መክብብ 10:1-20

  • ትንሽ ሞኝነት ጥበብን ዋጋ ያሳጣል (1)

  • የችሎታ ማነስ አደጋ ላይ ይጥላል (2-11)

  • ሞኝ ሰው የሚደርስበት አሳዛኝ መከራ (12-15)

  • የገዢዎች ሞኝነት (16-20)

    • ቃልህን ወፍ ደግማ ልትናገር ትችላለች (20)

10  የሞቱ ዝንቦች በጥሩ ቀማሚ የተዘጋጀውን ሽቶ እንዲበላሽና እንዲገማ እንደሚያደርጉት ሁሉ ትንሽ ሞኝነትም ጥበብንና ክብርን ዋጋ ያሳጣል።+   የጥበበኛ ሰው ልብ በትክክለኛ መንገድ ይመራዋል፤* የሞኝ ልብ ግን በተሳሳተ መንገድ ይመራዋል።*+  ሞኝ ሰው በየትኛውም መንገድ ቢመላለስ ማስተዋል* ይጎድለዋል፤+ ሞኝ መሆኑንም ሰው ሁሉ እንዲያውቅ ያደርጋል።+  የገዢ ቁጣ* በአንተ ላይ ቢነድ ስፍራህን አትልቀቅ፤+ የረጋ መንፈስ ታላቅ ኃጢአትን ጸጥ ያደርጋልና።+  ከፀሐይ በታች ያየሁት አንድ የሚያስጨንቅ ነገር አለ፤ ይህም በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እንደሚሠሩት ያለ ስህተት ነው፦+  ሞኞች በከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች ላይ ሲቀመጡ የናጠጡ ሀብታሞች* ግን በዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ።  አገልጋዮች በፈረስ ተቀምጠው ሲጓዙ፣ መኳንንት ግን እንደ አገልጋዮች በእግራቸው ሲሄዱ አይቻለሁ።+  ጉድጓድ የሚቆፍር ራሱ ሊገባበት ይችላል፤+ ግንብን የሚያፈርስም በእባብ ሊነደፍ ይችላል።  ድንጋይ የሚፈነቅል ሰው በፈነቀለው ድንጋይ ሊጎዳ ይችላል፤ ግንድንም የሚፈልጥ አደጋ ሊያደርስበት ይችላል።* 10  ከብረት የተሠራ መሣሪያ ቢደንዝ፣ ሰውም ባይስለው ብዙ ጉልበት መጠቀም ያስፈልገዋል። ጥበብ ግን ስኬታማ ለመሆን ይረዳል። 11  እባብ በድግምት ከመፍዘዙ በፊት ቢነድፍ፣ በድግምት የተካነው ሰው* ምንም ጥቅም አያገኝም። 12  ጥበበኛ ሰው ከአፉ የሚወጡት ቃላት ሞገስ ያስገኙለታል፤+ የሞኝ ሰው ከንፈር ግን ለጥፋት ይዳርገዋል።+ 13  ከአፉ የሚወጡት የመጀመሪያ ቃላት ሞኝነት ይንጸባረቅባቸዋል፤+ የንግግሩ ማሳረጊያም የከፋ እብደት ነው። 14  ይሁንና ሞኙ ማውራቱን ይቀጥላል።+ ሰው ወደፊት የሚሆነውን ነገር አያውቅም፤ ከእሱ በኋላ የሚመጣውን ነገር ማን ሊነግረው ይችላል?+ 15  ሞኝ ሰው የሚሠራው አድካሚ ሥራ እንዲዝል ያደርገዋል፤ ወደ ከተማ የሚወስደውን መንገድ ማግኘት እንኳ አይችልምና። 16  አንዲት አገር ንጉሧ ልጅ ቢሆን፣+ መኳንንቷ ደግሞ በጠዋት ግብዣ ላይ የሚገኙ ቢሆኑ ምንኛ አሳዛኝ ነው! 17  ከትልቅ ቤተሰብ የተወለደ ንጉሥ ያላት እንዲሁም ለስካር ሳይሆን ብርታት ለማግኘት በተገቢው ጊዜ የሚመገቡ መኳንንት ያሏት አገር ምንኛ ደስተኛ ናት!+ 18  ስንፍና ሲበዛ ጣሪያ ይዘብጣል፤ እጆችም ካልሠሩ ቤት ያፈሳል።+ 19  ምግብ* ለሳቅ ይዘጋጃል፤ የወይን ጠጅም ሕይወትን አስደሳች ያደርጋል፤+ ይሁን እንጂ ገንዘብ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ያሟላል።+ 20  በሐሳብህ* እንኳ ንጉሡን አትርገም፤*+ በመኝታ ቤትህም ሆነህ ባለጸጋውን አትርገም፤ ቃሉን* ወፍ* ልትወስደው አሊያም ክንፍ ያላት ፍጥረት የተወራውን ደግማ ልትናገር ትችላለችና።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “በስተ ቀኙ ነው።”
ቃል በቃል “በስተ ግራው ነው።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ቃል በቃል “መንፈስ፤ እስትንፋስ።”
ወይም “ብቃት ያላቸው።”
“ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “የምላስ ጌታ።”
ቃል በቃል “ዳቦ።”
“በመኝታህ ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በንጉሡ ላይ ክፉ ቃል አትናገር።”
ወይም “መልእክቱን።”
ቃል በቃል “በሰማያት የምትበር ፍጥረት።”