መክብብ 12:1-14

  • እርጅና ሳይመጣ ፈጣሪን አስብ (1-8)

  • የሰብሳቢው የመደምደሚያ ቃላት (9-14)

    • “የጥበበኞች ቃላት እንደ በሬ መውጊያ ናቸው” (11)

    • “እውነተኛውን አምላክ ፍራ” (13)

12  እንግዲያው አስጨናቂ የሆኑት ዘመናት*+ ከመምጣታቸው እንዲሁም “ደስ አያሰኙኝም” የምትላቸው ዓመታት ከመድረሳቸው በፊት በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ፤+  ፀሐይ፣ ብርሃን፣ ጨረቃና ከዋክብት ከመጨለማቸው በፊት+ እንዲሁም ዶፍ ከጣለ በኋላ ደመናት ተመልሰው* ከመምጣታቸው በፊት ፈጣሪህን አስብ፤  በዚያን ጊዜ ቤት ጠባቂዎች* ይንቀጠቀጣሉ፤* ጠንካራ የነበሩ ሰዎች ይጎብጣሉ፤ የሚፈጩ ሴቶች ጥቂት በመሆናቸው ሥራቸውን ያቆማሉ፤ በመስኮት የሚያዩ ወይዛዝርትም ይጨልምባቸዋል፤+  ወደ መንገድ የሚያወጡ በሮች ይዘጋሉ፤ የወፍጮ ድምፅ ይቀንሳል፤ ሰውም የወፍ ድምፅ ይቀሰቅሰዋል፤ ሴቶች ልጆችም ሁሉ ዝግ ባለ ድምፅ ይዘምራሉ።+  በተጨማሪም ሰው ከፍታ ያስፈራዋል፤ በመንገድ ሲሄድም ይሸበራል። የአልሞንድ ዛፍ ያብባል፤+ ፌንጣም እየተጎተተ ይሄዳል፤ የምግብ ፍላጎት* ይጠፋል፤ ምክንያቱም ሰው ለረጅም ጊዜ ወደሚኖርበት ቤት ይሄዳል፤+ አልቃሾችም በጎዳና ይዞራሉ፤+  የብር ገመድ ሳይበጠስ፣ የወርቅ ሳህን ሳይሰበር፣ እንስራ በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፣ ከጉድጓድ ውኃ ለማውጣት የሚያገለግለው መንኮራኩር* ሳይሰበር ፈጣሪህን አስብ።  አፈር ቀድሞ ወደነበረበት መሬት ይመለሳል፤+ መንፈስም* ወደ ሰጪው፣ ወደ እውነተኛው አምላክ ይመለሳል።+  ሰብሳቢው+ “የከንቱ ከንቱ* ነው! ሁሉም ነገር ከንቱ ነው!” ይላል።+  ሰብሳቢው ጥበበኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሕዝቡ የሚያውቀውን ነገር ሁልጊዜ ያስተምር ነበር፤+ ብዙ ምሳሌዎችንም ማጠናቀር* ይችል ዘንድ አሰላሰለ እንዲሁም ሰፊ ምርምር አደረገ።+ 10  ሰብሳቢው ደስ የሚያሰኙ ቃላትን+ ለማግኘትና የእውነትን ቃል በትክክል ለመመዝገብ ጥረት አደረገ። 11  የጥበበኞች ቃላት እንደ በሬ መውጊያ ናቸው፤+ የሰበሰቧቸው አባባሎችም በሚገባ እንደተቸነከሩ ምስማሮች ናቸው፤ እነዚህ ቃላት ከአንድ እረኛ የተሰጡ ናቸው። 12  ልጄ ሆይ፣ ከዚህም ሌላ ይህን ማስጠንቀቂያ ልብ በል፦ ብዙ መጻሕፍት መጻፍ ማብቂያ የለውም፤ በእነሱ ዙሪያ ምርምር ማብዛትም ሰውነትን ያደክማል።+ 13  ሁሉ ነገር ከተሰማ በኋላ መደምደሚያው ይህ ነው፦ እውነተኛውን አምላክ ፍራ፤+ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤+ ይህ የሰው አጠቃላይ ግዴታ ነውና።+ 14  እውነተኛው አምላክ እያንዳንዱን የተሰወረ ነገር ጨምሮ ማንኛውንም ሥራ፣ ጥሩም ይሁን መጥፎ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የመከራ ቀናት።”
“ደመናት ዶፍ ይዘው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ይብረከረካሉ።”
ወይም “ዘበኞች።”
እዚህ ላይ የተሠራበት ቃል የምግብን ፍላጎት ለመቀስቀስ የሚያገለግልን ከእንጆሪ ጋር የሚመሳሰል ተክል ያመለክታል።
ወይም “መዘውር።”
ወይም “የሕይወት ኃይልም።”
ወይም “ዋጋ ቢስ።”
ወይም “በሥርዓት ማዘጋጀት።”