መሳፍንት 1:1-36

  • ይሁዳና ስምዖን ድል አድርገው የያዟቸው ግዛቶች (1-20)

  • ኢያቡሳውያን በኢየሩሳሌም መኖራቸውን ቀጠሉ (21)

  • ዮሴፍ ቤቴልን ያዘ (22-26)

  • ከነአናውያን ሙሉ በሙሉ ከምድሪቱ አልተባረሩም (27-36)

1  ኢያሱ+ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን* “ከከነአናውያን ጋር ለመዋጋት ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” በማለት ይሖዋን ጠየቁ።+  ይሖዋም “ይሁዳ ይውጣ።+ እኔም ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ”* አለ።  ከዚያም ይሁዳ ወንድሙን ስምዖንን “ከከነአናውያን ጋር ለመዋጋት ወደተመደበልኝ ርስት* + አብረኸኝ ውጣ። እኔም ደግሞ በዕጣ ወደደረሰህ ርስት አብሬህ እሄዳለሁ” አለው። ስለዚህ ስምዖን አብሮት ሄደ።  ይሁዳም በወጣ ጊዜ ይሖዋ ከነአናውያንንና ፈሪዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤+ በመሆኑም ቤዜቅ ላይ 10,000 ሰዎችን ድል አደረጉ።  አዶኒቤዜቅን ቤዜቅ ላይ ባገኙት ጊዜ በዚያ ከእሱ ጋር ተዋጉ፤ ከነአናውያንንና+ ፈሪዛውያንንም+ ድል አደረጉ።  አዶኒቤዜቅም በሸሸ ጊዜ አሳደው ያዙት፤ ከዚያም የእጆቹንና የእግሮቹን አውራ ጣቶች ቆረጡ።  አዶኒቤዜቅም እንዲህ አለ፦ “የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የተቆረጡባቸው ከገበታዬ ሥር ሆነው ፍርፋሪ የሚለቃቅሙ 70 ነገሥታት ነበሩ። አምላክም ልክ እኔ እንዳደረግኩት አደረገብኝ።” ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤+ እሱም በዚያ ሞተ።  በተጨማሪም የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ወግተው በቁጥጥር ሥር አዋሏት፤+ ከተማዋንም በሰይፍ መትተው በእሳት አቃጠሏት።  ከዚያም የይሁዳ ሰዎች በተራራማው አካባቢ፣ በኔጌብና በሸፌላ+ ከሚኖሩት ከነአናውያን ጋር ለመዋጋት ወረዱ። 10  በመሆኑም ይሁዳ በኬብሮን ይኖሩ በነበሩት ከነአናውያን ላይ ዘመተ (ኬብሮን ቀደም ሲል ቂርያትአርባ ተብላ ትጠራ ነበር)፤ እነሱም ሸሻይን፣ አሂማንን እና ታልማይን መቱ።+ 11  ከዚያም ተነስተው በደቢር ነዋሪዎች ላይ ዘመቱ።+ (ደቢር ቀደም ሲል ቂርያትሰፈር ትባል ነበር።)+ 12  ካሌብም+ “ቂርያትሰፈርን መትቶ በቁጥጥር ሥር ላደረጋት ሰው ሴት ልጄን አክሳን እድርለታለሁ” አለ።+ 13  የካሌብ ታናሽ ወንድም የሆነው የቀናዝ+ ልጅ ኦትኒኤልም+ ከተማዋን በቁጥጥር ሥር አደረጋት። ስለሆነም ካሌብ ሴት ልጁን አክሳን ዳረለት። 14  እሷም ወደ ባሏ ቤት እየሄደች ሳለ ባሏን ከአባቷ መሬት እንዲጠይቅ ወተወተችው። ከዚያም ከአህያዋ ላይ ወረደች።* በዚህ ጊዜ ካሌብ “ምን ፈለግሽ?” ሲል ጠየቃት። 15  እሷም “የሰጠኸኝ በስተ ደቡብ* ያለ ቁራሽ መሬት ስለሆነ እባክህ ባርከኝ፤ ጉሎትማይምንም* ስጠኝ” አለችው። በመሆኑም ካሌብ ላይኛውን ጉሎት እና ታችኛውን ጉሎት ሰጣት። 16  የቄናዊው+ የሙሴ አማት+ ዘሮች ከይሁዳ ሰዎች ጋር በመሆን ከዘንባባ ዛፎች ከተማ+ ወጥተው ከአራድ+ በስተ ደቡብ ወደሚገኘው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ አቀኑ። እነሱም ወደዚያ ሄደው ከሕዝቡ ጋር መኖር ጀመሩ።+ 17  ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር በመዝመት በጸፋት በሚኖሩት ከነአናውያን ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ ከተማዋንም ሙሉ በሙሉ ደመሰሱ።+ በመሆኑም ከተማዋን ሆርማ* + ብለው ሰየሟት። 18  ከዚያም ይሁዳ ጋዛንና+ ግዛቶቿን፣ አስቀሎንንና+ ግዛቶቿን እንዲሁም ኤቅሮንንና+ ግዛቶቿን ተቆጣጠረ። 19  ይሖዋ ከይሁዳ ጋር ስለነበር ይሁዳ ተራራማውን አካባቢ ወረሰ፤ በሜዳው* ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ግን ማባረር አልቻሉም፤ ምክንያቱም እነሱ የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው የጦር ሠረገሎች* ነበሯቸው።+ 20  ሙሴ ቃል በገባው መሠረት ኬብሮንን ለካሌብ ሰጡት፤+ እሱም ሦስቱን የኤናቅ ልጆች ከዚያ አባረራቸው።+ 21  ቢንያማውያን ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያን ከዚያ አላስወጧቸውም ነበር፤ በመሆኑም ኢያቡሳውያኑ ከቢንያማውያን ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም አብረው ይኖራሉ።+ 22  በዚህ ጊዜ የዮሴፍ ቤት+ ቤቴልን ለመውጋት ወጣ፤ ይሖዋም ከእነሱ ጋር ነበር።+ 23  የዮሴፍ ቤት ቤቴልን እየሰለለ ነበር (ቤቴል ቀደም ሲል ሎዛ ተብላ ትጠራ ነበር)፤+ 24  ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማዋ ሲወጣ አዩ። በመሆኑም “እባክህ ወደ ከተማዋ የሚያስገባውን መንገድ አሳየን፤ እኛም ደግነት እናደርግልሃለን”* አሉት። 25  በመሆኑም ሰውየው ወደ ከተማዋ የሚያስገባውን መንገድ አሳያቸው፤ እነሱም የከተማዋን ነዋሪዎች በሰይፍ መቱ፤ ይሁንና ሰውየውንና ቤተሰቡን በሙሉ ነፃ ለቀቋቸው።+ 26  ሰውየውም ወደ ሂታውያን ምድር ሄዶ ከተማ ገነባ፤ ከተማዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ስሟ ይኸው ነው። 27  ምናሴ ቤትሼንንና በሥሯ* ያሉትን ከተሞች፣ ታአናክንና+ በሥሯ ያሉትን ከተሞች፣ የዶርን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች፣ የይብለአምን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች እንዲሁም የመጊዶን ነዋሪዎችና በሥሯ ያሉትን ከተሞች አልወረሰም ነበር።+ ከነአናውያን ይህን ምድር ላለመልቀቅ ቆርጠው ነበር። 28  እስራኤላውያንም እያየሉ በሄዱ ጊዜ ከነአናውያንን የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው+ እንጂ ሙሉ በሙሉ አላባረሯቸውም።+ 29  ኤፍሬምም ቢሆን በጌዜር ይኖሩ የነበሩትን ከነአናውያን አላባረራቸውም። ከነአናውያን በጌዜር አብረዋቸው ይኖሩ ነበር።+ 30  ዛብሎንም የቂትሮንን ነዋሪዎችና የናሃሎልን+ ነዋሪዎች አላባረራቸውም። ከነአናውያን አብረዋቸው ይኖሩ የነበረ ሲሆን የግዳጅ ሥራም እንዲሠሩ ተገደው ነበር።+ 31  አሴር የአኮን ነዋሪዎች እንዲሁም የሲዶናን፣+ የአህላብን፣ የአክዚብን፣+ የሄልባን፣ የአፊቅን+ እና የሬሆብን+ ነዋሪዎች አላባረራቸውም። 32  በመሆኑም አሴራውያን በምድሩ ይኖሩ ከነበሩት ከነአናውያን ጋር አብረው መኖራቸውን ቀጠሉ፤ ምክንያቱም አላባረሯቸውም ነበር። 33  ንፍታሌም የቤትሼሜሽን ነዋሪዎችና የቤትአናትን ነዋሪዎች+ አላባረራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ በምድሩ ይኖሩ ከነበሩት ከነአናውያን ጋር አብረው ኖሩ።+ የቤትሼሜሽ ነዋሪዎችና የቤትአናት ነዋሪዎች የግዳጅ ሥራ ይሠሩላቸው ነበር። 34  ዳናውያን ወደ ሜዳው* እንዲወርዱ አሞራውያን ስላልፈቀዱላቸው በተራራማው አካባቢ ተወስነው ለመኖር ተገደዱ።+ 35  አሞራውያን የሃሬስ ተራራን፣ አይሎንን+ እና ሻአልቢምን+ አንለቅም በማለት በዚያ መኖራቸውን ቀጠሉ። ይሁንና የዮሴፍ ቤት ኃይሉ* እየጨመረ* በመጣ ጊዜ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ተገደዱ። 36  የአሞራውያን ክልል ከአቅራቢም አቀበትና+ ከሴላ አንስቶ ወደ ላይ ያለው ነበር።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ሰጥቼዋለሁ።”
ቃል በቃል “ወደ ዕጣዬ።”
“በአህያዋ ላይ እያለች አጨበጨበች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በኔጌብ።”
“የውኃ ምንጮች” የሚል ትርጉም አለው።
“ለጥፋት መዳረግ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”
ቃል በቃል “የብረት ሠረገሎች።”
ቃል በቃል “ታማኝ ፍቅር እናሳይሃለን።”
ወይም “በዙሪያዋ።”
ወይም “ረባዳማው ሜዳ።”
ቃል በቃል “እጁ።”
ቃል በቃል “እየከበደ።”