መክብብ 2:1-26

  • ሰለሞን፣ ያከናወናቸውን ሥራዎች መለስ ብሎ አሰበ (1-11)

  • የሰው ጥበብ ያለው አንጻራዊ ጥቅም (12-16)

  • የሰው ልፋት ከንቱ ነው (17-23)

  • ብላ፣ ጠጣ እንዲሁም በሥራህ ተደሰት (24-26)

2  እኔም በልቤ “እስቲ ደስታን ልፈትንና ምን መልካም ነገር እንደሚገኝ ልይ” አልኩ። ይሁንና ይህም ከንቱ ነበር።   ሳቅ “እብደት ነው!” ደስታም “ምን ይጠቅማል?” አልኩ።  በገዛ ጥበቤ እየተመራሁና ራሴን በወይን ጠጅ እያስደሰትኩ+ በጥልቀት መረመርኩ፤ ሰዎች አጭር በሆነው የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ሊያደርጉት የሚችሉት ከሁሉ የተሻለ ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ በሞኝነት እንኳ ሳይቀር ተመላለስኩ።  ታላላቅ ሥራዎችን አከናወንኩ።+ ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፤+ ወይንም ተከልኩ።+  ለራሴ የአትክልት ስፍራዎችንና መናፈሻዎችን አዘጋጀሁ፤ በእነዚህም ቦታዎች ሁሉንም ዓይነት የፍራፍሬ ዛፎች ተከልኩ።  በእርሻው መሬት ላይ እያደጉ ያሉትን ዛፎች* ለማጠጣት የውኃ ማጠራቀሚያዎችን ሠራሁ።  ወንድና ሴት አገልጋዮች አስመጣሁ፤+ በቤቴ የተወለዱ አገልጋዮችም* ነበሩኝ። በተጨማሪም ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ ብዛት ያላቸው እንስሶች፣ ከብቶችና መንጎች ነበሩኝ።+  ለራሴም ብርና ወርቅ፣+ የነገሥታትንና የአውራጃዎችን ውድ ሀብት* አከማቸሁ።+ ወንድና ሴት ዘፋኞችን እንዲሁም የሰው ልጆች እጅግ የሚደሰቱባቸውን ብዙ ሴቶች* ሰበሰብኩ።  በመሆኑም ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሰው ሆንኩ።+ ደግሞም ጥበቤ ከእኔ አልተለየችም። 10  የተመኘሁትን ነገር ሁሉ ራሴን አልነፈግኩም።*+ ልቤንም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ሁሉ አልከለከልኩትም፤ ልቤ በትጋት በማከናውነው ሥራ ሁሉ ደስ ይሰኝ ነበርና፤ ብዙ ለደከምኩበት ሥራ ሁሉ ያገኘሁት ወሮታ* ይህ ነበር።+ 11  ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሥራ ሁሉና ዳር ለማድረስ የደከምኩበትን ሥራ+ ሁሉ መለስ ብዬ ሳስብ፣ ሁሉ ነገር ከንቱ፣ ነፋስንም እንደማሳደድ መሆኑን አስተዋልኩ፤+ ከፀሐይም በታች እውነተኛ ፋይዳ* ያለው አንዳች ነገር አልነበረም።+ 12  ከዚያም ትኩረቴን ወደ ጥበብ፣ እብደትና ሞኝነት አዞርኩ።+ (ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል? ሊያደርግ የሚችለው ቀደም ሲል የተደረገውን ነገር ብቻ ነው።) 13  እኔም ብርሃን ከጨለማ የተሻለ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጥበብም ከሞኝነት የተሻለ ጥቅም እንዳለው ተገነዘብኩ።+ 14  የጥበበኛ ሰው ዓይኖች ያሉት በራሱ ላይ ነው፤*+ ሞኝ ሰው ግን በጨለማ ውስጥ ይሄዳል።+ ደግሞም የሁለቱም ፍጻሜ* አንድ እንደሆነ ተገነዘብኩ።+ 15  እኔም በልቤ “በሞኙ ላይ የሚደርሰው በእኔም ላይ ይደርሳል” አልኩ።+ ታዲያ እጅግ ጥበበኛ በመሆኔ ምን አተርፋለሁ? በልቤም “ይህም ከንቱ ነው” አልኩ። 16  ጥበበኛውም ሆነ ሞኙ ለዘለቄታው አይታወሱምና።+ ሁሉም በሚመጡት ዘመናት ይረሳሉ። ለመሆኑ ጥበበኛው የሚሞተው እንዴት ነው? ልክ እንደ ሞኙ ሰው ይሞታል።+ 17  እኔም ከፀሐይ በታች የሚሠራው ሥራ ሁሉ አስጨናቂ ሆኖ ስለታየኝ ሕይወትን ጠላሁ፤+ ሁሉም ከንቱ፣+ ነፋስንም እንደማሳደድ ነውና።+ 18  ከኋላዬ ለሚመጣው ሰው ትቼው ስለምሄድ+ ከፀሐይ በታች እጅግ የደከምኩበትን ሥራ ሁሉ+ ጠላሁ። 19  ጥበበኛ ወይም ሞኝ እንደሚሆን የሚያውቅ ማን ነው?+ ሆኖም ከፀሐይ በታች በድካሜና በጥበቤ ያፈራሁትን ነገር ሁሉ ይወርሰዋል። ይህም ቢሆን ከንቱ ነው። 20  በመሆኑም ከፀሐይ በታች በለፋሁበት አድካሚ ሥራ ሁሉ ልቤ ተስፋ መቁረጥ ጀመረ። 21  ሰው በጥበብ፣ በእውቀትና በብልሃት እየተመራ ሥራውን በትጋት ሊያከናውን ይችላል፤ ይሁንና ድርሻውን* ምንም ላልደከመበት ሰው ያስረክባል።+ ይህም ከንቱና እጅግ አሳዛኝ* ነው። 22  ሰው ከፀሐይ በታች ከደከመበት ሁሉና ተግቶ እንዲሠራ ከሚገፋፋው ብርቱ ፍላጎት* የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው?+ 23  በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሥራው የሚያስገኝለት ነገር ቢኖር ሥቃይና ብስጭት ነው፤+ በሌሊትም እንኳ ልቡ አያርፍም።+ ይህም ከንቱ ነው። 24  ሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት* የሚሻለው ነገር የለም።+ ይህም ቢሆን ከእውነተኛው አምላክ እጅ የተገኘ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ፤+ 25  ደግሞስ ከእኔ የተሻለ የሚበላና የሚጠጣ ማን ነው?+ 26  አምላክ እሱን ለሚያስደስት ሰው ጥበብ፣ እውቀትና ደስታ ይሰጣል፤+ ኃጢአተኛ ለሆነው ግን እውነተኛውን አምላክ ለሚያስደስት ሰው ይሰጥ ዘንድ የመሰብሰብና የማከማቸት ሥራ ሰጥቶታል።+ ይህም ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ ነው።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ጫካውን።”
ቃል በቃል “የቤቱ ወንዶች ልጆችም።”
ወይም “በነገሥታት እጅና በአውራጃዎች ውስጥ ብቻ የሚገኝ ንብረት።”
ወይም “እመቤቶች።”
ቃል በቃል “ዓይኖቼንም የፈለጉትን ነገር ሁሉ አልከለከልኳቸውም።”
ወይም “ድርሻ።”
ወይም “ጥቅም።”
ወይም “ዕጣ ፋንታ።”
ወይም “ዓይኖች ክፍት ናቸው።”
ወይም “ያለውን ሁሉ።”
ወይም “ታላቅ ኪሳራ።”
ቃል በቃል “ከልቡ ጥረት።”
ወይም “ነፍሱ መልካም ነገር እንድታገኝ ከማድረግ።”