መሳፍንት 9:1-57
9 ከጊዜ በኋላ የየሩባአል ልጅ አቢሜሌክ+ በሴኬም ወደሚገኙት የእናቱ ወንድሞች ሄዶ እነሱንና የአያቱን ቤተሰብ* በሙሉ እንዲህ አላቸው፦
2 “እባካችሁ የሴኬምን መሪዎች* ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፦ ‘70ዎቹ የየሩባአል ልጆች+ በሙሉ ቢገዟችሁ ይሻላችኋል ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ? ደግሞም እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ፣ የሥጋችሁ ቁራጭ* መሆኔን አስታውሱ።’”
3 በመሆኑም የእናቱ ወንድሞች እሱን ወክለው ለሴኬም መሪዎች በሙሉ ይህንኑ ነገሯቸው፤ እነሱም “እሱ እኮ የገዛ ወንድማችን ነው” በማለት ልባቸው አቢሜሌክን ወደመከተል አዘነበለ።
4 እነሱም ከባአልበሪት+ ቤት* 70 የብር ሰቅል ሰጡት፤ አቢሜሌክም ተከታዮቹ እንዲሆኑ በዚህ ገንዘብ ሥራ ፈቶችንና ወሮበሎችን ቀጠረበት።
5 ከዚያም በኦፍራ+ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄዶ ወንድሞቹን ማለትም 70ዎቹን የየሩባአል ልጆች በአንድ ድንጋይ ላይ ገደላቸው።+ በሕይወት የተረፈው የሁሉም ታናሽ የሆነው የየሩባአል ልጅ ኢዮዓታም ብቻ ነበር፤ ምክንያቱም እሱ ተደብቆ ነበር።
6 ከዚያም የሴኬም መሪዎች ሁሉ እንዲሁም የቤትሚሎ ሰዎች በሙሉ በአንድነት ተሰብስበው በመሄድ አቢሜሌክን በትልቁ ዛፍ አጠገብ ይኸውም በሴኬም በነበረው ዓምድ አጠገብ አነገሡት።+
7 ኢዮዓታምም ይህን በነገሩት ጊዜ ወዲያውኑ ሄዶ በገሪዛን ተራራ+ አናት ላይ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሴኬም መሪዎች እኔን ስሙኝ፤ ከዚያም አምላክ ይሰማችኋል።
8 “ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች በላያቸው የሚነግሥ ንጉሥ ለመቀባት ሄዱ። በመሆኑም የወይራ ዛፍን ‘በእኛ ላይ ንገሥ’+ አሉት።
9 ሆኖም የወይራ ዛፍ ‘ሄጄ ከሌሎች ዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል አምላክንና ሰዎችን ለማክበር የሚጠቀሙበትን ዘይቴን* መስጠት ልተው?’ አላቸው።
10 ከዚያም ዛፎቹ የበለስን ዛፍ ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት።
11 የበለስ ዛፍ ግን ‘ሄጄ ከሌሎች ዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል ጣፋጭና መልካም ፍሬዬን መስጠት ልተው?’ አላቸው።
12 በመቀጠልም ዛፎቹ የወይን ተክልን ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት።
13 የወይን ተክልም መልሶ ‘ሄጄ ከሌሎች ዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል አምላክንና ሰዎችን የሚያስደስተውን አዲስ የወይን ጠጅ መስጠቴን ልተው?’ አላቸው።
14 በመጨረሻም ሌሎቹ ዛፎች ሁሉ የእሾህ ቁጥቋጦን ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’+ አሉት።
15 በዚህ ጊዜ የእሾህ ቁጥቋጦው ዛፎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘በእናንተ ላይ ንጉሥ እንድሆን የምትቀቡኝ እውነት ከልባችሁ ከሆነ መጥታችሁ በጥላዬ ሥር ተጠለሉ። ካልሆነ ግን እሳት ከእሾህ ቁጥቋጦው ወጥቶ አርዘ ሊባኖሶችን ያቃጥል።’
16 “ለመሆኑ አቢሜሌክን ንጉሥ ያደረጋችሁት+ በየዋህነትና በቅንነት ነው? ለየሩባአልና ለቤተሰቡ ጥሩነት አሳይታችኋል? የሚገባውን ውለታስ መልሳችሁለታል?
17 አባቴ ለእናንተ ሲል በተዋጋ ጊዜ+ እናንተን ከምድያማውያን እጅ ለመታደግ ሕይወቱን* አደጋ ላይ ጥሏል።+
18 እናንተ ግን ዛሬ በአባቴ ቤተሰብ ላይ ተነሳችሁ፤ 70 ልጆቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ ገደላችኋቸው።+ ወንድማችሁ ስለሆነ ብቻ ከባሪያይቱ የወለደውን ልጁን አቢሜሌክን+ በሴኬም መሪዎች ላይ አነገሣችሁት።
19 በዛሬው ዕለት ለየሩባአልና ለቤተሰቡ ይህን ያደረጋችሁት በየዋህነትና በቅንነት ከሆነ በአቢሜሌክ ደስ ይበላችሁ፤ እሱም በእናንተ ደስ ይበለው።
20 ይህ ካልሆነ ግን እሳት ከአቢሜሌክ ወጥቶ የሴኬምን መሪዎችና ቤትሚሎን+ ያቃጥል፤ እንዲሁም እሳት ከሴኬም መሪዎችና ከቤትሚሎ ወጥቶ አቢሜሌክን ያቃጥል።”+
21 ከዚያም ኢዮዓታም+ ወደ በኤር ሸሽቶ አመለጠ፤ በወንድሙ በአቢሜሌክ የተነሳም በዚያ ኖረ።
22 አቢሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ገዛ።*
23 ከዚያም አምላክ በአቢሜሌክና በሴኬም መሪዎች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር አደረገ፤* እነሱም በአቢሜሌክ ላይ ተንኮል አሴሩበት።
24 ይህም የሆነው ወንድሞቹን የገደለውን አቢሜሌክንና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬምን መሪዎች በሞቱት ሰዎች ደም ተጠያቂ በማድረግ+ በ70ዎቹ የየሩባአል ልጆች ላይ የተፈጸመውን ግፍ ለመበቀል ነው።
25 በመሆኑም የሴኬም መሪዎች አድብተው እሱን የሚጠባበቁ ሰዎችን በተራሮች አናት ላይ መደቡ፤ እነሱም በአጠገባቸው የሚያልፈውን መንገደኛ ሁሉ ይዘርፉ ነበር። በኋላም ሁኔታው ለአቢሜሌክ ተነገረው።
26 ከዚያም የኤቤድ ልጅ ገአል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም ተሻገረ፤+ የሴኬምም መሪዎች እምነት ጣሉበት።
27 እነሱም ወደ እርሻ ወጥተው የወይን ፍሬያቸውን ከሰበሰቡ በኋላ ጨመቁት፤ በዓልም አከበሩ፤ ከዚያም ወደ አምላካቸው+ ቤት ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ አቢሜሌክንም ረገሙ።
28 ከዚያም የኤቤድ ልጅ ገአል እንዲህ አለ፦ “ለመሆኑ አቢሜሌክ ማን ነው? እናገለግለውስ ዘንድ ሴኬም ማን ነው? እሱ የየሩባአል+ ልጅ አይደለም? የእሱ ተወካይስ ዘቡል አይደለም? የሴኬምን አባት የኤሞርን ሰዎች አገልግሉ! አቢሜሌክን የምናገለግለው ለምንድን ነው?
29 ይህን ሕዝብ የማዘው እኔ ብሆን ኖሮ አቢሜሌክን አስወግደው ነበር።” ከዚያም አቢሜሌክን “ብዙ ሠራዊት አሰባስበህ ና ውጣ” አለው።
30 የከተማዋ ገዢ የሆነው ዘቡል የኤቤድ ልጅ ገአል የተናገረውን ነገር በሰማ ጊዜ ቁጣው ነደደ።
31 በመሆኑም ለአቢሜሌክ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት በሚስጥር መልእክተኞችን ላከ፦* “እነሆ፣ የኤቤድ ልጅ ገአልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተዋል፤ ከተማዋም በአንተ ላይ እንድታምፅ እያነሳሱ ነው።
32 በመሆኑም አንተም ሆንክ አብረውህ ያሉት ሰዎች በሌሊት ወጥታችሁ ሜዳው ላይ አድፍጡ።
33 ጠዋት ላይ ልክ ፀሐይ ስትወጣ፣ ማልደህ በመነሳት በከተማዋ ላይ ጥቃት ሰንዝር፤ እሱና አብረውት ያሉት ሰዎች አንተን ለመውጋት ሲወጡም እሱን ድል ለመምታት የቻልከውን ሁሉ አድርግ።”*
34 በመሆኑም አቢሜሌክና አብረውት ያሉት ሰዎች በሙሉ በሌሊት ተነሱ፤ በአራት ቡድንም ሆነው በሴኬም ላይ አደፈጡ።
35 የኤቤድ ልጅ ገአል ወጥቶ በከተማዋ መግቢያ በር ላይ በቆመ ጊዜ አቢሜሌክና አብረውት ያሉት ሰዎች ካደፈጡበት ቦታ ተነሱ።
36 ገአልም ሰዎቹን ባያቸው ጊዜ ዘቡልን “ተመልከት፣ ከተራሮቹ አናት ላይ ሰዎች እየወረዱ ነው” አለው። ዘቡል ግን “ሰው መስሎ የታየህ የተራሮቹ ጥላ ነው” አለው።
37 በኋላም ገአል “ተመልከት፤ ከምድሩ መሃል ሰዎች እየወረዱ ነው፤ አንደኛው ቡድን በመኦነኒም ትልቅ ዛፍ በኩል አድርጎ እየመጣ ነው” አለ።
38 ዘቡልም “‘እናገለግለው ዘንድ አቢሜሌክ ማን ነው?’+ እያልክ ጉራህን ስትነዛ አልነበረም? የናቅከው ሕዝብ ይህ አይደለም? እስቲ አሁን ውጣና ግጠማቸው” ሲል መለሰለት።
39 በመሆኑም ገአል ከሴኬም መሪዎች ፊት ፊት በመሄድ ከአቢሜሌክ ጋር ተዋጋ።
40 አቢሜሌክም አሳደደው፤ ገአልም ከፊቱ ሸሸ፤ እስከ ከተማዋም መግቢያ በር ድረስ ብዙ ሰው ተረፈረፈ።
41 አቢሜሌክም በአሩማ መኖሩን ቀጠለ፤ ዘቡልም+ ገአልንና ወንድሞቹን ከሴኬም አስወጣቸው።
42 በማግስቱም ሕዝቡ ከከተማዋ ወጣ፤ ይህም ለአቢሜሌክ ተነገረው።
43 እሱም ሰዎቹን ወስዶ በሦስት ቡድን በመክፈል ሜዳ ላይ አድፍጦ ይጠባበቅ ጀመር። ሕዝቡም ከከተማዋ መውጣቱን ተመለከተ፤ በዚህ ጊዜም በእነሱ ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ መታቸውም።
44 አቢሜሌክና አብረውት የነበሩት ቡድኖች በፍጥነት ወደ ፊት በመገስገስ በከተማዋ መግቢያ በር ላይ ቆሙ፤ ሁለቱ ቡድኖች ደግሞ ከከተማዋ ውጭ ባሉት ሰዎች ሁሉ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ መቷቸውም።
45 አቢሜሌክም ያን ቀን ሙሉ ከተማዋን ሲወጋ ዋለ፤ በመጨረሻም በቁጥጥሩ ሥር አዋላት። በከተማዋም ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ገደለ፤ ከዚያም ከተማዋን አፈራረሳት፤+ በላይዋም ጨው ዘራባት።
46 የሴኬም ግንብ መሪዎች በሙሉ ይህን ሲሰሙ ወዲያውኑ በኤልበሪት+ ቤት* ወደሚገኘው መሸሸጊያ ቦታ* ሄዱ።
47 የሴኬም ግንብ መሪዎች በሙሉ አንድ ላይ እንደተሰባሰቡ ለአቢሜሌክ በተነገረውም ጊዜ
48 አቢሜሌክና አብረውት የነበሩት ሰዎች በሙሉ ወደ ጻልሞን ተራራ ወጡ። አቢሜሌክም መጥረቢያ ይዞ የዛፍ ቅርንጫፍ ከቆረጠ በኋላ አንስቶ በትከሻው ተሸከመው፤ አብረውት የነበሩትንም ሰዎች “እኔ ሳደርግ ያያችሁትን ፈጥናችሁ አድርጉ!” አላቸው።
49 በመሆኑም ሰዎቹ ሁሉ ቅርንጫፎች ቆርጠው በመያዝ አቢሜሌክን ተከተሉት። ከዚያም ቅርንጫፎቹን መሸሸጊያ ቦታው ላይ በመቆለል መሸሸጊያ ቦታውን በእሳት አያያዙት። በዚህም የተነሳ የሴኬም ግንብ ሰዎች በሙሉ ይኸውም 1,000 ገደማ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች ሞቱ።
50 ከዚያም አቢሜሌክ ወደ ቴቤጽ ሄደ፤ ቴቤጽንም ከቦ በቁጥጥር ሥር አዋላት።
51 በከተማዋ መሃል ጠንካራ ግንብ ስለነበር ወንዶችና ሴቶች በሙሉ እንዲሁም የከተማዋ መሪዎች በሙሉ ወደዚያ ሸሹ። እነሱም ከውስጥ ሆነው በሩን ከዘጉት በኋላ የግንቡ አናት ላይ ወጡ።
52 አቢሜሌክም ወደ ግንቡ ሄደ፤ ጥቃትም ሰነዘረበት። ግንቡንም በእሳት ለማቃጠል ወደ መግቢያው ተጠጋ።
53 ከዚያም አንዲት ሴት በአቢሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ በመልቀቅ ጭንቅላቱን ፈረከሰችው።+
54 እሱም ጋሻ ጃግሬውን ወዲያውኑ ጠርቶ “‘ሴት ገደለችው’ እንዳይሉኝ ሰይፍህን ምዘዝና ግደለኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬውም ወጋው፤ እሱም ሞተ።
55 የእስራኤል ሰዎች አቢሜሌክ መሞቱን ሲያዩ ሁሉም ወደቤታቸው ተመለሱ።
56 በዚህ መንገድ አምላክ፣ አቢሜሌክ 70 ወንድሞቹን በመግደል በአባቱ ላይ ለፈጸመው ክፉ ነገር የእጁን እንዲያገኝ አደረገ።+
57 በተጨማሪም አምላክ የሴኬም ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ እንዲደርስ አደረገ። በመሆኑም የየሩባአል+ ልጅ የኢዮዓታም+ እርግማን ደረሰባቸው።