።”
11 ከዚያም በፍታ የለበሰውና በወገቡ ላይ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ተመልሶ መጥቶ “ልክ እንዳዘዝከኝ አድርጌአለሁ” አለ።
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “የጸሐፊ ቀለም መያዣ።”