መሳፍንት 19:1-30

  • ቢንያማውያን በጊብዓ የፈጸሙት የፆታ ጥቃት (1-30)

19  በእስራኤል ንጉሥ ባልነበረበት+ በዚያ ዘመን በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ ራቅ ብሎ በሚገኝ ስፍራ የሚኖር አንድ ሌዋዊ በይሁዳ ካለችው ከቤተልሔም+ አንዲት ቁባት አገባ።  ቁባቱ ግን ለእሱ ታማኝ አልነበረችም፤ ከዚያም ትታው በይሁዳ ባለችው ቤተልሔም ወደሚገኘው ወደ አባቷ ቤት ሄደች። እሷም በዚያ ለአራት ወር ተቀመጠች።  ባሏም እንድትመለስ ሊያግባባት ተነስቶ ወደ እሷ ሄደ፤ ወደዚያም የሄደው አገልጋዩንና ሁለት አህዮቹን ይዞ ነበር። እሷም ወደ አባቷ ቤት አስገባችው። አባቷም ባየው ጊዜ እሱን በማግኘቱ ተደሰተ።  ስለሆነም አማቱ ማለትም የወጣቷ አባት ሰውየውን ለሦስት ቀን እሱ ጋ እንዲቆይ አግባባው፤ እነሱም በሉ፣ ጠጡም፤ እሱም እዚያው አደረ።  በአራተኛው ቀን በማለዳ ለመሄድ ሲነሱ የወጣቷ አባት አማቹን “ብርታት እንድታገኙ* ትንሽ እህል ቅመሱ፤ ከዚያ በኋላ ትሄዳላችሁ” አለው።  በመሆኑም ተቀመጡ፤ እነሱም አብረው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም የወጣቷ አባት ሰውየውን “እባክህ እዚሁ እደር፤ ልብህም ደስ ይበለው” አለው።  ሰውየውም ለመሄድ ሲነሳ አማቱ ይለምነው ነበር፤ ስለዚህ ዳግመኛ እዚያው አደረ።  በአምስተኛውም ቀን ለመሄድ በማለዳ ሲነሳ የወጣቷ አባት “ብርታት እንድታገኝ* እባክህ ትንሽ እህል ቅመስ” አለው። እነሱም ቀኑ እስኪገባደድ ድረስ እዚያው ዋሉ፤ አብረውም ሲበሉ ቆዩ።  ሰውየውም ከቁባቱና ከአገልጋዩ ጋር ለመሄድ ሲነሳ አማቱ ማለትም የወጣቷ አባት እንዲህ አለው፦ “አሁን እኮ እየመሸ ነው! እባካችሁ እዚሁ እደሩ። ቀኑ እየተገባደደ ነው። እዚሁ እደሩና ልባችሁ ደስ ይበለው። ነገ በማለዳ ተነስታችሁ ትጓዛላችሁ፤ ወደ ቤታችሁም* ትሄዳላችሁ።” 10  ሆኖም ሰውየው እዚያ ለማደር አልፈለገም፤ ስለሆነም ተነስቶ እስከ ኢያቡስ ማለትም እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ተጓዘ።+ ከእሱም ጋር ጭነት የተጫኑት ሁለቱ አህዮች፣ ቁባቱና አገልጋዩ ነበሩ። 11  ወደ ኢያቡስም በቀረቡ ጊዜ ቀኑ መሸትሸት ብሎ ነበር። በመሆኑም አገልጋዩ ጌታውን “ወደዚህች የኢያቡሳውያን ከተማ ጎራ ብለን ብናድር አይሻልም?” አለው። 12  ጌታው ግን “እስራኤላውያን ወዳልሆኑ ባዕድ ሰዎች ከተማ መግባት የለብንም። ከዚህ ይልቅ እስከ ጊብዓ+ ድረስ እንሂድ” አለው። 13  ከዚያም አገልጋዩን “ና፣ ከእነዚህ ስፍራዎች ወደ አንዱ ለመድረስ እንሞክር፤ ጊብዓ ወይም ራማ+ እናድራለን” አለው። 14  በመሆኑም ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ የቢንያም ወደሆነችው ወደ ጊብዓ በተቃረቡም ጊዜ ፀሐይዋ መጥለቅ ጀመረች። 15  ስለዚህ በጊብዓ ለማደር ወደዚያ ጎራ አሉ። ገብተውም በከተማዋ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም ሊያሳድራቸው ወደ ቤቱ የወሰዳቸው ማንም ሰው አልነበረም።+ 16  በመጨረሻም ምሽት ላይ ከእርሻ ሥራው እየተመለሰ ያለ አንድ አረጋዊ ሰው መጣ። ይህ ሰው የኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ ሰው ነበር፤ በጊብዓም መኖር ከጀመረ የተወሰነ ጊዜ ሆኖታል፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ቢንያማውያን+ ነበሩ። 17  አረጋዊውም ቀና ብሎ መንገደኛውን ሰው በከተማዋ አደባባይ ሲያየው “ወዴት ነው የምትሄደው? የመጣኸውስ ከየት ነው?” አለው። 18  እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እኛ በይሁዳ ከምትገኘው ቤተልሔም ተነስተን በኤፍሬም ተራራማ አካባቢዎች ራቅ ብሎ ወደሚገኝ ስፍራ እየተጓዝን ነው፤ እኔ የዚያ አካባቢ ሰው ነኝ። በይሁዳ ወደምትገኘው ቤተልሔም+ ሄጄ ነበር፤ አሁን ወደ ይሖዋ ቤት እየሄድኩ ነው፤* ይሁንና ወደ ቤቱ የሚያስገባኝ ሰው አላገኘሁም። 19  ለአህዮቻችን የሚሆን በቂ ገለባና ገፈራ አለን፤+ በተጨማሪም ለእኔም ሆነ ለሴትየዋ እንዲሁም ለአገልጋያችን የሚሆን ምግብና+ የወይን ጠጅ አለን። ምንም የጎደለ ነገር የለም።” 20  ሆኖም አረጋዊው ሰው “ሰላም ለአንተ ይሁን! የሚያስፈልጋችሁን ማንኛውንም ነገር እኔ አሟላላችኋለሁ። ብቻ እዚህ አደባባይ ላይ አትደሩ” አለው። 21  ስለዚህ ወደ ቤቱ ይዞት ገባ፤ ለአህዮቹም ገፈራ ሰጣቸው። ሰዎቹም እግራቸውን ታጠቡ፤ በሉ፣ ጠጡም። 22  እነሱም እየተደሰቱ ሳለ በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የተወሰኑ ጋጠወጥ ወንዶች ቤቱን ከበው እርስ በርስ እየተገፈታተሩ በሩን ይደበድቡ ጀመር፤ የቤቱ ባለቤት የሆነውንም አረጋዊ “ከእሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም ቤትህ የገባውን ሰው ወደ ውጭ አውጣልን” ይሉት ነበር።+ 23  በዚህ ጊዜ የቤቱ ባለቤት ወደ እነሱ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞቼ ተዉ፤ ይህን መጥፎ ድርጊት አትፈጽሙ። እባካችሁ ይህ ሰው የእኔ እንግዳ ነው። እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ። 24  ይኸው ድንግል የሆነች ልጄና የሰውየው ቁባት አሉ። እንግዲህ አሻፈረኝ ካላችሁ እነሱን ላውጣላችሁና ልታዋርዷቸው ትችላላችሁ።* + በዚህ ሰው ላይ ግን እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ።” 25  ሰዎቹ ግን ሊሰሙት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ በመሆኑም ሰውየው ቁባቱን+ ይዞ ወደ ውጭ አወጣላቸው። እነሱም ደፈሯት፤ እስኪነጋም ድረስ ሌሊቱን ሙሉ ሲጫወቱባት አደሩ። ከዚያም ጎህ ሲቀድ ለቀቋት። 26  ሴትየዋም በማለዳ መጥታ ጌታዋ ባለበት የሰውየው ቤት በር ላይ ተዘረረች፤ ብርሃን እስኪሆንም ድረስ እዚያው ወድቃ ቀረች። 27  በኋላም ጌታዋ ጉዞውን ለመቀጠል በጠዋት ተነስቶ የቤቱን በሮች ሲከፍት ሴትየዋ ማለትም ቁባቱ እጇ ደፉ ላይ ተዘርግቶ የቤቱ በር ላይ ወድቃ ተመለከተ። 28  እሱም “ተነሽ፤ እንሂድ” አላት። ነገር ግን ምንም መልስ አልነበረም። ከዚያም ሰውየው እሷን በአህያው ላይ አድርጎ ወደ ቤቱ ሄደ። 29  ቤቱም እንደደረሰ ቢላ አንስቶ ቁባቱን በአጥንቶቿ መገጣጠሚያ ላይ 12 ቦታ ቆራረጣት፤ ከዚያም ወደ እያንዳንዱ የእስራኤል ክልል አንድ ቁራጭ ላከ። 30  ይህን ያየ ሰው ሁሉ እንዲህ ይል ነበር፦ “እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ ታይቶም፣ ተሰምቶም አያውቅም። ይህን ጉዳይ በቁም ነገር አስቡበት፤* ተመካከሩበት፤+ ከዚያም ምን መደረግ እንዳለበት ንገሩን።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ልባችሁን ለመደገፍ።”
ወይም “ልብህን ለመደገፍ።”
ቃል በቃል “ድንኳናችሁ።”
“አሁን በይሖዋ ቤት አገለግላለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አስነውሯቸው፤ መልካም መስሎ የታያችሁንም አድርጉባቸው።”
ወይም “ልብ በሉት።”