መሳፍንት 6:1-40

  • ምድያማውያን እስራኤላውያንን ጨቆኗቸው (1-10)

  • አንድ መልአክ መስፍኑን ጌድዮንን እንደሚረዳው ቃል ገባለት (11-24)

  • ጌድዮን የባአልን መሠዊያ አፈራረሰ (25-32)

  • የአምላክ መንፈስ በጌድዮን ላይ ወረደ (33-35)

  • ጌድዮን በተባዘተው የበግ ፀጉር ያደረገው ሙከራ (36-40)

6  እስራኤላውያን ግን እንደገና በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ በመሆኑም ይሖዋ ለሰባት ዓመት ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጣቸው።+  የምድያማውያን እጅ በእስራኤል ላይ በረታ።+ እስራኤላውያን በምድያማውያን የተነሳ በተራሮች ላይ፣ በዋሻዎች ውስጥና በቀላሉ በማይደረስባቸው ስፍራዎች ለመደበቂያ የሚሆኑ ቦታዎችን* ለራሳቸው አዘጋጁ።+  እነሱም ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ሁሉ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና+ የምሥራቅ ሰዎች+ ጥቃት ይሰነዝሩባቸው ነበር።  እንዲሁም በዙሪያቸው በመስፈር እስከ ጋዛ ድረስ ያለውን የምድሩን ሰብል ያጠፉ ነበር፤ ለእስራኤላውያን የሚበሉት ምንም ነገር አያስተርፉላቸውም፤ በግም ሆነ ከብት ወይም አህያ አያስቀሩላቸውም ነበር።+  ምክንያቱም ከብቶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው እንደ አንበጣ መንጋ ብዙ ሆነው ይመጡ ነበር፤+ እነሱም ሆኑ ግመሎቻቸው ለቁጥር የሚያታክቱ ነበሩ፤+ ወደዚያም የሚመጡት ምድሪቱን ለማጥፋት ነበር።  በመሆኑም እስራኤላውያን በምድያማውያን የተነሳ ለከፍተኛ ድህነት ተዳረጉ፤ እነሱም ይሖዋ እንዲረዳቸው መጮኽ ጀመሩ።+  እስራኤላውያን በምድያማውያን የተነሳ ለእርዳታ ወደ ይሖዋ በጮኹ ጊዜ+  ይሖዋ ነቢይ ላከላቸው፤ እሱም እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከግብፅ አወጣኋችሁ፤ በዚህ መንገድ ከባርነት ቤት አላቀኳችሁ።+  ከግብፅ እጅና ከሚጨቁኗችሁ ሁሉ ታደግኳችሁ፤ እነሱንም ከፊታችሁ በማባረር ምድራቸውን ሰጠኋችሁ።+ 10  እንዲሁም “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው አሞራውያን የሚያመልኳቸውን አማልክት አትፍሩ” አልኳችሁ።+ እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም።’”+ 11  በኋላም የይሖዋ መልአክ መጥቶ+ በኦፍራ በሚገኘው በአቢዔዜራዊው+ በዮአስ ትልቅ ዛፍ ሥር ተቀመጠ። የዮአስም ልጅ ጌድዮን+ ከምድያማውያን ተደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴ እየወቃ ነበር። 12  ከዚያም የይሖዋ መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኃያል ተዋጊ፣ ይሖዋ ከአንተ ጋር ነው”+ አለው። 13  ጌድዮንም እንዲህ አለው፦ “ይቅርታ ጌታዬ፤ ታዲያ ይሖዋ ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ የሚደርስብን ለምንድን ነው?+ አባቶቻችን ‘ይሖዋ ከግብፅ ምድር አላወጣንም?’+ እያሉ ይነግሩን የነበረው ድንቅ ሥራው ሁሉ የት አለ?+ አሁን ይሖዋ ትቶናል፤+ ለምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል።” 14  ይሖዋም ፊት ለፊቱ ቆመና እንዲህ አለው፦ “በል ባለህ ኃይል ሂድ፤ እስራኤልንም ከምድያማውያን እጅ ታድናለህ።+ የምልክህ እኔ አይደለሁም?” 15  ጌድዮንም መልሶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እኔ እንዴት እስራኤልን ላድን እችላለሁ? የእኔ ጎሳ* እንደሆነ ከምናሴ ነገድ የመጨረሻው ነው፤ እኔም ብሆን በአባቴ ቤት ውስጥ እዚህ ግባ የምባል አይደለሁም።” 16  ሆኖም ይሖዋ “እኔ ከአንተ ጋር ስለምሆን+ ምድያማውያንን ልክ እንደ አንድ ሰው ትመታቸዋለህ” አለው። 17  ከዚያም ጌድዮን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ ከእኔ ጋር እየተነጋገርክ ያለኸው አንተ ስለመሆንህ አንድ ምልክት አሳየኝ። 18  ደግሞም ተመልሼ መጥቼ ስጦታዬን በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ ከዚህ አትሂድ”+ አለው። እሱም “እስክትመለስ ድረስ እዚሁ እጠብቅሃለሁ” አለው። 19  ጌድዮንም ገብቶ አንድ የፍየል ጠቦትና ከአንድ ኢፍ* ዱቄት ቂጣ* አዘጋጀ።+ ሥጋውን በቅርጫት፣ መረቁን ደግሞ በድስት አድርጎ ወደ እሱ ይዞ በመምጣት በትልቁ ዛፍ ሥር አቀረበለት። 20  የእውነተኛው አምላክ መልአክም “ሥጋውንና ቂጣውን ወስደህ እዚያ ባለው ዓለት ላይ አስቀምጣቸው፤ መረቁንም አፍስሰው” አለው። እሱም እንዲሁ አደረገ። 21  ከዚያም የይሖዋ መልአክ በእጁ ይዞት የነበረውን በትር ዘርግቶ በጫፉ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ በዚህ ጊዜ እሳት ከዓለቱ ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ።+ ከዚያም የይሖዋ መልአክ ከእይታው ተሰወረ። 22  በዚህ ጊዜ ጌድዮን የይሖዋ መልአክ እንደነበር አስተዋለ።+ ወዲያውኑም “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ የይሖዋን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ!” አለ።+ 23  ሆኖም ይሖዋ “ሰላም ለአንተ ይሁን። አትፍራ፤+ አትሞትም” አለው። 24  ጌድዮንም በዚያ ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያውም እስከ ዛሬ ድረስ ‘ይሖዋ ሻሎም’* + ተብሎ ይጠራል። አሁንም ድረስ የአቢዔዜራውያን በሆነችው በኦፍራ ይገኛል። 25  በዚያ ምሽት ይሖዋ ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ “የአባትህ ንብረት የሆነውን ሰባት ዓመት የሞላውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ የአባትህ የሆነውን የባአልን መሠዊያም አፈራርስ፤ አጠገቡም የሚገኘውን የማምለኪያ ግንድ* ሰባብር።+ 26  በዚህ ምሽግ አናት ላይ ድንጋይ ደርድረህ ለአምላክህ ለይሖዋ መሠዊያ ከሠራህ በኋላ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ በምትሰባብረው የማምለኪያ ግንድ* እንጨት ላይ የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው።” 27  ስለዚህ ጌድዮን ከአገልጋዮቹ መካከል አሥር ሰዎችን ወስዶ ልክ ይሖዋ እንዳለው አደረገ። ይሁንና የአባቱን ቤትና የከተማዋን ሰዎች በጣም ስለፈራ ይህን ያደረገው በቀን ሳይሆን በሌሊት ነበር። 28  የከተማዋ ሰዎች በማግስቱ በማለዳ ሲነሱ የባአል መሠዊያ ፈራርሶ፣ አጠገቡ የነበረው የማምለኪያ ግንድም* ተሰባብሮ እንዲሁም ሁለተኛው ወይፈን በተሠራው መሠዊያ ላይ ተሠውቶ ተመለከቱ። 29  እነሱም እርስ በርሳቸው “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ተባባሉ። ሁኔታውንም ካጣሩ በኋላ “ይህን ያደረገው የዮአስ ልጅ ጌድዮን ነው” አሉ። 30  በመሆኑም የከተማዋ ሰዎች ዮአስን “ልጅህ የባአልን መሠዊያ ስላፈራረሰና አጠገቡ የነበረውን የማምለኪያ ግንድ* ስለሰባበረ ወደዚህ አውጣው፤ መሞት አለበት” አሉት። 31  ከዚያም ዮአስ+ እሱን የሚቃወሙትን ሰዎች ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “ለባአል መሟገት ይኖርባችኋል? እሱን ለማዳን መሞከርስ ይገባችኋል? ለእሱ የሚሟገት ማንኛውም ሰው በዚህ ጠዋት መሞት ይገባዋል።+ እሱ አምላክ ከሆነ አንድ ሰው መሠዊያውን ስላፈረሰበት ለራሱ ይሟገት።”+ 32  እሱም “ባአል አንድ ሰው መሠዊያውን ስላፈረሰበት ለራሱ ይሟገት” በማለት ጌድዮንን በዚያ ቀን የሩባአል* ብሎ ጠራው። 33  ምድያማውያን፣+ አማሌቃውያንና+ የምሥራቅ ሰዎች በሙሉ ግንባር ፈጥረው+ ወደ ኢይዝራኤል ሸለቆ* በመሻገር በዚያ ሰፈሩ። 34  የይሖዋም መንፈስ በጌድዮን ላይ ወረደ፤* + እሱም ቀንደ መለከት ነፋ፤+ አቢዔዜራውያንም+ እሱን በመደገፍ ተከትለውት ወጡ። 35  ከዚያም በመላው ምናሴ መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም እሱን በመደገፍ ተከትለውት ወጡ። በተጨማሪም ወደ አሴር፣ ወደ ዛብሎንና ወደ ንፍታሌም መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም ከእሱ ጋር ለመገናኘት ወጡ። 36  ከዚያም ጌድዮን እውነተኛውን አምላክ እንዲህ አለው፦ “ቃል በገባኸው መሠረት በእኔ አማካኝነት እስራኤልን የምታድን ከሆነ+ 37  ይኸው አውድማው ላይ የተባዘተ የበግ ፀጉር አስቀምጣለሁ። በዙሪያው ያለው ምድር በሙሉ ደረቅ ሆኖ የበግ ፀጉሩ ላይ ብቻ ጤዛ ከተገኘ ቃል በገባኸው መሠረት በእኔ አማካኝነት እስራኤልን እንደምታድን አውቃለሁ።” 38  ልክ እንደዚሁም ሆነ። በማግስቱ በማለዳ ተነስቶ የበግ ፀጉሩን ሲጨምቀው ከበግ ፀጉሩ ላይ የወጣው ውኃ በትልቅ ጎድጓዳ ሳህን ሙሉ ሆነ። 39  ሆኖም ጌድዮን እውነተኛውን አምላክ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ቁጣህ በእኔ ላይ አይንደድ፤ አንድ ጊዜ ብቻ እንድናገር ፍቀድልኝ። ከበግ ፀጉሩ ጋር በተያያዘ አንድ ሌላ ሙከራ ብቻ ላድርግ። እባክህ የበግ ፀጉሩ ብቻ ደረቅ ሆኖ ምድሩ በሙሉ ጤዛ እንዲሆን አድርግ።” 40  በመሆኑም አምላክ በዚያ ሌሊት እንደዚሁ አደረገ፤ የበግ ፀጉሩ ብቻ ደረቅ ሆኖ ምድሩ በሙሉ ጤዛ ሆነ።

የግርጌ ማስታወሻ

“የምድር ውስጥ ዕቃ ማከማቻዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ሺህ።”
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
“ይሖዋ ሰላም ነው” የሚል ትርጉም አለው።
“ባአል በሕግ ይሟገት (ይከራከር)” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ቃል በቃል “ጌድዮንን አለበሰው።”