መሳፍንት 11:1-40

  • መስፍኑ ዮፍታሔ ከአባቱ ቤት ተባረረ፤ በኋላም መሪ ሆነ (1-11)

  • ዮፍታሔ ለአሞናውያን ንጉሥ መልእክት ላከ (12-28)

  • የዮፍታሔ ስእለትና ሴት ልጁ (29-40)

    • የዮፍታሔ ልጅ ሳታገባ ኖረች (38-40)

11  ጊልያዳዊው ዮፍታሔ+ ኃያል ተዋጊ ነበር፤ እሱም የአንዲት ዝሙት አዳሪ ልጅ የነበረ ሲሆን አባቱ ጊልያድ ነበር።  ይሁንና የጊልያድ ሚስትም ለጊልያድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት። የዚህችኛዋ ሚስቱ ልጆች ሲያድጉም ዮፍታሔን “አንተ ከሌላ ሴት የተወለድክ ስለሆንክ በአባታችን ቤት ምንም ውርሻ አይኖርህም” በማለት አባረሩት።  በመሆኑም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ በጦብ ምድር መኖር ጀመረ። ሥራ ፈት ሰዎችም ከእሱ ጋር በመተባበር ተከተሉት።  ከተወሰነ ጊዜ በኋላም አሞናውያን ከእስራኤላውያን ጋር ተዋጉ።+  አሞናውያን ከእስራኤላውያን ጋር በሚዋጉበት ጊዜ የጊልያድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር መልሰው ለማምጣት ወዲያውኑ ወደዚያ ሄዱ።  ዮፍታሔንም “አሞናውያንን መውጋት እንድንችል መጥተህ አዛዣችን ሁን” አሉት።  ዮፍታሔ ግን የጊልያድን ሽማግሌዎች “እኔን እጅግ ከመጥላታችሁ የተነሳ ከአባቴ ቤት ያባረራችሁኝ እናንተ አይደላችሁም?+ ታዲያ አሁን ጭንቅ ውስጥ ስትገቡ ወደ እኔ የምትመጡት ለምንድን ነው?” አላቸው።  በዚህ ጊዜ የጊልያድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን እንዲህ አሉት፦ “አሁን ወደ አንተ ተመልሰን የመጣነውም ለዚህ ነው። ከእኛ ጋር አብረኸን በመሄድ ከአሞናውያን ጋር የምትዋጋ ከሆነ ለጊልያድ ነዋሪዎች በሙሉ መሪ ትሆናለህ።”+  ዮፍታሔም የጊልያድን ሽማግሌዎች “እንግዲህ ከአሞናውያን ጋር እንድዋጋ ወደዚያ ብትመልሱኝና ይሖዋ እነሱን ድል ቢያደርግልኝ በእርግጥ እኔ መሪያችሁ እሆናለሁ!” አላቸው። 10  የጊልያድ ሽማግሌዎችም ዮፍታሔን “እንዳልከው ካላደረግን ይሖዋ በመካከላችን ምሥክር* ይሁን” አሉት። 11  በመሆኑም ዮፍታሔ ከጊልያድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም መሪና አዛዥ አደረገው። ዮፍታሔም የተናገረውን ነገር ሁሉ በምጽጳ+ በይሖዋ ፊት ደገመው። 12  ከዚያም ዮፍታሔ ለአሞናውያን+ ንጉሥ “ምድሬን ልትወጋ የመጣኸው ከእኔ ጋር ምን ጠብ ቢኖርህ ነው?”* ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞች ላከ። 13  የአሞናውያን ንጉሥም የዮፍታሔን መልእክተኞች እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ያደረግኩት እስራኤል ከግብፅ በወጣበት ጊዜ ከአርኖን+ አንስቶ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ+ ድረስ ያለውን መሬቴን ስለወሰደብኝ ነው።+ አሁንም መሬቴን በሰላም መልሱልኝ።” 14  ዮፍታሔ ግን መልእክተኞቹን እንደገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ በመላክ 15  እንዲህ አለው፦ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤል የሞዓባውያንን+ ምድርና የአሞናውያንን+ ምድር አልወሰደም፤ 16  ምክንያቱም እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ ጊዜ በምድረ በዳው አልፈው እስከ ቀይ ባሕርና+ እስከ ቃዴስ+ ድረስ መጡ። 17  ከዚያም እስራኤል ለኤዶም+ ንጉሥ “እባክህ ምድርህን አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን” ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ላከ፤ የኤዶም ንጉሥ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። ለሞዓብም+ ንጉሥ መልእክት ላኩ፤ እሱም ቢሆን በዚህ ሐሳብ አልተስማማም። ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ+ ተቀመጠ። 18  በምድረ በዳው በተጓዙበት ጊዜ በኤዶም ምድርና በሞዓብ ምድር ዳርቻ አልፈው ሄዱ።+ ከሞዓብ ምድር በስተ ምሥራቅ ተጉዘውም+ በአርኖን ክልል ሰፈሩ፤ ወደ ሞዓብ ወሰንም አልገቡም፤+ ምክንያቱም አርኖን የሞዓብ ወሰን ነበር። 19  “‘ከዚያም እስራኤል ወደ አሞራውያን ንጉሥ ማለትም ወደ ሃሽቦን ንጉሥ ወደ ሲሖን መልእክተኞችን ላከ፤ እስራኤልም “እባክህ ምድርህን አቋርጠን ወደ ገዛ ስፍራችን እንድናልፍ ፍቀድልን” አለው።+ 20  ሲሖን ግን በግዛቱ አቋርጦ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ በመሆኑም ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት ሰብስቦ በያሃጽ ሰፈረ፤ ከእስራኤልም ጋር ውጊያ ገጠመ።+ 21  በዚህ ጊዜ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሲሖንንና ሕዝቡን ሁሉ ለእስራኤላውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ በመሆኑም ድል አደረጓቸው፤ እስራኤላውያንም በዚያ የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሱ።+ 22  በዚህ መንገድ ከአርኖን አንስቶ እስከ ያቦቅ እንዲሁም ከምድረ በዳው አንስቶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን የአሞራውያንን ግዛት በሙሉ ወረሱ።+ 23  “‘እንግዲህ አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤላውያን ፊት ያባረራቸው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ነው፤+ እና አሁን አንተ ደግሞ እነሱን ልታባርራቸው ነው? 24  አንተስ ብትሆን አምላክህ ከሞሽ+ እንድትወርሰው የሰጠህን ሁሉ አትወርስም? ስለዚህ እኛም አምላካችን ይሖዋ ከፊታችን ያባረራቸውን ሁሉ እናባርራለን።+ 25  ደግሞስ አንተ የሞዓብ ንጉሥ ከሆነው ከሴፎር ልጅ ከባላቅ+ ትበልጣለህ? ለመሆኑ እሱ እስራኤልን ለመገዳደር ሞክሮ ያውቃል? ወይስ ከእነሱ ጋር ውጊያ ገጥሞ ያውቃል? 26  እስራኤል በሃሽቦንና በሥሯ* ባሉት ከተሞች፣+ በአሮዔርና በሥሯ ባሉት ከተሞች እንዲሁም በአርኖን ሸለቆ ዳርቻ በሚገኙት ከተሞች ሁሉ ለ300 ዓመት ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ እነዚያን ቦታዎች መልሳችሁ ለመውሰድ ያልሞከራችሁት ለምንድን ነው?+ 27  እንግዲህ እኔ ምንም የበደልኩህ ነገር የለም፤ አንተም ብትሆን በእኔ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መነሳትህ ተገቢ አይደለም። ፈራጁ ይሖዋ+ በእስራኤል ሕዝብና በአሞን ሕዝብ መካከል ዛሬ ይፍረድ።’” 28  የአሞናውያን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከበትን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። 29  የይሖዋ መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤+ እሱም በጊልያድ ወደምትገኘው ወደ ምጽጳ+ ለመሄድ ጊልያድንና ምናሴን አቋርጦ አለፈ፤ በጊልያድ ከምትገኘው ምጽጳም ተነስቶ ወደ አሞናውያን ሄደ። 30  ከዚያም ዮፍታሔ እንዲህ ሲል ለይሖዋ ስእለት ተሳለ፦+ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ከሰጠኸኝ 31  ከአሞናውያን ዘንድ በሰላም በምመለስበት ጊዜ ሊቀበለኝ ከቤቴ በር የሚወጣው ማንኛውም ሰው የይሖዋ ይሆናል፤+ እኔም የሚቃጠል መባ አድርጌ አቀርበዋለሁ።”+ 32  በመሆኑም ዮፍታሔ ከአሞናውያን ጋር ለመዋጋት ሄደ፤ ይሖዋም እነሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው። 33  እሱም ከአሮዔር አንስቶ እስከ ሚኒት ድረስ ማለትም 20 ከተሞችን፣ ከዚያም አልፎ እስከ አቤልከራሚም ድረስ ፈጽሞ ደመሰሳቸው። በዚህ መንገድ አሞናውያን ለእስራኤላውያን ተገዙ። 34  በመጨረሻም ዮፍታሔ በምጽጳ+ ወደሚገኘው ቤቱ መጣ፤ በዚህ ጊዜ ሴት ልጁ አታሞ እየመታችና እየጨፈረች ልትቀበለው ወጣች! ልጁ እሷ ብቻ ነበረች። ከእሷ ሌላ ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም። 35  እሱም ባያት ጊዜ ልብሱን ቀደደ፤ እንዲህም አለ፦ “ወዮ፣ ልጄ! ልቤን ሰበርሽው፤* እንግዲህ ከቤት የማስወጣው አንቺን ነው። አንዴ ለይሖዋ ቃል ገብቻለሁ፤ ልመልሰውም አልችልም።”+ 36  እሷም እንዲህ አለችው፦ “አባቴ ሆይ፣ ለይሖዋ ቃል ከገባህ፣ የገባኸውን ቃል በእኔ ላይ ፈጽምብኝ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ጠላቶችህን አሞናውያንን ተበቅሎልሃል።” 37  እሷም በመቀጠል አባቷን እንዲህ አለችው፦ “እንዲህ ይደረግልኝ፦ ለሁለት ወር ያህል ብቻዬን ልሁን፤ ወደ ተራሮቹም ልሂድ፤ ከሴት ባልንጀሮቼም ጋር ሆኜ ስለ ድንግልናዬ ላልቅስ።”* 38  በዚህ ጊዜ “እሺ ሂጂ!” አላት፤ ለሁለት ወርም አሰናበታት፤ እሷም ስለ ድንግልናዋ ለማልቀስ ከባልንጀሮቿ ጋር ወደ ተራሮቹ ሄደች። 39  ከሁለት ወር በኋላም ወደ አባቷ ተመለሰች፤ አባቷም እሷን በተመለከተ የተሳለውን ስእለት ፈጸመ።+ እሷም ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽማ አታውቅም ነበር። ይህም በእስራኤል ውስጥ ልማድ* ሆነ፦ 40  የእስራኤል ወጣት ሴቶች የጊልያዳዊውን የዮፍታሔን ሴት ልጅ ለማመስገን በየዓመቱ ለአራት ቀን ያህል ይሄዱ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “አዳማጭ።”
ቃል በቃል “ለእኔም ሆነ ለአንተ ምንድን ነው?”
ወይም “በዙሪያዋ።”
ቃል በቃል “በጣም ዝቅ አደረግሽኝ።”
ወይም “ከእንግዲህ ስለማላገባ ከጓደኞቼ ጋር ላልቅስ።”
ወይም “ሥርዓት።”