መክብብ 6:1-12

  • ሰው ባፈራው ንብረት ላይደሰት ይችላል (1-6)

  • ባለህ ነገር ተደሰት (7-12)

6  ከፀሐይ በታች ያየሁት ሌላ አሳዛኝ ነገር* አለ፤ ይህም በሰው ልጆች ላይ በተደጋጋሚ ሲከሰት ይታያል፦  እውነተኛው አምላክ፣ ሰው የሚፈልገውን ነገር* ሁሉ እንዳያጣ ሀብትን፣ ቁሳዊ ንብረትንና ክብርን ይሰጠዋል፤ ሆኖም እውነተኛው አምላክ በእነዚህ ነገሮች እንዲደሰት አያስችለውም፤ ከዚህ ይልቅ እንግዳ ሰው ይደሰትባቸዋል። ይህም ከንቱና እጅግ አስከፊ ነገር ነው።  አንድ ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፣ ብዙ ዓመት ቢኖርና ለእርጅና ቢበቃ፣ ወደ መቃብር ከመውረዱ በፊት ባሉት መልካም ነገሮች መደሰት ካልቻለ* ከእሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል እላለሁ።+  ከማህፀን የወጣው በከንቱ ነውና፤ በጨለማም ሄዷል፤ ስሙም በጨለማ ተሸፍኗል።  ፀሐይን ባያይና ምንም ነገር ባያውቅም እንኳ ከዚያኛው ይልቅ ይሄኛው ይሻላል።*+  ሰው ደስታ ካላገኘ ሁለት ጊዜ ሺህ ዓመት ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? ሁሉም የሚሄደው ወደ አንድ ቦታ አይደለም?+  የሰው ልጅ በትጋት የሚሠራው ሆዱን ለመሙላት ነው፤+ የምግብ ፍላጎቱ* ግን ፈጽሞ አይረካም።  ታዲያ ጥበበኛው ከሞኙ ሰው የሚሻለው በምንድን ነው?+ ድሃስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚችል* ማወቁ የሚያስገኝለት ጥቅም ምንድን ነው?  በምኞት ከመቅበዝበዝ* ይልቅ ዓይን በሚያየው መደሰት ይሻላል። ይህም ቢሆን ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ ነው። 10  አሁን ያለው ነገር ሁሉ አስቀድሞ ስያሜ የተሰጠው ነው፤ ደግሞም የሰው ምንነት የታወቀ ነው፤ ከእሱ ከሚበረታም ጋር ሊከራከር* አይችልም። 11  ቃል ሲበዛ* ከንቱነት ይበዛል፤ ታዲያ ይህ ለሰው ምን ጥቅም ያስገኛል? 12  ሰው በሕይወት ሳለ ይኸውም ከንቱ በሆነውና እንደ ጥላ በሚያልፈው አጭር የሕይወት ዘመኑ ሊያደርገው የሚችለው የተሻለ ነገር ምን እንደሆነ የሚያውቅ ማን ነው?+ እሱ ካለፈስ በኋላ ከፀሐይ በታች የሚሆነውን ነገር ማን ሊነግረው ይችላል?

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ክፉ ነገር።”
ወይም “ነፍሱ የምትሻውን ነገር።”
ወይም “ነፍሱ መደሰት ካልቻለች።”
ቃል በቃል “የተሻለ እረፍት አለው።”
ወይም “ነፍሱ።”
ቃል በቃል “በሕያዋን ፊት እንዴት መሄድ እንደሚችል።”
ወይም “ከነፍስ መቅበዝበዝ።”
ወይም “ሊሟገት።”
“ነገር ሲበዛ” ማለትም ሊሆን ይችላል።