መዝሙር 135:1-21

  • ለታላቅነቱ ያህን አወድሱ

    • ‘በግብፅ ምልክቶችንና ተአምራትን አደረገ’ (8, 9)

    • “ስምህ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” (13)

    • በድን የሆኑ ጣዖታት (15-18)

135  ያህን አወድሱ!* የይሖዋን ስም አወድሱ፤እናንተ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ውዳሴ አቅርቡ፤+   በይሖዋ ቤት፣በአምላካችን ቤት ቅጥር ግቢዎች የቆማችሁ ሁሉ አወድሱት።+   ይሖዋ ጥሩ ነውና፣+ ያህን አወድሱ። ደስ የሚያሰኝ ነውና፣ ለስሙ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ።   ያህ ያዕቆብን የራሱ፣እስራኤልን ልዩ ንብረቱ* አድርጎ መርጧልና።+   ይሖዋ ታላቅ መሆኑን በሚገባ አውቃለሁና፤ጌታችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ የላቀ ነው።+   በሰማይና በምድር፣ በባሕሮችና በጥልቆች ውስጥይሖዋ ደስ ያሰኘውን ነገር ሁሉ ያደርጋል።+   ደመና* ከምድር ዳርቻዎች ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርጋል፤በዝናብ ጊዜ መብረቅን ያበርቃል፤*ነፋሱን ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።+   በግብፅ የተወለደውንየሰውም ሆነ የእንስሳ በኩር ገደለ።+   ግብፅ ሆይ፣ በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ሁሉ ላይ፣+በመካከልሽ ምልክቶችንና ተአምራትን አደረገ።+ 10  ብዙ ብሔራትን መታ፤+ኃያላን ነገሥታትንም ገደለ፤+ 11  የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንን፣+የባሳንን ንጉሥ ኦግን፣+የከነአንንም መንግሥታት ሁሉ ድል አደረገ። 12  ምድራቸውን ርስት አድርጎ፣አዎ፣ ርስት አድርጎ ለሕዝቡ ለእስራኤል ሰጠ።+ 13  ይሖዋ ሆይ፣ ስምህ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ይሖዋ ሆይ፣ ዝናህ* ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዘልቃል።+ 14  ይሖዋ ለሕዝቡ ይሟገታልና፤*+ለአገልጋዮቹም ይራራል።*+ 15  የብሔራት ጣዖቶች ከብርና ከወርቅ የተሠሩ፣የሰው እጅ ሥራ ናቸው።+ 16  አፍ አላቸው፤ መናገር ግን አይችሉም፤+ዓይን አላቸው፤ ማየት ግን አይችሉም፤ 17  ጆሮ አላቸው፤ መስማት ግን አይችሉም። በአፋቸው ውስጥ እስትንፋስ የለም።+ 18  የሚሠሯቸውም ሆኑ የሚታመኑባቸው ሁሉ፣+እንደ እነሱ ይሆናሉ።+ 19  የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ይሖዋን አወድሱ። የአሮን ቤት ሆይ፣ ይሖዋን አወድሱ። 20  የሌዊ ቤት ሆይ፣ ይሖዋን አወድሱ።+ እናንተ ይሖዋን የምትፈሩ፣ ይሖዋን አወድሱ። 21  በኢየሩሳሌም የሚኖረው ይሖዋ፣+ከጽዮን ይወደስ።+ ያህን አወድሱ!+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ሃሌሉያህ!” “ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ወይም “ውድ ሀብቱ።”
ወይም “ተን።”
“ለዝናብ መውጫ ያዘጋጃል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ስምህ።” ቃል በቃል “መታሰቢያህ።”
ወይም “ጥብቅና ይቆማልና።”
ወይም “ይጸጸታል።”