መዝሙር 16:1-11

  • ይሖዋ የጥሩነት ምንጭ ነው

    • “ይሖዋ ድርሻዬ” ነው (5)

    • ‘በሌሊት በውስጤ ያለው ሐሳብ ያርመኛል’ (7)

    • ‘ይሖዋ በቀኜ ነው’ (8)

    • “መቃብር ውስጥ አትተወኝም” (10)

የዳዊት ሚክታም።* 16  አምላክ ሆይ፣ አንተን መጠጊያ አድርጌአለሁና ጠብቀኝ።+   ይሖዋን እንዲህ አልኩት፦ “አንተ ይሖዋ ነህ፤ ለእኔ የጥሩ ነገሮች ምንጭ አንተ ነህ።   ደግሞም በምድር ላይ ያሉት ቅዱሳን፣ክብር የተላበሱት አገልጋዮች እጅግ ደስ ያሰኙኛል።”+   ሌሎች አማልክትን የሚከተሉ ሐዘናቸውን ያበዛሉ።+ እንደ እነሱ ደምን የመጠጥ መባ አድርጌ አላቀርብም፤በከንፈሬም ስማቸውን አላነሳም።+   ይሖዋ ድርሻዬ፣ ዕጣ ፋንታዬና+ ጽዋዬ+ ነው። ርስቴን ትጠብቅልኛለህ።   ለእኔ ርስት አድርገህ ለመስጠት የለካኸው ቦታ ያማረ ነው። አዎ፣ ባገኘሁት ርስት ረክቻለሁ።+   ምክር የሰጠኝን ይሖዋን አወድሳለሁ።+ በሌሊትም እንኳ በውስጤ ያለው ሐሳብ* ያርመኛል።+   ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አደርገዋለሁ።+ እሱ በቀኜ ስላለ ፈጽሞ አልናወጥም።*+   ስለዚህ ልቤ ሐሴት ያደርጋል፤ ሁለንተናዬ* ደስ ይለዋል። ያለስጋትም እኖራለሁ።* 10  መቃብር* ውስጥ አትተወኝምና።*+ ታማኝ አገልጋይህ ጉድጓድ እንዲያይ* አትፈቅድም።+ 11  የሕይወትን መንገድ አሳወቅከኝ።+ በፊትህ* ብዙ ደስታ አለ፤+በቀኝህ ለዘላለም ደስታ* አለ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ጥልቅ ስሜቴ።” ቃል በቃል “ኩላሊቴ።”
ወይም “ፈጽሞ አልንገዳገድም (አልውተረተርም)።”
ቃል በቃል “ክብሬ።”
ወይም “ሥጋዬም ያለስጋት ይኖራል።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነፍሴን አትተዋትምና።”
“መበስበስን እንዲያይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ከፊትህ ጋር።”
ወይም “ፍስሐ።”