መኃልየ መኃልይ 5:1-16
5 “እህቴ፣ ሙሽራዬ ሆይ፣ወደ አትክልት ቦታዬ ገብቻለሁ።+
ከርቤዬንና ቅመሜን+ ወስጃለሁ።
የማር እንጀራዬንና ወለላውን በልቻለሁ፤የወይን ጠጄንና ወተቴን ጠጥቻለሁ።”+
“ውድ ጓደኞቼ፣ ብሉ!
ጠጥታችሁም በፍቅር መግለጫዎች ስከሩ!”+
2 “እኔ ተኝቻለሁ፤ ልቤ ግን ነቅቷል።+
ውዴ በሩን ሲያንኳኳ ይሰማኛል!
‘እህቴ ሆይ፣ የእኔ ፍቅር፣እንከን የለሽ ርግቤ ሆይ፣ ክፈቺልኝ!
ራሴ በጤዛ፣ፀጉሬም በሌሊቱ እርጥበት ርሷል።’+
3 ልብሴን አውልቄአለሁ።
መልሼ መልበስ ሊኖርብኝ ነው?
እግሬን ታጥቤአለሁ።
እንደገና ላቆሽሸው ነው?
4 ውዴ እጁን ከበሩ ቀዳዳ መለሰ፤ለእሱ ያለኝ ስሜትም ተነሳሳ።
5 እኔም ለውዴ በሩን ለመክፈት ተነሳሁ፤የመዝጊያው እጀታ ላይእጆቼ ከርቤ፣ጣቶቼም የከርቤ ፈሳሽ አንጠባጠቡ።
6 ለውዴ በሩን ከፈትኩለት፤ውዴ ግን በዚያ አልነበረም፤ ሄዶ ነበር።
በመሄዱም ተስፋ ቆረጥኩ።*
ፈለግኩት፤ ግን አላገኘሁትም።+
ጠራሁት፤ እሱ ግን አልመለሰልኝም።
7 ከተማዋን እየተዘዋወሩ የሚጠብቁት ሰዎች አገኙኝ።
መቱኝ፤ አቆሰሉኝ።
የቅጥሩ ጠባቂዎች ነጠላዬን* ገፈፉኝ።
8 የኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች ሆይ፣
ውዴን ካገኛችሁት በፍቅሩ ተይዤ መታመሜንእንድትነግሩት አምላችኋለሁ።”
9 “አንቺ ከሴቶች ሁሉ እጅግ የተዋብሽ ሆይ፣ውድሽ ሌሎች ከሚያፈቅሯቸው ወንዶች ሁሉ እንዴት ቢበልጥ ነው?
እንዲህ ያለ መሐላ ያስገባሽን፣ለመሆኑ ውድሽ ሌሎች ከሚያፈቅሯቸው ወንዶች ሁሉ እንዴት ቢበልጥ ነው?”
10 “ውዴ በጣም ቆንጆና ቀይ ነው፤በአሥር ሺህ ሰዎች መካከል እንኳ ጎልቶ ይታያል።
11 ራሱ እንደ ወርቅ፣ አዎ እንደጠራ ወርቅ ነው።
ፀጉሩ እንደሚወዛወዝ የዘንባባ ዝንጣፊ* ነው፤እንደ ቁራም ጥቁር ነው።
12 ዓይኖቹ በውኃ ጅረት አጠገብ እንዳሉ፣ጢም ብሎ በሞላ ኩሬ ዳርቻ* ሆነውበወተት እንደሚታጠቡ ርግቦች ናቸው።
13 ጉንጮቹ የቅመማ ቅመም መደብ፣+ጥሩ መዓዛ ያላቸው ዕፀዋት ክምር ይመስላሉ።
ከንፈሮቹ ፈሳሽ ከርቤ የሚያንጠባጥቡ አበቦች ናቸው።+
14 የእጆቹ ጣቶች ወርቅ፣ የጣቶቹም ጫፎች ክርስቲሎቤ ናቸው።
ሆዱ በሰንፔር የተሸፈነ የተወለወለ የዝሆን ጥርስ ነው።
15 እግሮቹ ከምርጥ ወርቅ በተሠሩ መሰኪያዎች ላይ የቆሙ የእብነ በረድ ዓምዶች ናቸው።
መልኩ እንደ ሊባኖስ ያማረ ነው፤ እንደ አርዘ ሊባኖስም አቻ የለውም።+
16 አፉ* እጅግ ጣፋጭ ነው፤ሁለመናውም ደስ ያሰኛል።+
የኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች ሆይ፣ ውዴ ይህ ነው፤ ፍቅሬ እንዲህ ያለ ነው።”