መሳፍንት 18:1-31

  • ዳናውያን ተጨማሪ ርስት ፈለጉ (1-31)

    • ዳናውያን የሚክያስን ጣዖታትና ካህን ወሰዱ (14-20)

    • ላይሽን ያዟት፤ ዳን ብለው ጠሯት (27-29)

    • ዳን ውስጥ የጣዖት አምልኮ ተስፋፋ (30, 31)

18  በዚያ ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም።+ በዚያ ጊዜ የዳናውያን ነገድ+ የሚሰፍርበት ርስት እየፈለገ ነበር፤ ምክንያቱም ዳናውያን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልተሰጣቸውም ነበር።+  ዳናውያን ከቤተሰባቸው መካከል ብቃት ያላቸውን አምስት ወንዶች መርጠው ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲቃኙ ከጾራና ከኤሽታዖል+ ላኳቸው። እነሱንም “ሂዱ፣ ምድሪቱን ቃኙ” አሏቸው። እነሱም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ወደሚገኘው ወደ ሚክያስ+ ቤት ሲደርሱ እዚያ አደሩ።  ወደ ሚክያስ ቤት በቀረቡም ጊዜ የወጣቱን ሌዋዊ ድምፅ* ለዩት፤ በመሆኑም ወደ እሱ ገብተው “ለመሆኑ እዚህ ማን አመጣህ? ደግሞስ እዚህ ምን ትሠራለህ? እዚህ እንድትቆይ ያደረገህስ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።  እሱም መልሶ “ሚክያስ ይህን ይህን አደረገልኝ፤ ካህን ሆኜ እንዳገለግለውም ቀጠረኝ”+ አላቸው።  ከዚያም እነሱ “መንገዳችን የተቃና መሆን አለመሆኑን እባክህ አምላክን ጠይቅልን” አሉት።  ካህኑም “በሰላም ሂዱ። በመንገዳችሁ ሁሉ ይሖዋ ከእናንተ ጋር ነው” አላቸው።  ስለሆነም አምስቱ ሰዎች ጉዟቸውን በመቀጠል ወደ ላይሽ+ መጡ። የከተማዋም ሰዎች ልክ እንደ ሲዶናውያን ራሳቸውን ችለው እንደሚኖሩ ተመለከቱ። እነዚህ ሰዎች ያለምንም ስጋት ተረጋግተው የተቀመጡ+ ከመሆናቸውም ሌላ በምድሪቱ ላይ እነሱን የሚያውክ ጨቋኝ ቅኝ ገዢ አልነበረም። በተጨማሪም የሚኖሩት ከሲዶናውያን ርቀው ነበር፤ ከማንም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራቸውም።  እነሱም በጾራና በኤሽታዖል+ ወደሚገኙት ወንድሞቻቸው በተመለሱ ጊዜ ወንድሞቻቸው “የሄዳችሁበት ጉዳይ እንዴት ሆነ?” በማለት ጠየቋቸው።  እነሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ምድሪቱ በጣም ጥሩ ምድር መሆኗን ስላየን ተነሱ፣ እንዝመትባቸው። ለምን ታመነታላችሁ? ገብታችሁ ምድሪቱን ለመውረስ አትዘግዩ። 10  እዚያ ስትደርሱ ያለምንም ስጋት የተቀመጠ+ ሕዝብ ታገኛላችሁ፤ ምድሪቱም በጣም ሰፊ ነች። አምላክም በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ነገር የማይታጣበትን ስፍራ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቷችኋል።”+ 11  ከዚያም ከዳናውያን ቤተሰብ የሆኑና ለጦርነት የታጠቁ 600 ሰዎች ከጾራና ከኤሽታዖል+ ተንቀሳቀሱ። 12  እነሱም ወጥተው በይሁዳ በምትገኘው በቂርያትየአሪም+ ሰፈሩ። ከቂርያትየአሪም በስተ ምዕራብ የሚገኘው ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ ማሃነህዳን* + ተብሎ የሚጠራው በዚህ የተነሳ ነው። 13  ከዚያም ተነስተው ወደ ኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ተጓዙ፤ ወደ ሚክያስም+ ቤት መጡ። 14  በኋላም ላይሽን+ ለመሰለል ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወንድሞቻቸውን “እነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድ፣ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾች፣* የተቀረጸ ምስልና ከብረት የተሠራ ሐውልት* እንዳለ ታውቃላችሁ?+ እንግዲህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ አስቡ” አሏቸው። 15  እነሱም በሚክያስ ቤት ወደሚገኘው ወደ ወጣቱ ሌዋዊ+ ቤት ጎራ ብለው ስለ ደህንነቱ ጠየቁት። 16  በዚህ ጊዜ ሁሉ ለጦርነት የታጠቁት 600ዎቹ የዳን ሰዎች+ መግቢያው በር ላይ ቆመው ነበር። 17  ምድሪቱን ለመሰለል+ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም የተቀረጸውን ምስል፣ ኤፉዱን፣+ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹንና* + ከብረት የተሠራውን ምስል* + ለመውሰድ ወደ ውስጥ ገቡ። (ካህኑም+ ለጦርነት ከታጠቁት 600 ሰዎች ጋር መግቢያው በር ላይ ቆሞ ነበር።) 18  እነሱም ወደ ሚክያስ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል፣ ኤፉዱን፣ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹንና* ከብረት የተሠራውን ምስል* ወሰዱ። ካህኑም “ምን እያደረጋችሁ ነው?” አላቸው። 19  እነሱ ግን እንዲህ አሉት፦ “ዝም በል። ምንም ቃል አትናገር፤ ይልቅስ ከእኛ ጋር ሄደህ አባትና* ካህን ሁነን። ለአንድ ሰው ቤት ካህን ብትሆን ይሻልሃል+ ወይስ በእስራኤል ለሚገኝ አንድ ነገድና+ ቤተሰብ ካህን ብትሆን?” 20  በዚህ ጊዜ የካህኑ ልብ ደስ ተሰኘ፤ እሱም ኤፉዱን፣ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹንና* የተቀረጸውን ምስል+ ይዞ ከሕዝቡ ጋር ሄደ። 21  ከዚያም ልጆቹን፣ ከብቶቹንና ውድ የሆኑትን ነገሮች ከፊት አስቀድመው ጉዟቸውን ለመቀጠል ተነሱ። 22  ከሚክያስ ቤት የተወሰነ መንገድ ርቀው ከሄዱም በኋላ በሚክያስ ቤት አቅራቢያ በሚገኙ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አንድ ላይ ተሰበሰቡ፤ ዳናውያንንም ተከታትለው ደረሱባቸው። 23  ከዚያም ጮኸው ሲጠሯቸው ዳናውያኑ ዞር በማለት ሚክያስን “ምን ሆነሃል? ተሰባስባችሁ የመጣችሁትስ ለምንድን ነው?” አሉት። 24  እሱም “የሠራኋቸውን አማልክቴን ወሰዳችሁ፤ ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችሁ። እንግዲህ ምን ቀረኝ? ታዲያ እንዴት ‘ምን ሆነሃል?’ ትሉኛላችሁ?” አላቸው። 25  በዚህ ጊዜ ዳናውያኑ “አትጩኽብን፤ አለዚያ የተቆጡ ሰዎች* ጉዳት ያደርሱባችኋል፤ ይህም የገዛ ሕይወትህንና* የቤተሰብህን ሕይወት* ሊያሳጣህ ይችላል” አሉት። 26  ዳናውያኑም ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ ሚክያስም እነሱ ከእሱ ይልቅ ብርቱዎች እንደሆኑ ስለተረዳ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ። 27  እነሱም ሚክያስ የሠራቸውን ነገሮችና የእሱን ካህን ከወሰዱ በኋላ ወደ ላይሽ+ ይኸውም ያለምንም ስጋት ተረጋግተው ይኖሩ ወደነበሩት+ ሰዎች ሄዱ። እነሱንም በሰይፍ መቷቸው፤ ከተማዋንም በእሳት አቃጠሉ። 28  ከተማዋ የምትገኘው ከሲዶና ርቃ ስለነበርና ነዋሪዎቿም ከማንኛውም ሕዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ስላልነበራቸው ማንም የሚያድናት አልነበረም፤ ላይሽ የምትገኘው በቤትሬሆብ+ ባለው ሸለቋማ ሜዳ* ላይ ነበር። እነሱም ከተማዋን ዳግመኛ ገንብተው በዚያ መኖር ጀመሩ። 29  በተጨማሪም ከተማዋን ለእስራኤል በተወለደለት+ በአባታቸው በዳን ስም ዳን+ ብለው ጠሯት። የከተማዋ የቀድሞ ስም ግን ላይሽ ነበር።+ 30  ከዚያም ዳናውያን የተቀረጸውን ምስል+ ለራሳቸው አቆሙት፤ የሙሴ ልጅ የሆነው የጌርሳም+ ልጅ ዮናታንና+ ወንዶች ልጆቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች በግዞት እስከተወሰዱበት ጊዜ ድረስ የዳናውያን ነገድ ካህናት ሆኑ። 31  ሚክያስ የሠራውንም የተቀረጸ ምስል አቆሙት፤ ምስሉም የእውነተኛው አምላክ ቤት በሴሎ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በዚያ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “አነጋገር።”
“የዳን ሰፈር” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክት፤ ጣዖታት።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራውን ሐውልት።”
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክቱንና፤ ጣዖታቱንና።”
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክቱንና፤ ጣዖታቱንና።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራውን ሐውልት።”
ወይም “አማካሪና።”
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክቱንና፤ ጣዖታቱንና።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስህንና።”
ወይም “በነፍሳቸው የተመረሩ ሰዎች።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”