መሳፍንት 14:1-20

  • መስፍኑ ሳምሶን ፍልስጤማዊት ሴት ማግባት ፈለገ (1-4)

  • ሳምሶን በይሖዋ መንፈስ እርዳታ አንበሳ ገደለ (5-9)

  • የሳምሶን እንቆቅልሽ (10-19)

  • የሳምሶን ሚስት ለሌላ ሰው ተዳረች (20)

14  ከዚያም ሳምሶን ወደ ቲምና ወረደ፤ በቲምናም አንዲት ፍልስጤማዊት ሴት አየ።  ወጥቶም አባቱንና እናቱን “በቲምና ያለች አንዲት ፍልስጤማዊት ዓይኔን ማርካዋለች፤ እሷን እንድታጋቡኝ እፈልጋለሁ” አላቸው።  ሆኖም አባቱና እናቱ “ከዘመዶችህና ከእኛ ሕዝብ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት አጥተህ ነው?+ የግድ ሄደህ ካልተገረዙት ፍልስጤማውያን መካከል ሚስት ማግባት አለብህ?” አሉት። ሳምሶን ግን አባቱን “ልቤን የማረከችው እሷ ስለሆነች እሷን አጋባኝ” አለው።  በዚያን ጊዜ በእስራኤል ላይ ይገዙ የነበሩት ፍልስጤማውያን ስለነበሩ አባቱና እናቱ ነገሩ ከይሖዋ መሆኑንና እሱም ከፍልስጤማውያን ጋር ግጭት የሚፈጠርበትን አጋጣሚ እየፈለገ እንደነበር አላወቁም።+  ስለዚህ ሳምሶን ከአባቱና ከእናቱ ጋር ወደ ቲምና ወረደ። በቲምና ወዳለው የወይን እርሻ ሲደርስም አንድ ደቦል አንበሳ እያገሳ መጣበት።  ከዚያም የይሖዋ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤+ አንድ ሰው በባዶ እጁ የፍየልን ጠቦት ለሁለት እንደሚገነጥል እሱም አንበሳውን ለሁለት ገነጠለው። ሆኖም ያደረገውን ነገር ለአባቱም ሆነ ለእናቱ አልነገራቸውም።  ከዚያም ወርዶ ሴቲቱን አነጋገራት፤ አሁንም የሳምሶን ልብ በእሷ እንደተማረከ ነበር።+  ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ወደ ቤቱ ሊያመጣት+ ተመልሶ ሲሄድ የአንበሳውን በድን ለማየት ከመንገድ ዞር አለ፤ በአንበሳውም በድን ውስጥ የንብ መንጋና ማር ነበር።  እሱም ማሩን ዛቅ አድርጎ መዳፉ ላይ በማድረግ በመንገድ ላይ እየበላ ሄደ። ከአባቱና ከእናቱ ጋር እንደተገናኘም ከማሩ ሰጣቸው፤ እነሱም በሉ። ሆኖም ማሩን የወሰደው ከአንበሳ በድን ውስጥ እንደሆነ አልነገራቸውም ነበር። 10  አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ፤ ሳምሶንም በዚያ ግብዣ አዘጋጀ፤ ምክንያቱም ወጣቶች እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበራቸው። 11  እነሱም ባዩት ጊዜ አብረውት እንዲሆኑ 30 ሚዜዎችን አመጡ። 12  ሳምሶንም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ አንድ እንቆቅልሽ ልንገራችሁ። ግብዣው በሚቆይበት በዚህ ሰባት ቀን ውስጥ ፍቺውን ካወቃችሁና መልሱን ከነገራችሁኝ 30 የበፍታ ልብሶችንና 30 የክት ልብሶችን እሰጣችኋለሁ። 13  መልሱን ልትነግሩኝ ካልቻላችሁ ግን 30 የበፍታ ልብሶችንና 30 የክት ልብሶችን ትሰጡኛላችሁ።” እነሱም “እንቆቅልሽህን ንገረን፤ እስቲ እንስማው” አሉት። 14  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከበላተኛው መብል ወጣ፤ ከብርቱውም ውስጥ ጣፋጭ ነገር ወጣ።”+ እነሱም እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቆቅልሹን ሊፈቱት አልቻሉም። 15  በአራተኛውም ቀን የሳምሶንን ሚስት እንዲህ አሏት፦ “ባልሽን አታለሽ+ የእንቆቅልሹን ፍቺ እንዲነግረን አድርጊ። አለዚያ አንቺንም ሆነ የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን። እዚህ የጋበዛችሁን ንብረታችንን ልትዘርፉን ነው?” 16  የሳምሶንም ሚስት ላዩ ላይ እያለቀሰች “አንተ ትጠላኛለህ፤ ደግሞም አትወደኝም።+ ለሕዝቤ አንድ እንቆቅልሽ ነግረሃቸው ነበር፤ መልሱን ግን ለእኔ አልነገርከኝም” አለችው። እሱም በዚህ ጊዜ “እንዴ፣ ለገዛ አባቴና እናቴ እንኳ አልነገርኳቸውም! ታዲያ ለአንቺ ለምን እነግርሻለሁ?” አላት። 17  እሷ ግን ግብዣው እስከቆየበት እስከ ሰባተኛው ቀን ድረስ ስታለቅስበት ሰነበተች። በመጨረሻም አጥብቃ ስለነዘነዘችው በሰባተኛው ቀን ነገራት። እሷም የእንቆቅልሹን ፍቺ ለሕዝቧ ነገረች።+ 18  የከተማዋም ሰዎች ሳምሶንን በሰባተኛው ቀን ፀሐይዋ ከመጥለቋ በፊት* እንዲህ አሉት፦ “ከማር ይልቅ የሚጣፍጥ ምን ተገኝቶ?ከአንበሳስ ይልቅ የበረታ ከየት መጥቶ?”+ እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “በጊደሬ ባላረሳችሁ፣+እንቆቅልሼን ባልፈታችሁ።” 19  ከዚያም የይሖዋ መንፈስ ለሳምሶን ኃይል ሰጠው፤+ እሱም ወደ አስቀሎን+ ወርዶ ከሰዎቻቸው መካከል 30ውን ገደለ፤ ልብሳቸውንም ገፎ እንቆቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጣቸው።+ ቁጣው እንደነደደም ወደ አባቱ ቤት ወጣ። 20  የሳምሶንም ሚስት+ አብረውት ከነበሩት ሚዜዎች ለአንዱ ተዳረች።+

የግርጌ ማስታወሻ

“ወደ ውስጠኛው ክፍል ከመግባቱ በፊት” ማለትም ሊሆን ይችላል።