መዝሙር 115:1-18
115 ከታማኝ ፍቅርህና ከታማኝነትህ የተነሳ+ለእኛ ሳይሆን፣ ይሖዋ ሆይ፣ ለእኛ ሳይሆን፣*ለስምህ ክብር ስጥ።+
2 ብሔራት “አምላካቸው የት አለ?”
ለምን ይበሉ?+
3 አምላካችን ያለው በሰማያት ነው፤እሱ የወደደውን ሁሉ ያደርጋል።
4 የእነሱ ጣዖቶች ከብርና ከወርቅ የተሠሩ፣የሰው እጅ ሥራ ናቸው።+
5 አፍ አላቸው፤ መናገር ግን አይችሉም፤+ዓይን አላቸው፤ ማየት ግን አይችሉም፤
6 ጆሮ አላቸው፤ መስማት ግን አይችሉም፤አፍንጫ አላቸው፤ ማሽተት ግን አይችሉም፤
7 እጅ አላቸው፤ መዳሰስ ግን አይችሉም፤እግር አላቸው፤ መራመድ ግን አይችሉም፤+በጉሮሯቸው የሚያሰሙት ድምፅ የለም።+
8 የሚሠሯቸውም ሆኑ የሚታመኑባቸው ሁሉ፣እንደ እነሱ ይሆናሉ።+
9 እስራኤል ሆይ፣ በይሖዋ ታመኑ፤+እሱ ረዳታቸውና ጋሻቸው ነው።+
10 የአሮን ቤት ሆይ፣+ በይሖዋ ታመኑ፤እሱ ረዳታቸውና ጋሻቸው ነው።
11 እናንተ ይሖዋን የምትፈሩ፣ በይሖዋ ታመኑ፤+እሱ ረዳታቸውና ጋሻቸው ነው።+
12 ይሖዋ ያስታውሰናል፤ ደግሞም ይባርከናል፤የእስራኤልን ቤት ይባርካል፤+የአሮንን ቤት ይባርካል።
13 ይሖዋ እሱን የሚፈሩትን፣ታናናሾችንም ሆነ ታላላቆችን ይባርካል።
14 ይሖዋ እናንተን፣አዎ፣ እናንተንና ልጆቻችሁን* ያበዛል።+
15 ሰማይንና ምድርን የሠራው+ይሖዋ ይባርካችሁ።+
16 ሰማያት የይሖዋ ናቸው፤+ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።+
17 ሙታንም ሆኑ ወደ ዝምታው ዓለም* የሚወርዱ ሁሉ፣+ያህን አያወድሱም።+
18 እኛ ግን ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም፣ያህን እናወድሳለን።
ያህን አወድሱ!*