መክብብ 5:1-20

  • ለአምላክ ተገቢውን ፍርሃት ማሳየት (1-7)

  • ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ከእነሱ በታች ያሉትን ይመለከታሉ (8, 9)

  • የሀብት ከንቱነት (10-20)

    • ገንዘብን የሚወዱ አይጠግቡም (10)

    • “የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው” (12)

5  ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ አካሄድህን ጠብቅ፤+ ሞኞች እንደሚያደርጉት መሥዋዕት ለማቅረብ ከመሄድ+ ይልቅ ለመስማት መሄድ ይሻላል፤+ እነሱ እየሠሩ ያሉት ነገር መጥፎ መሆኑን አያውቁምና።  በአፍህ ለመናገር አትጣደፍ፤ ልብህም በእውነተኛው አምላክ ፊት ለመናገር አይቸኩል፤+ እውነተኛው አምላክ በሰማያት፣ አንተ ግን በምድር ላይ ነህና። ስለዚህ የምትናገራቸው ቃላት ጥቂት ሊሆኑ ይገባል።+  ሐሳብ ሲበዛ* ለቅዠት ይዳርጋል፤+ የቃላት ብዛትም ሞኝን ሰው ለፍላፊ ያደርገዋል።+  ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤+ እሱ በሞኞች አይደሰትምና።+ ስእለትህን ፈጽም።+  ስእለት ተስለህ ሳትፈጽም ከምትቀር ባትሳል ይሻላል።+  አፍህ ወደ ኃጢአት እንዲመራህ* አትፍቀድ፤+ በመልአክም* ፊት “ተሳስቼ ነው” አትበል።+ እውነተኛው አምላክ በተናገርከው ነገር ተቆጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ?+  ሐሳብ ሲበዛ ቅዠት እንደሚያስከትል፣+ የቃላት ብዛት ደግሞ ከንቱነትን ያስከትላልና። አንተ ግን እውነተኛውን አምላክ ፍራ።+  በምትኖርበት ግዛት ውስጥ በድሃ ላይ ግፍ ሲፈጸም፣ ፍትሕ ሲጓደልና ጽድቅ ወደ ጎን ገሸሽ ሲደረግ ብታይ በዚህ ጉዳይ አትገረም።+ ይህን ባለሥልጣን፣ ከእሱ ከፍ ያለ ቦታ ያለው ይመለከተዋልና፤ ከእነሱም በላይ የሆኑ ሌሎች አሉ።  ከምድሩ የሚገኘውን ትርፍ ሁሉም ይከፋፈሉታል፤ ንጉሡ እንኳ የሚያስፈልገውን ነገር የሚያገኘው ከእርሻው ነው።+ 10  ብርን የሚወድ ብርን አይጠግብም፤ ሀብትንም የሚወድ በሚያገኘው ገቢ አይረካም።+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው።+ 11  መልካም ነገሮች ሲበዙ፣ በላተኛውም ይበዛል።+ ታዲያ በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ይህ ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል?+ 12  የሚበላው ጥቂትም ሆነ ብዙ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ ባለጸጋ ሰው ያለው ብዙ ሀብት ግን እንቅልፍ ይነሳዋል። 13  ከፀሐይ በታች ያየሁት እጅግ አሳዛኝ የሆነ ነገር* አለ፦ ይህም ባለቤቱ በገዛ ራሱ ላይ ጉዳት ለማምጣት ያከማቸው ሀብት ነው። 14  ይህ ሰው አደገኛ ነገር* ውስጥ በመግባቱ ሀብቱን አጥቷል፤ ልጅ በሚወልድበት ጊዜም ለልጁ የሚያወርሰው ምንም ነገር አይኖረውም።+ 15  ሰው ከእናቱ ማህፀን ራቁቱን እንደወጣ ሁሉ፣ ልክ እንደዚያው ተመልሶ ይሄዳል።+ ደግሞም ከደከመበት ነገር ሁሉ ሊወስደው የሚችል አንዳች ነገር የለም።+ 16  ይህም ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነገር* ነው፦ ሰው በዚያው በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ለነፋስ የሚደክም ሰው የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው?+ 17  ደግሞም በየቀኑ ጨለማ ውስጥ በከፍተኛ ብስጭት፣ በሕመምና በንዴት ይበላል።+ 18  እኔ ያየሁት መልካምና ተገቢ የሆነ ነገር፣ ሰው እውነተኛው አምላክ በሰጠው አጭር የሕይወት ዘመን ሁሉ መብላቱና መጠጣቱ እንዲሁም ከፀሐይ በታች በደከመበትና በትጋት ባከናወነው ሥራ ሁሉ ደስታ ማግኘቱ ነው፤+ ይህ ብድራቱ* ነውና።+ 19  ደግሞም እውነተኛው አምላክ ለሰው ሀብትና ቁሳዊ ንብረት+ ብሎም በእነዚህ ነገሮች የመደሰት ችሎታ ሲሰጠው ብድራቱን* ተቀብሎ በትጋት በሚያከናውነው ሥራ መደሰት ይገባዋል። ይህ የአምላክ ስጦታ ነው።+ 20  እውነተኛው አምላክ ልቡን ደስ በሚያሰኙ ነገሮች እንዲጠመድ ስለሚያደርገው የሚያልፈውን የሕይወት ዘመኑን ፈጽሞ ልብ አይለውም።*+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ጭንቀት ሲበዛ።”
ቃል በቃል “ሥጋህን ወደ ኃጢአት እንዲመራ።”
ወይም “በመልእክተኛም።”
ወይም “ክፉ ነገር።”
ወይም “ሥራ።”
ወይም “ክፉ ነገር።”
ወይም “ድርሻው።”
ወይም “ድርሻውን።”
ወይም “አያስታውሰውም።”